የአሜሪካና የሱዳን ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ተወያዩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና ስለሱዳን የሽግግር ሂደት መወያየታቸው ተነገረ።
ሁለቱ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች መዛመቱን እንዲሁም በትግራይ ክልል እያሽቆለቆለ ስለመጣው የሰብዓዊ ሁኔታ በተመለከተ ያላቸውን ስጋት አንስተው መወያየታቸው ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ረቡዕ ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ ባለሥልጣናቱ ከዚህም በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች እንደገና ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል ስለሚሉ ሪፖርቶችና በቀጠናው መረጋጋት ላይ ስለሚያሳድረው ተፅእኖ መክረዋል ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከንና ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ሁሉም ወገኖች በስምምነት ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ለማበረታታት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ውይይትና እና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት ለማስጠበቅ እንዲሁም እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ያልተገደበ ተደራሽነት እንዲኖር ለመስራትም ተስማምተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ባለሥልጣናት በሱዳን እየተካሄደ ያለው ዴሞክራሲያዊ ሽግግር መሻሻል ላይ እና የአሜሪካ-ሱዳን ግንኙነቶችን ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይም ተወያይተዋል።
ከሰሞኑ በሱዳን ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ግዛቶች ከጦርነቱ በፊት እንደነበረው እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
በዚህም መሰረት የህወሓት ኃይሎች ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች እንዲወጡ እንዲሁም በትግራይ ክልል የሚገኙ የአማራ ክልል ኃይሎችም ይውጡ ሲሉ ጠይቀዋል።
ኃላፊዋ ጦርነት መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል በጠቆሙበት በዚህ መግለጫ በትግራይ ያለው የኤርትራ ሠራዊት በአስቸኳይ እና ለጨመረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ መውጣት አለባቸው ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ኃላፊዋ አክለውም "በትግራይ ለሚገኙ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ሁሉም አካላት ግጭት ማቆም አለባቸው። ለዚህ ግጭት ወታደራዊ መፍትሄ አማራጭ አይደለም" ሲሉ አስፍረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ ኤጀንሲ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት የሻከረ ቢሆንም ለትግራይ በሱዳን በኩል ምግብ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑን መግለጹን ኤሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ተዘግቷል የተባለውን የትግራይ ክልል ለመድረስ የሚደረገው ድርድር በጣም አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱን የሱዳን የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ማሪያን ዋርድ ተናግረዋል።
ምክትል ዳይሬክተሯ ከዚህ ቀደም በሱዳን በኩል 50 ሺህ ቶን ስንዴ ወደ ኢትዮጵያ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።












