ታካሚዎቹን ያለፈቃዳቸው ያስረገዘው ዶክተር ልጆች 13 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ቀረበላቸው

የሬቤካ ዲክሰን ቤተሰብ

የፎቶው ባለመብት, REBECCA DIXON

የምስሉ መግለጫ, የሬቤካ ዲክሰን ቤተሰብ

መውለድ የማይችሉ ታካሚዎችን ያለፈቃዳቸው ያስረገዘው ዶክተር ልጆችና ታካሚዎች 13 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ካሳ ቀረበላቸው።

ይህ ጉዳይ በካናዳ የግልግል ዳኝነት ታሪክ የመጀመሪያው መዝገብ ነው ተብሏል።

በስምምነቱ መሠረት በደል ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች ፍርድ ቤት በደላቸውን አይቶ በሚወስንላቸው መሠረት ካሳ ይሰጣቸዋል።

ከዚህም አልፎ በርካታ ሕፃናት ትክክለኛ አባታቸውን እንዲለዩ የዘረ መል [ዲኤንኤ] ምርመራ የሚያደርጉበት ገንዘብ ይመደባል ተብሏል።

በዚህ የግልግል ዳኝነት መዝገብ ሥር 226 ሰዎች አሉ።

ዶክተር ባርዊን፤ ኦቶዋና ኦንታሪዮ በሚገኙ ሁለት ክሊኒኮች ውስጥ አገልግሏል።

አንዳንድ ታካሚዎች የወንድ አጋሮቻቸው የዘር ፍሬ ይሰጣችኋል ቢባሉም የማይታወቅ ወንድ አሊያም የዶክተሩ የዘሬ ፍሬ ነበር የተሰጣቸው።

አንዳንዶቹ ክሶች እስከ 1970ዎቹ ድረስ ወደኋላ የሚሄዱ ናቸው።

ዶ/ር ባርዊን አሁን በ80ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በፈረንጆቹ ከ2014 ጀምሮ በሙያው ሠርቶ አያውቅም።

ለተበዳዮቹ የተመደበው የካሳ ገንዘብ መከፈል የሚጀምረው በፍርድ ቤት ዳኛ ተቀባይነት ሲያገኝ ነው።

የ31 ዓመቷ ሬቤካ ዲክሰን አባቷ ዶ/ር ባርዊን እንደሆነ ያወቀችው በቤተሰቧ አባላት ዘንድ የሌለ አንድ በሽታ በያዛት ወቅት ነው።

ቤተሰቦቿ የመውለድ ችግር ያለባቸው ሰዎችን የሚያክመው ዶ/ር ባርዊን ደንበኞች ነበሩ።

ሬቤካና ቤተሰቦቿ ጉዳዩን በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት የወሰኑት በፈረንጆቹ 2016 ነበር።

"በፍፁም ለዚህ ጉዳይ መቋጫ እናገኛለን ብዬ አላስብም" ስትል ለኦቶዋ-ሲቲዝን ጋዜጣ ተናግራለች።

"ይህ ጉዳይ በተቀረው ዘመናችን ሁሉ አብሮን የሚኖር ነገር ነው። ነገር ግን ሰዎች በሕጋዊ መንገድ መፍትሄ ማግኘታቸው ቢያንስ የተወሰነ ሰላም ይሰጣቸዋል" ብላለች።

በስምምነቱ መሠረት 75 ሺህ የካናዳ ዶላር የሚውለው የልጆች ዘር ቅንጣት ተወስዶ ምርመራ እንዲደረግና ትክክለኛ አባታቸው ማን እንደሆነ እንዲለዩ ነው።

ልጆች ትክክለኛ አባታቸውን ከማወቅ አልፎ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ካሏቸው እንዲረዱ ያስችላል ተብሏል።

ዶ/ር ባርዊንና ጠበቃው በስምምነቱ ዙሪያ አስተያየት መስጠት አልፈለጉም። ነገር ግን ስምምነቱ የቀድሞው ዶ/ር ጥፋቱን የማመን ግዴታ እንደሌለበት ያሳያል።

"ሁሉንም ክሶች አልፈፀምኩም ሲል አስተባብሏል፤ አሁንም ማስተባበሉን ይቀጥላል" ሲሉ ጠበቃዎች እንደተናገሩ የችሎት ወሬዎች ጠቁመዋል።

ዶ/ር ባርዊን ከሁለት ዓመት በፊት ነው የሕክምና ፈቃዱን የተነጠቀው።