የትግራይ ተወላጆች እስርና የፈጠረባቸው ስጋት

የፎቶው ባለመብት, Sean Gallup
በርካታ የትግራይ ተወላጆች አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በጅምላ እየታሰሩ፣ አካላዊ ጉዳትና ማስፈራራት እየደረሰባቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
ባለፈው ሳምንት ቢቢሲ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች "ማንነት መሰረት ያደረገ እስራትና እንግልት እየደረሰብን ነው" ይላሉ።
መንግሥት በበኩሉ አንድም በማንነቱ ምክንያት የታሰረና የተንገላታ እንደሌለ በመግለጽ በግለሰቦቹ የቀረበውን አቤቱታ አጣጥሏቸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሐምሌ 09/2013 ባወጣው መግለጫ በንፁሃን ዜጎች ላይ እንግልትና እስር፣ የንግድ ተቋማት መዝጋት ተፈጽሟል በማለት ቁጥሩን ያልገለጸው ሞት እንዳጋጠመም ጠቁሟል።
የመብት ተሟጓቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የትግራይ ተወላጆችን ከሕግ ውጪ አስሯል በማለት እርምጃው "ማንነት መሰረት ያደረገ" እንደሚመስል ገልጿል።
ታስረው የተፈቱ እና የቤተሰብ አባላሎቻው የታሰሩባቸው ቤተሰቦች ይህ ድርጊት ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ እንደቀጠለ ይናገራሉ።
አክለውም አንዳንዶች በዋስ ሲፈቱ አብዛኛዎቹ ግን ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡና ያሉበትን ቦታ ማወቅ አዳጋች እንደሆነባቸው ገልፀዋል።
ለቀናት በተለያዩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎች ቆይተው የወጡ እና የንግድ ተቋሞቻቸው የተዘጉቸው ግለሰቦች፣ የከተማዋ የጸጥታ አካላትና አስተዳዳሪዎች ያለአግባብ እያንገላቱን ነው የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ።
ይህ አዲስ እስርና የሚያንቀሳቅሷቸው የንግድ ተቋማት መዝጋት፤ የፌደራል መንግሥት ሠራዊቱን ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ማስወጣቱን ተከትሎ እያጋጠመ ያለ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹና የመብት ተሟጓቾች ይገልጻሉ።
በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል ውስጥ ግጭቱ ከጀመረ በኋላ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ትጥቃቸው እንዲፈቱና ወደ ሥራ እንዳይገቡ መደረጉን ሲገለጽ፤ አንዳንዶቹ ይህ በማንነታቸው ምክንያት እንደሆነ ተናግረው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከእስር የተለቀቁት ምን ይላሉ?
ጎይቶም መኮንን ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም ከጓደኛው ጋር ሻይ በሚጣጠበት ቦሌ ኤድናሞል አካባቢ ከሚገኘው ካፌ ተወስዶ መታሰሩን ይናገራል።
"አላየናቸውም፤ ግን 10 የሚሆኑ የጸጥታ አካላት መጥተው ስልኮቻችን ቀምተው በፖሊስ መኪና ወደ ማላውቀው ቦታ ወሰዱን" ይላል።
በወቅቱ እርሱና ጓደኞቹ ስልኮቻቸው ተፈትሸው፣ ወደ አዲስ አበባ የመጡበት ምክንያት ምን እንደሆነ ተጠይቆ ቢፈታም፤ ሐምሌ 11/2013 ዓ.ም ከቤቱ ተወስዶ ለአራት ቀናት ያህል መታሰሩን ይናገራል።
"ጠዋት 12፡00 ከእንቅልፌ ቀስቅሰው ነው የወሰዱኝ፤ ቤት ውስጥ የነበሩ ላፕቶች፣ ስልክና ወረቀቶችን ወሰዱ። በጊዜው በካራማራ ፖሊስ ጣቢያ የነበረው መርማሪ ተጋሩዎች ረበሻችሁን እያለ ብዙ ውርጂብኝ ሲያደርስብኝ ነበር" ብሏል።
የቤተሰብ አባላቶቿ፣ የቅርብ ዘመድና ጓደኞቿ በአጠቃላይ 20 ሰዎች እንደታሰሩባት የምትናገረው የአዲስ አበባ ነዋሪዋ ሕይወት በበኩሏ፤ ያሉበትን ቦታ እደማታውቅ ትናገራለች።
ሕይወት በአንድ ስሙን መጥቀስ ባልፈለገችው ሆቴል ውስጥ ተቀጥራ ትሰራ እንደነበር እና አሁን ግን ሆቴሉም ተዘግቶ ሥራ መፍታቷን ለቢቢሲ ገልጻለች።
አክላም "የባንክ ሂሳባችንም ስለተዘጋ የገንዘብ ችግር ገጥሞኛል። ብዙ የትግራይ ተወላጅ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል፤ ሆቴላችንም ታሽጓል። እየደረሰብን ያለው ጉዳት ብዙ ነው።"
"ከዚህ በፊት እኔ ራሴ ታስሬያለሁ፤ ከዛ በኋላም ፖሊስ ይከታተለኛል። ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ሰው ይታሰራል፤ በዚህ ጊዜ የሚደርስብኝ ድብደባ አለ፣ 'ጁንታ ደገፋችሁ' በማለት የሚደርስ እንግልት አለ።"
ጎይቶም ታስሮ በነበረበት ወቅት ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበር በመግለጽ "ወደ ፍርድ ቤት ስቀርብ ገንዘብ ተቀብሎ ረብሻ ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ እጅ ከፍንጅ ይዘነዋል የሚል ክስ ቀረበብኝ፤ ደነገጥኩ። እኔ ግን ሥራዬም ከፖለቲካ ውጪ እንደሆነና የተባለውን አለመፈጸሜን፣ የባንክ ሂሳቤ ትግራይ የተከፈተ በመሆኑ እንደተዘጋ አስረዳሁ። ይህን ለማጣራት ፖሊስ ሁለት ቀን ተሰጠው" ይላል።
ሆኖም በቀጣዩ ቀጠሮ የቀረበው ክስ ውድቅ በመደረጉ በአንድ ሺ ብር ዋስ መፈታቱን ይናገራል።
በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ መታወቂያ እንደተጠየቀና እንደተፈተሸ የሚናገረው ዳዊት ኃይሉ የቅርብ ቤተሰቤ ታስሯል ከሚሉት ወገን ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የዚህ ዓመት ተመራቂውና የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት በሚደረጉ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ የሚታወቀው ወጣት ጸጋዝአብ ኪዳኑ ወደ መኖሪያ ቤቱ በመምጣት ፖሊስ አብሮት የነበረውን የቅርብ ዘመዱን መውሰዱን ይገልጻል።
እሱ እንደሚለው ፖሊስ ምሽት 2፡30 የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሳይዝ ከቤት እንደወሰደውና ቤተሰቦቹ ለአንድ ወር ሙሉ ያለበትን ቦታና ሁኔታ ሳያውቁ እንደቆዩ ያስረዳል።
"ሲነጋ የፌደራል ፖሊስ ምርመራ ጽህፈት ቤት እንዳለ ሰምተን ሄደን አገኘነው፤ በሦስተኛው ቀን ስንሄድ ግን ተፈቷል አሉን። ተፈትቶ ወዴት ሄደ? ብለን ስንጠይቅ ግን ማወቅ አልቻልንም። በዚህ ሁኔታ አንድ ወር ስናፈላልግ ቆይተን መጨረሻ ላይ በአካል እንዲቀርብ ክስ መሰረትን። በዚህ ወቅት ነው ፖሊስ አዋሽ አርባ እንዳለ ያሳወቀን" ብሏል።
በዚህ ጊዜ፤ ፖሊስ መንግሥትን በኃይል ለመጣል፣ ከሽብርተኛ አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠርና በማኅበራዊ ሚዲያ የውሸት መረጃዎችን ማሰራጨት የሚሉ ክሶችን ይዞ ፍርድቤት መቅረቡን ይናገራል።
የቤተሰቡ አባላት ግን ክሶቹ ፈጽሞ ከእሱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ናቸው በማለት አይቀበሏቸውም።
ነገር ግን ይህ ለአብዛኛዎቹ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ግለሰቦች እየቀረበ ያለው ክስ መሆኑን በመግለጽ "ማንነት ትኩረት ያደረገ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ለምሳሌ ሸዋ ዳቦ አካባቢ ሰዎች መታወቂያ ተጠይቀው በጅምላ ሲወሰዱ፣ 22 አካባቢ የተጋሩ የንግድ ተቋማት ተለይተው ሲዘጉ አይቻለሁ" የሚለው ዳዊት ሁኔታው ያሰጋኛል ይላል።
'ባለቤቴ የትግራይ ሰው ስለሆነ ነው የታሰረው'
የአምስት ልጆች እናት የሆነችውና የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ግለሰብ ስሟ እንዳይገለጽ በመጠየቅ፣ ከሦስት ሳምንት በፊት ባለቤቷ ከሚሰራበት ቦታ መታሰሩንና እስከ አሁን ፍርድ ቤት አለመቅረቡን ተናግራለች።
"እኔ ደሴ ተወልጄ ነው ያደግኩት፤ ባለቤቴ ግን የትግራይ ሰው ነው። እዚህም እዛም የሚል ሰው ሆኖ ሳይሆን ከትግራይ ስለሆነ ነው የታሰረው ነው የምለው። የእኛን ጨምሮ የትግራይ ተወላጆች የሚኖሩባቸው ቤቶች በሙሉ ተፈትሸዋል።"
በሐምሌ ወር አጋማሽ የባይቶና ዓባይ ትግራይ ከፍተኛ አመራር የሆነው አቶ ክብሮም በርሀ በአዲስ አበባ አንድ ካፍቴሪያ በፖሊሶች መወሰዱንና እስከ አሁን የት እንዳለ እንደማያውቁ ጓደኞቹና ባለቤቱ ይናገራሉ።
አሁንም የት እንዳለ አላውቅም የምትለው ባለቤቱ ወይዘሮ ትዝታ፤ መሳርያና ሌሎች ሕጋዊ ያልሆኑ ነገሮች አሉ በሚል በተደጋጋሚ ቤቷ እንደተፈተሸና ስጋት ውስጥ እንዳለች ገልጻለች።
"የት እንደሄደ ስጠይቅ 'የበላይ ትዕዛዝ ነው' ከሚል ውጪ ሌላ አይነገረኝም። እሱ ፖለቲከኛ ነው፤ ግን በአጠቃላይ ሲቪሎች ላይ የሚደርሰው እንግልት ልክ የለውም" የምትለው ወይዘሮ ትዝታ ችግሩ "አስከፊ ነው" ትላለች።
ፖሊስ ምን ይላል?
በአዲስ አበባ፣ ሶማሌ ክልል፣ አማራ ክልል፣ ድሬዳዋ ከተማና ሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ መታሰራቸውና የንግድ ተቋማቶቻቸው መዘጋታቸውን ይነገራል።
የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በሐምሌ 15/2013 ዓ.ም ለህወሓት እርዳታ ሲያደርጉ ነበሩ ያላቸው 28 ግለሰቦችና ንብረታቸው በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የክልሉ ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር መሐመድ ዓሊ 28 ግለሰቦች፣ 10 የሲኖትራክ መኪናና ሌሎች ንብረቶች በኅብረተሰቡ ጥቆማ መሰረት መያዛቸውን ሲገልጹ፤ "ግለሰቦቹ በክልሉ ብጥብጥ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው" ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።
የአዲስ ፖሊስ ኮሚሽን ሐምሌ 21/2021 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ከሰኔ 19 እስከ ሐምሌ 8 2013 ዓ.ም በሁሉም የከተማዋ ክፍለ ከተሞች ፍተሻ ማካሄዱን ገልጿል።
ኮሚሽነር ጌቱ አርጋውን ጠቅሶ የአዲስ አበባ ፖሊስ በማኅበራዊ ገጹ ላይ በከተማዋ "ብጥብጥና ረብሻ ለማስነሳት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 325 ግለሰቦች በሕግ አግባብ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ" አስፍሯል።
በተጨማሪም በአንዳንድ መዝናኛና የጭፈራ ቤቶች የአገሪቱን ሰንደቅ አላማ "በሚያዋርድ መልኩ ያልተገባ ድርጊት እየፈፀሙ ሲጨፍሩ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው" የሚገኙ ግለሰቦችም እንዳሉ ተገልጿል።
በዚህም በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች በተጨማሪ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮሚሽነር ጌቱ አመልክተዋል።
ፖሊስ በተለያዩ ግሮሰሪዎች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ሆቴሎችና ሌሎች የንግድ ተቋማት የሚገኙባቸው 793 ተቋማት በተካሄደው ፍተሻ ሽጉጦችና የሽጉጥ ጥይቶች እንዲሁም ላፕቶፕ ኮምፒዩተር፣ ፍላሽ፣ ሞባይልና ሌሎችንም በማስረጃነት መያዙን ኮሚሽኑ በፌስቡክ ገጽ ባሰራጨው መረጃ ገልጿል።
በዚህ መሰረት ፖሊስ አንድም ግለሰብ በማንነቱ ምክንያት እንዳላሰረና ተቋሞቻቸውም አለመዝጋቱን ያስረዳል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ቃል አቀባይ ፋሲካ ፈንታ የታሰሩም ሆነ የተዘጉ የንግድ ተቋማት ስለመኖራቸው "የማውቀው የለም" ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ በበኩላቸው፤ "ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ ማንም ሰው ማንነቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ለእስር አልተዳረገም" ሲሉ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ግን እርምጃው የትግራይ ተወላጆችን ለማሸማቀቅና ለማንገላታት እንደሆነ በመግለጽ "ጥቃት" እየደረሰብን ነው ይላሉ።
ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወይም ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ወቅት አንድ አይነት ክስ እንደሚቀርብባቸው በመግለጽ ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥሪ
ዓለም አቀፍ የትግራይ ምሁራን ማኅበር ባወጣው መግለጫ በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል እየቀጠለ ባለው ግጭት ምክንያት ብዙ የትግራይ ተወላጆች በጅምላ ታስረዋል፣ ተንገላተዋል፣ ያሉበት ቦታ አይታወቅም በማለት ክስተቱን እንዲቆም ተማጽኗል።
የትግራይ መብት ተሟጓቾችም ሁኔታው ትልቅ ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው በመግለጽ "ለረጅም ጊዜ ወደ ትግራይ ሄደው የማያውቁና ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሌላቸው ሰላማዊ ሰዎች ሳይቀር እየታሰሩ ነው" በማለት ድርጊቱን ይቃወማሉ።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ መንግሥት ተጋላጭ ለሆነው የማኅበረሰብ ክፍል ከፍተኛ ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት አለበት ያሉ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታውን በተመለከተ የሚያደርገውን የክትትል ሥራ ይቀጥላል ብለዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽል በበኩሉ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ የትግራይ ተወላጆችን ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መልኩ አስሯል ብሏል።
አምነስቲ፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች መታሰራቸውን እንዲሁም ለአምንስቲ ቃላቸውን የሰጡ ከእስር የወጡ የትግራይ ተወላጆች እስር ቤቶች ትግርኛ ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች እንደተሞሉ መናገራቸውን የድርጅቱ የምሥራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዲፕሮስ ሙሽን ገልጿል።
አምነስቲ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ታስረው ይገኛሉ ያለ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስርን እንዲያቆም ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቁ ጠይቋል።
















