ሳማንታ ፓዎር፡ የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ተቋም ኃላፊ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

ሳማንታ ፓዎር

የፎቶው ባለመብት, USAID

የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት-ዩኤስኤይድ ዋና ኃላፊ ሳማንታ ፓዎር ወደ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በመሄድ ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑን ድርጅቱ አስታወቀ።

ሳማንታ ፓዎር ከነገ ቅዳሜ ሐምሌ 24 እስከ ሐምሌ 28 ድረስ ወደ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ጉዞ እንደሚያደርጉ እና የሁለቱን አገራት ባለሥልጣናት ያገኛሉ ተብሏል።

ዩኤስኤይድ የአለቃዋን ጉዞ በማስመልከት ባወጣው መግለጫ ላይ ሳማንታ ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙት "በትግራይ ክልል ረሃብ እንዳይከሰት የተሟላ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግፊት ለማድረግ ነው" ይላል።

ሳማንታ በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይገናኛሉ የተባለ ሲሆን የዩኤስኤይድ እና የዩኤስኤይድ አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ የሚያከናውኑትን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሥራዎችንም ይጎበኛሉ ተብሏል።

ሳማንታ ወደ ሱዳን በሚያቀኑበት ወቅት ከአገሪቱ ባለስልጣናት በተጨማሪ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከትግራይ ክልል ወደ ሱዳን የሸሹ ስደተኞችን ያገኛሉ ተብሏል።

ሳማንታ ፓዎር በትዊተር ገጻቸው እና በተለያዩ መድረኮ ወደ ትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ያልተገደበ ፍቃድ ይስጥ ሲሉ በተደጋጋሚ ድማቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ይህም በተለይ በኢትዮጵያ መንግሥት ደጋፊዎች ዘንድ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ነው በሚል ይተቻሉ።

ሳማንታ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ሱዳን ይጓዛሉ። ሱዳን በሲቪል መንግሥት እየተመራቸው ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋጋር በምታደርገው ጥረት ዩኤስኤይድ ለሱዱን ሊያደርግ ስለሚችለው ድጋፍ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ይመክራሉ።

ሳማንታ ከሱዳን ጠቅላይ ሚንሰትር አብደላ ሃምዶክ፣ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሌፍተናንት ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና ሌሎች የአገሪቱን ባለሥልጣናት ያገኛሉ።

ሳማንታ ፓዎር ማን ናቸው?

ሳማንታ ፓዎር ወደ አሜሪካ መንግሥት መንበረ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ጋዜጠኛ ነበሩ። በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ የተደረጉ ጦርነቶችን በስፋት ዘግበዋል።

በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ዘመን የፕሬዝደንቱ ከፍተኛ አማካሪ እና በተባባሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደርም በመሆን አገልግለዋል።

ሳማንታ በኦባማ አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበራቸው ከሚያስብሉ ምክንያቶች አንዱ፤ የሊቢያውን የቀድሞ መሪ ሙአመር ጋዳፊን ከስልጣን ለማውረድ አሜሪካ የጦር አማራጭን እንድትጠቀም የኦባማ አስተዳደር ላይ ጫና ማሳደራቸው አንዱ ነው።

በፎርብስ የ2016 የዓለማችን ተጽእኖ ፈጣሪ 100 ሴቶች ዝርዝር ውስጥ መካተት ችለዋል።

የ50 ዓመቷ ሴት በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ መንግሥት እርዳታ ድርጅት የሆነውን ዩኤስኤይድን በበላይነት ይመራሉ።

line

በተያያዘ ዜና አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ በኢትዮጵያ ጉብኝነት እያደረጉ ነው።

የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች እና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ማስተባበሪያ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ከትናንት ጀምሮ ለስድስት ቀናት የሚቆይ ጉብኝት ማድረግ ጀምረዋል።

"የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ኃላፊ ሆኜ የመጀመሪያውን ይፋዊ ተልዕኮዬን ለማከናወን ወደ ኢትዮጵያ መሄዴ ለእኔ ወሳኝ ተግባር ነው" ያሉት ኃላፊው ወደ ትግራይ ክልል በመጓዝ በግጭቱ የተጎዱ ሰዎችን እና የሰብአዊ እርዳታ በማቅረብ ላይ የተሰማሩ አካላት የገጠማቸውን ተግዳሮት በስፍራው ተገኝተው ለመመልከት አቅደዋል።