የዩኤስ ኤይድ ኃላፊ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በምን ጉዳይ ተወያዩ?

የፎቶው ባለመብት, FBC/USIAD
በኢትዮጵያ የብሔር ግጭትን የሚያነሳሱ ቃላቶችን መጠቀም ሊያመጣው የሚችለውን አደጋ በተመለከተ የፈጠረባቸውን ስጋት ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ኃላፊ ሰማንታ ፓወር ተናግረዋል።
ሰማንታ ፓወር እንዳሉት "ሰብዓዊነትን ዝቅ የሚያደርጉ ቃላት ውጥረቶችን ማባባስና በታሪክም እንደታዘብነው በብሄር ላይ የተመሰረተ ጭፍጨፋዎችን እንደሚያነሳሱ አይተናል" ብለዋል።
ኃላፊዋ በኢትዮጵያ እያደረጉ ባሉት ጉብኝት ከሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን በትግራይ ጦርነት ለተጎዱ ሚሊዮኖች እርዳታ ለማቅረብ ያለውን ፈታኝ ሁኔታ አንስተው መወያየታቸውን ገልፀዋል።
ኃላፊዋ በኢትዮጵያ ባለው ቆይታቸው ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ህወሃትን ለመግለፅ የሚጠቀሟቸውን ቃላቶች በተመለከተ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የህወሓትን አመራሮች ለመግለጽ 'አረም'፣ 'ካንሰር'፣ 'በሽታ' የሚሉ ቃላትን በመጠቀማቸው ተተችተዋል።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እነዚህን ቃላት የተጠቀምነው የትግራይን ህዝብ ለመግለፅ ሳይሆን ህወሃትን ነው ብለዋል።
ነገር ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘር ጭፍጨፋ አማካሪ እንዲህ አይነት ቃላቶች የሚያመጡትን መዘዝና ያላቸውን ስጋት አጋርተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የበለጠ ጥሰትና ወንጀሎች ሌሎች አካባቢ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችም ላይ ሊፈፀም ይችላል የሚልም ስጋት እንዳለ ተጠቁሞ በዘር ጭፍጨፋ ላይ ከፍተኛ ስራ ከመስራታቸው አንፃር እንዲህ አይነት ቃላቶች ሲሰሙ ምን ይሰማዎታል ተብለዋል።
ኃላፊዋ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊያነሷቸው የሚገቡ ጉዳዮችን ከሰላም ሚኒስትሯም ጋር ማንሳታቸውን አውስተው ሰብዓዊነትን ዝቅ የሚያደርጉ እና ጥላቻ የሚሰብኩ ትርክቶች ውጥረትን ከማባበስ በተጨማሪ ወደ ውይይትም ለመምጣት አዳጋች ይሆናል ብለዋል።
አሜሪካን ጨምሮ በሌሎች አገራት በጥላቻ የተሞሉ ትርክቶችን ሲሰሙ እርምጃ የሚወስዱ ሰዎችን ሊያነሳሳ ይችላልም በማለት የቃላቶችን ጠቃሚነት አጉልተዋል።
እነዚህ ትርክቶችም በረድዔት ሰራተኞችም ላይ ማነጣጠራቸውን አንስተዋል። በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በተለያዩ ፅሁፎች ላይ መውጣታቸውን ተከትሎ አሰቃቂ የሆኑ ጥቃቶች በረድዔት ሰራተኞች ላይ እየተፈፀሙ ነው ብለዋል።
ኃላፊዋ በመግቢያ ንግግራቸውም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡት በአውሮፓውያኑ 2016 በወቅቱም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አምባሳደር በነበሩበት ወቅት መሆኑን ገልፀው በወቅቱም ያለ ፍትህ የታሰሩ ሴት የፖለቲካ እስረኞችን ለማስለቀቅ የነበረ ዘመቻ አካል ነበሩ።
በወቅቱ ዘመቻው በቀድሞው አስተዳደር የታሰሩትን ሶስት ሴት ፖለቲከኞች ለማስለቀቅ ያለመ ነበር ሲሉ አስታውሰዋል። አሁን ግን ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ በርካታ ለውጦችን ወዳካሄደችው ኢትዮጵያ መመለሳቸውን አውስተዋል።
ሊያስፈቱ የመጧቸውን ሶስቱ የፖለቲካ እስረኞችን ጨምሮ በብዙ አስር ሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ነፃ መውጣታቸውን በመጥቀስ አገሪቷ ያሳየችውንም ለውጥ አድንቀዋል።
በተቃራኒው በትግራይ የተከሰተው ጦርነት ዘጠኝ ወራትን ደፍኖ 5.2 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ በከፋ ሁኔታ ላይ መገኘቱም ሁኔታውን የጨለመ ያደርገዋል ብለዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ አሜሪካ የቀድሞውን አስተዳደር የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ የወቅቱንም አስተዳደር እርዳታ እንዲገባ ሲጠይቅና ግጭቶች እንዲቆሙ ስትጠይቅ በመርሆች ላይ የተመሰረተ ነው በማለት የመንግሥታቸውን አቋም ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልን የምንፈልገው ከህዝቡም ሆነ ከመንግሥታችሁ ጋር የምንነጋገረው በተወሰኑ መርሆች ላይ ተመርኩዘን ነው። በግጭት ላይ ለማንም ለማዳላት ወይም ለአንድ ወገን በመወገን አይደለም" ብለዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ኃላፊዋ መርሆች ብለው የጠቀሱትም ለግጭት ወታደራዊ መፍትሄ የለውም የሚለውን እሳቤ፣ ሁሉም አካላት ከውጊያ ታቅበው አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈርሙና ውይይት እንዲጀምሩና ስለ እርቅና ሚሊሻና ወታደሮች ከአጎራባች ክልሎች የሚወጡበትን መንገድ እንዲያበጁ የሚሉ ናቸው።
በዚህም የመንግሥታቸውን አቋም ለሰላም ሚኒስትሯ አስረድተዋል። ግዛቶች ከጦርነቱ በፊት እንደነበረው እንዲመለሱና የህወሓት ኃይሎች ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች እንዲወጡ እንዲሁም በትግራይ ክልል የሚገኙ የአማራ ክልል ኃይሎችም ይውጡ ሲሉ ጠይቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪም ትግራይ ያለው የኤርትራ ሠራዊት በአስቸኳይ እና ለጨመረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ መውጣት እንዳለበት ገልፀው በድርድር ላይ የተመሰረተ አስቸኳይ የተኩስ አቁም አስፈላጊነትን አፅንኦት ሰጥተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አሜሪካ ከትግራይ አልፎ በአጎራባች ክልሎች የተዛመተውን ጦርነት በከፍተኛ ስጋት እየተከታተለችው ነው ብለዋል።
ህወሃት ወደ እነዚህ አካባቢዎች ጦርነቱን ማስፋቱን ተከትሎ አሁን ባለው ሁኔታ 76 ሺህ ሰዎች በአፋር፣ 150 ሺህ ሰዎች ደግሞ ከአማራ ተፈናቅለዋል ብለዋል።
ይህም ወደበለጠ ጥፋት ሊወስድ ስለሚችል ሁሉም አካላት ከግጭት እንዲታቀቡ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ሌሎች ያነሷቸው መርሆች የረድዔት ድርጅት ሰራተኞች በከፍተኛ ሁኔታ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን እርዳታ እንዲያደርሱ በነፃነት ስራቸውን ማከናወን እንደሚገባቸውም ነው።
" የእርዳታ ሰራተኞቹ በፍፁም ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ወይም ኢላማ ሊሆኑ አይገባም፣ ትንኮሳም ሊፈፀምባቸው አይገባም" ብለዋል።
ኃላፊዋ ለአንድ ወገን አሜሪካ እያዳላች ነው የሚለውን እንደማይቀበሉ አፅንኦት የሰጡ ሲሆን ለህወሃትም ቢሆን የተኩስ አቁምና በድርድር ላይ የተመሰረተ ስምምነትን አስፈላጊነትን ለአመራሮቹ መንገራቸውን አስታውሰዋል።
በኦባማ አስተዳደር ወቅት ነፃ ምርጫ እንዲደረግ፣ በሲቪል ሶሳይቲ ጉዳይ ላይ ያሉ አሳሪ ህጎች እንዲላሉና መድረኩ እንዲከፈት እንዲሁም የዜጎች መብት እንዲከበር ስንሰራ ነበር አሁንም ቀጥሏል ብለዋል።
አሁንም ቢሆን በወገንተኝነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በሰብዓዊ መብቶች እና አለም አቀፍ ሰብዓዊ ህጎች ላይ የተመሰረተ ነው በማለትም በጦርነቱ የሚሳተፉ አካላት እነዚህን መርሆች በመተዋቸውና በመጣሳቸው እንዲያከብሩ ነው ጥሪ ነው የምናቀርበው ብለዋል።
ሰማንታ ፓወር አክለውም "መግለጫዎቻችን የተመሰረቱት መሬት ላይ እየሰሩ ካሉት አጋሮቻችን በሚሰጡን እውነታ ላይ በተመረኮዘ መረጃ ነው" ሲሉ አብራርተዋል።
"ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ የሚያግድ ከሆነ፣ የአማራ ሚሊሻ ንፁሃንን እየጎዱ ከሆነና እርዳታንም እያገዱ ከሆነ ፣የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉና ጥሰቶች እየፈፀሙ ከሆነ እርዳታንም የሚዘርፉ ከሆነ መነገር አለባቸው። እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታዎችን የሚያግድ ከሆነ ነፃ በሆነ መንገድ የመናገር ኃላፊነት አለብን" ብለዋል።
የሰብዓዊ እርዳታን በተመለከተ
በትናንትናው ዕለት ከአዲስ አበባ ራቅ ያላለ የየኤስአይድ የምግብ ማከማቻ የጎበኙ ሲሆን በዚያም ስፍራ በርካታ ክምችት ስንዴ፣ ምስርና ክክ በብዛት ቢኖርም ቢኖርም የጭነት መኪኖቹ ያለ ስራ ቆመዋል ብለዋል።
በክልሉ ባለው የእርዳታ መዘጋትም ምክንያት እርዳታዎች ለሳምንታት ያህል መድረስ አልተቻለም።
የእርዳታ ተደራሽነቱ ጉዳይ የበለጠ የሚያሳስብ ሆኗል ያሉት ኃላፊዋ በክልሉ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስም ለመፍታት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ500-600 እርዳታ የጫኑ መኪኖች በየሳምንቱ ትግራይ መግባት አለባቸው ቢልም ከሁለት ቀናት በፊት በነበረው መረጃ መሰረት 153 የጭነት መኪኖች ወደ ትግራይ ገብተዋል።
በተመድ መሰረት በባለፉት ሳምንታት 1500 የጭነት መኪኖች መግባት ቢያስፈልግም እስካሁን የገባው 153 ነው ይህም ማለት ከሚያስፈልገው 10 በመቶ ነው ተብሏል።
በተወሰነ መልኩ ስርዓቱና ፈቃዶች ላይ መሻሻል ቢታይም የእርዳታ መዘግየትና ህይወት አድን እርዳታዎችን ለማድረስ ማየት የሚፈለገውን ለውጥ ማየት አልተቻለም ብለዋል።
ለረዥም አመታት ኢትዮጵያ የአሜሪካ አጋር ነች በማለትም በተለይም በባለፈው አመት ብቻ አሜሪካ አንድ ቢሊዮን እርዳታ አድርጋለች፤ ከዚህም ውስጥ ከ750 ሚሊዮን በላይ ለሰብዓዊ እርዳታ ውሏል።
በትግራይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍሎች ከፍተኛ እርዳታ እያደጉ መሆናቸውን ጠቅሰው አሁንም ለተፈናቀሉት ሰዎች በምን መንገድ እርዳታ ማድረግ እንደሚቻልም እየተወያዩ መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በባለፈው ሳምንት ከ149 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለወራት በዘለቀው ግጭት ለተጎዱ የትግራይ ነዋሪዎች ከተሰጠው የሰብዓዊ እርዳታ በተጨማሪ በዛሬው ዕለት 45 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ለኮቪድ-19 ድጋፍና የጤና ስርዓቱን ለመደገፍ እንዲውልም በሚል ድጋፍ ተደርጓል።
ይሄም አሜሪካ /ዩኤስ ኤይድ በውጭ አገራት ወረርሽኙን ለመዋጋት ከመደበችው ውስጥ 740 ሚሊዮን ዶላር የሚካተት ነው። ከዚህም ውስጥ 445 ሚሊዮን ዶላሩ ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የሚውል ነው።
ከዚህም በተጨማሪ 1.6 ሚሊዮን ዶዝ ያለው የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ተደርጓል። እነዚህ ድጋፎች አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ቁርጠኛ ድጋፍ ማሳያ ናቸው ብለዋል።












