ከ200 በላይ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀለ እያቀኑ መሆኑ ተገለጸ

የአለም ምግብ ፕሮግራም መኪኖች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በትግራይና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በነበረው ግጭት ሳብያ ለሳምንታት ወደ ትግራይ የእርዳታ አቅርቦቱ ተስተጓጉሎ የቆየው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎች ከሰመራ ወደ መቀሌ ጉዞ መጀመራቸው ተገለጸ።

ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 20/2013 ዓ.ም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ ያለው የምግብ ክምችት ዛሬ ዓርብ ይጠናቀቃል ማለታቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኮምዩኒኬሽንስ ባለሙያ የሆኑት ክሌር ኔቪል ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእርዳታ አቅርቦት የጫኑ ከ200 በላይ ተሽከርካሪዎች ከአፋር ሰመራ ተነስተው ወደ ትግራይ መቀሌ ጉዞ ጀምረዋል።

ዴቪድ ቢዝሊይ የዓለም የምግብ ፕሮግራም በትግራይ የምግብ ድጋፍ ለማድረግ ለሚፈልጋቸው ሰዎች እርዳታውን ለማቅረብ በቀን 100 ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ መግባት እንዳለባቸው አመልክተው ነበር።

ወደ ትግራይ ክልል በዓለም ምግብ ፕሮግራም አማካይነት 900 ቶን የምግብ እርዳታ የጫኑ 50 ተሽከርካሪዎች ቡድን በመጨረሻ ወደ መቀለ የገቡት ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

ያንንም ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለ350 ሺህ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታን ያቀረበ ሲሆን በተጨማሪም 30 ሺህ ለሚሆኑ እናቶችና ልጆች አልሚ ምግቦችን አከፋፍሏል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው የእርዳታ ምግብ አቅርቦት በዛሬው እለት እንደሚያልቅና ያለውን የተረጂዎች ፍላጎት ለማሟላት በየዕለቱ በ100 የጭነት መኪናዎች የሚጓጓዙ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ያስፈልጋል ብሏል።

በአፋር በኩል ወደ ትግራይ የረድኤት አቅርቦት ለማከናወን ጥረት እያደረገ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተሽከርካሪዎቹ ላይ ጥቃት ማጋጠሙንና ባሉበት እንዲቆሙ መገደዱን አስታውቆ ነበር።

በዛሬው ዕለት ከ200 በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎች የእርዳታ አቅርቦት ይዘው ወደ ትግራይ ማቅናታቸውን የተናገሩት ክሌር ኔቪል ይህ ግን ካለው ፍላጎት አንጻር አናሳ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሁን ወደ መቀለ የተንቀሳቀሰው የእርዳታ አቅርቦት "በባሕር ላይ የውሃ ጠብታ ያህል ነው" ብለዋል።

በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው የተነገረ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ህይወት አድን እርዳታን ይሻሉ።

ከሁሉ የከፋው ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ድጋፍ ካላገኙ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች በረሃብ አደጋ አፋፍ ላይ መሆናቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።

አንዳንድ የእርዳታ ድርጅቶች ባለፉት ስምንት ወራት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሌሎች ኃይሎች ወደ ትግራይ የሚገቡ የእርዳታ አቅርቦቶችን አግደዋል ሲሉ ቢከሱም መንግሥት ግን ይህንን ክስ ሲቃወመው ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከካናዳው አቻቸው ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ያወጀው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት መሆኑን ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ትግራይ የሚደረግ የእርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ እንዳለው "የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የአፋርና የአማራ ክልሎች ትግራይ ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው የሚቀርብን እርዳታ በማገድ የሚያገኙት ጥቅም የለም" ሲል ሰብአዊ እርዳታዎች እንዳያልፉ እንዳልተደረገ ገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት-ዩኤስኤይድ ዋና ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ወደ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል።

ኃላፊዋ በኢትዮጵያ ጉዟቸው "በትግራይ ክልል ረሃብ እንዳይከሰት የተሟላ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግፊት ለማድረግ ነው" ይላል።

ሳማንታ በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይገናኛሉ የተባለ ሲሆን የዩኤስኤይድ እና የዩኤስኤይድ አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ የሚያከናውኑትን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሥራዎችንም ይጎበኛሉ ተብሏል።