ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ በተደረገው በረራ አስፈላጊ መድኃኒቶችን መውሰድ መከልከሉን ተመድ አስታወቀ

የተባበሩት መንግሥታት አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia

የመጀመሪያው የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ እርዳታ በረራ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም በተደረገበት ወቅት የሠራተኞቹን አስፈላጊ መድኃኒቶችን መውሰድ መከልከሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አስታወቀ።

ፀረ-ወባን ጨምሮ፣ የህመም ማስታገሻና፣ የልብና የስኳር ህመም የመሳሰሉ መሰረታዊ መድኃኒቶችን ጭምር ይዞ መጓዝ ባለመፈቀዱ ሁለት ሠራተኞቹ ወደ ኋላ መቅረታቸውንም ድርጅቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል።

እነዚህ ሠራተኞች በመድኃኒቶቹ ጥገኛም ስለሆኑ ወደ አካባቢው መሄድ አልቻሉም ተብሏል።

አውሮፕላኑ በአዲስ አበባ ጠበቅ ያለ ፍተሻ የገጠመው ሲሆን የግል መድኃኒቶችን እና ላፕቶፕ እና ዩኤስቢ ድራይቭ ያሉ ከሥራ ጋር የተያያዙ መሳሪያዎችንም እንዳይወስዱ መከልከላቸውን ዩኤን ኦቻ አስታውቋል።

በዚህ በረራ የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞችን እና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 34 የእርዳታ ሠራተኞች ተሳፍረው ነበር።

በዚህም ወቅት ለእያንዳንዱ ተሳፋሪ ወደ ትግራይ እንዲወስዱ የተፈቀደላቸው 225 ዶላር (10 ሺህ ብር) ሲሆን ይህም በትግራይ ቆይታቸው ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን በቂ አይደለም ብሏል ተመድ።

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ባንኮችና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎች በመቋረጣቸው ሁኔታዎችን ፈታኝ አድርጓቸዋል ተብሏል።

የመንግሥት እና አንዳንድ የረድኤት ሠራተኞች ደመወዝ ለወራት ያልተከፈለ ሲሆን የገንዘብ እጥረቱ የሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት ላይ መስተጓጎልን መፍጠሩም ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አጋጠመኝ ያለውን በተመለተ ከመንግሥት በኩል አስካሁን የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

በትግራይ ክልል ከግንቦት 22/2013 ዓ.ም ጀምሮ ምንም አይነት በረራዎች እንዳይኖሩ ቢከለከልም መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ለሚፈልጉ ሁሉ ልዩ ፈቃድ እንደሚሰጥና በረራዎችም ከሰኔ 28/2013 ዓ.ም እንደሚጀመሩ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ በሳምንት ሁለት ጊዜ ቢፈቀድለትም ከመጀመሪያው በረራ በኋላ ከመንግሥት ፈቃድ አልተገኘም ተብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በልዩ ሁኔታ የፈቀደውን የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች ከመከናወናቸው በፊት እንደ የበረራ ቁጥር፣ የአውሮፕላኑን ዓይነት፣ የበረራ ዓላማ፣ የተሳፋሪዎች ዝርዝር እና የጭነት ዓይነት ዝርዝር መረጃዎችን ማቅረብና ማረጋገጫ ማግኘት እንዳለባቸው መገለፁ የሚታወስ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚነሱ እና በሚመጡት አውሮፕላኖች፣ በካርጎዎች፣ በተሳፋሪዎች፣ በሠራተኞች ፍተሻና ምርመራ እንደሚደረግም በመመሪያው ተካቷል።

እንዲሁም ግዙፍ ካርጎዎችንም በተመለከተ መከፈት የሚያስፈልጋቸውም ከሆነ ይህም ተግባራዊ እንደሚሆንና መደበኛና ደረጃውን የጠበቀ ፍተሻ ይደረጋል ተብሏል።

በትግራይ ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ ከ 2.1 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ነዋሪዎች ቤታቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል።

በሱዳን ውስጥ ከ 46 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ዓለም አቀፍ ጥገኝነት እና ጥበቃን የጠየቁ ሲሆን ከ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በአገር ውስጥ ተፈናቅለው በትግራይ እና በአጎራባች የአፋር እና የአማራ ክልሎች በሚገኙ 380 በላይ ጣቢያዎች ላይ ተመዝግበዋል።