የሰብዓዊ እርዳታ በረራ ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of Ethiopia
የሰብዓዊ እርዳታ በረራ ከአዲስ አበባ መቀለ በትናንትናው ዕለት መጀመሩን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለሰብዓዊ እርዳታ በረራ ለማካሄድ በጠየቀው መሰረት ከመንግሥት ፈቃድ አግኝቶ በትናንትናው ዕለት መቀለ ደርሷል ተብሏል።
በትግራይ ክልል ከግንቦት 22/2013 ዓ.ም ጀምሮ ምንም አይነት በረራዎች እንዳይኖሩ ቢከለከልም መንግሥት ከሰሞኑ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ለሚፈልጉ ሁሉ ልዩ ፈቃድ እንደሚሰጥና በረራዎችም ከሰኔ 28/2013 ዓ.ም እንደሚጀመሩ ተገልጿል።
አውሮፕላኑ ስድስት መንገደኞቸን የጫነ ሲሆን በክልሉ ውስጥ በ21 ወረዳዎች ለሚገኙ የረድዔት ሰራተኞችችና ደመወዝ እንዲሁም ስራ ማስኬጃና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል ገንዘብም ጭኗል ተብሏል።
በረራው መንግሥት ባወጣው መመሪያ መሰረት አዲስ አበባ እንዳረፈና ሲመለስም በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል እንደሚያልፍም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በልዩ ሁኔታ የፈቀደውን የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች ከመከናወናቸው በፊት እንደ የበረራ ቁጥር፣ የአውሮፕላኑን ዓይነት፣ የበረራ ዓላማ፣ የተሳፋሪዎች ዝርዝር እና የጭነት ዓይነት ዝርዝር መረጃዎችን ማቅረብና ማረጋገጫ ማግኘት እንዳለባቸው መገለፁ የሚታወስ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሚነሱ እና በሚመጡት አውሮፕላኖች፣ በካርጎዎች፣ በተሳፋሪዎች፣ በሠራተኞች ፍተሻና ምርመራ እንደሚደረግም በመመሪያው ተካቷል።
እንዲሁም ግዙፍ ካርጎዎችንም በተመለከተ መከፈት የሚያስፈልጋቸውም ከሆነ ይህም ተግባራዊ እንደሚሆንና መደበኛና ደረጃውን የጠበቀ ፍተሻ ይደረጋል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የፌደራል መንግሥቱ ሁሉም የመንገደኞች እና የጭነት አውሮፕላን በረራዎች ከሰብዓዊ እርዳታ ተልዕኮዎች ጋር ብቻ የተገናኙ ሰዎችን ወይም ቁሶችን ብቻ እንዲጭኑም ጠይቋል።
በትግራይ ክልል የተነሳው ጦርነት 2 ሚሊዮን ነዋሪውን ከክልሉ ሲያፈናቅል 400 ሺህ ደግሞ ለረሃብ ተጋልጠዋል።
በባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለትግራይ ክልል የላካቸው ሰብዓዊ እርዳታ ጭነት መቀለ መግባታቸው ተገልጿል።
በሁለት ሳምንት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የደረሰው ይህ እርዳታ በ50 የጭነት መኪኖች የተጓጓዘ ነው።
በመቀለ የደረሰው እርዳታ 900 ሜትሪክ ቶን ምግብና አስፈላጊ ቁሳቁስ ቢሆንም በክልሉ ካለው ችግር አንፃር ይህ ቁጥር በእጥፍ ማደግ አለበት ተብሏል።
ከአራት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አስቸኳይ እርዳታ በሚፈልግባት ትግራይ 10 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብና 150 ሺህ ሊትር ነዳጅ በየሳምንቱ መድረስ አለበት በማለት ድርጅቱ አፅንኦት ሰጥቷል።












