የህወሓት ኃይሎች በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት መሰንዘር እንዲያቆሙ አሜሪካ አሳሰበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል በሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እና ማስፈራራት እንዲቆም ጠየቀ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጄሊና ፖርተር በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ዛቻ እንዲሁም ጥቃት እየደረሰ እንደሚገኝ ሪፖርቶች እንደደረሷቸው ገልጸዋል። ይህ ጥቃት በአፋጣኝ እንዲገታም አሳስበዋል።
"ከህወሓት ጋር ግንኙነት ባላቸው ታጣቂ ኃይሎች እና በትግራይ ሚሊሻ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ በክልሉ ውስጥ ጥቃት እየተሰነዘረ እንደሆነ የሚያሳዩ አስተማማኝ መረጃዎች ደርሰውናል። ይህም በጣም አስግቶናል" ብለዋል ቃል አቀባይዋ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ላይ በትግራይ ክልል ያሉ ኤርትራውያን ስደተኞች ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን አመልክቶ የተገደሉ ስደተኞች መኖራቸውንም መግለጹ ይታወሳል።
በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት እየተሰነዘረ እንደሆነ የሚጠቁሙ አስተማማኝ ሪፖርቶች እንደደረሰው የገለጸው የአሜሪካ መንግሥትም ሁኔታው በእጅጉ እንዳሳሰበው አመልክቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጄሊና "ትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ታጣቂ ኃይሎች ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ጥቃት መሰንዘር እንዲሁም ዛቻ እንዲያቆሙ እንጠይቃለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች፣ በግጭቱ ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎች እንዲሁም ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች ላይ ጥቃት እንዳይሰነዘርም አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት እንደ አዲስ ያገረሸው ሰብዓዊ ቀውስ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጾ፤ በትግራይ ክልል በሚገኙ ሁለት የስደተኞች መጠለያዎች የሚኖሩ ወደ 24,000 የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ሰብዓዊ ድጋፍ እንደተቋረጠባቸው ገልጿል።
እነዚህ ስደተኞች ምግብ እንዲሁም የመጠጥ ውሃ ሊያልቅባቸው እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ትላንት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
ትላንት ባወጣው ሪፖርት ላይ በማይ አይኒ እና አዲ ሃሩሽ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች እና በአቅራቢያቸው ግጭት መኖሩን ገልጾ ሁለት ስደተኞች ተገድለዋል ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ወደ 24 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች የተጠለሉባቸው ጣቢያዎችን መድረስ አለመቻሉን ገልጸ "በመጠለያ ጣቢያዎቹ ምግብ እና ውሃ አልቆ ሊሆን ይችላል" ብሏል።
ከቀናት በፊት መንግሥታዊው የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ የህወሓት አማጺያን መሠረተ ልማቶችን ለወታደራዊ አገልግሎት እያዋሉ በመሆኑ በትግራይ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው ማለቱ ይታወሳል።
አብዛኛውን ትግራይ ተቆጣጠሮ የሚገኘው ህወሓት በበኩሉ በክልሉ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን በመተለከተ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ላይ በትግራይ ያሉ ስደተኞች መፈናቀል እና ተፈጽመዋል የተባሉ ጥቃቶች እጅጉን አሳስቦኛል ብሎ ነበር።
በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከመቀስቀሱ በፊት አንድ መቶ ሺህ ያህል ኤርትራውያን ስደተኞች በተለያዩ የስደተኞ መጠለያዎች ይገኙ የነበሩ ሲሆን ከጦርነቱ በኋላ ግን ወደተለያዩ አካባቢዎች መሸሻቸው ይነገራል።
ለኤርትራውያኑ ስደተኞች ከትግራይ ክልል ውጪ በአማራ ክልል ውስጥ ተጨማሪ መጠለያ ካምፕ ለመክፈት ጥረት እተደረገ መሆኑን የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ከዚህ በፊት አሳውቆ ነበር።













