በዩኬ ትልቁ የትንባሆ አምራች እጸ ፋርስ የወደፊት እቅዴ ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዩናይትድ ኪንግደም ትልቁ የትንባሆ አምራች ከዚህ በኋላ የድሮ ሲጃራዎችን ወደ ጎን በማለት ፊቱን ወደ እጸ ፋርስ (ካናቢስ) ለማዞር እያሰበ እንደሆነ አስታውቋል።
ብሪቲተሽ አሜሪካን ቶባኮ (ቢኤቲ) የተባለው የሲጃራ አምራች ጤና ከላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶቹን ለመቀነስ የጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማፋጠን እንዳሰበም ገልጿል።
ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ ቢኤቲ 'ኦርጋኒግራም' ከተባለው የካናዳ ካናቢስ አምራች ድርሻ ገዝቷል። ይህ ድርጅት ለጤና የሚጠቅሙ ምርቶችን ከካናቢስ በማምረት ዓለማቀፍ ታዋቂነትን ማትረፍ የቻለ ድርጅት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ለአዋቂዎች የሚሆኑ የካናቢስ ምርቶች ላይ ጠለቅ ያለ ምርምር ለማድረግ ስምምነት አድርጓል።
''ወደፊት የሚኖረንን ድርሻ እና አሰራር ከግምት ውስጥ በማስገባት ከኒኮቲን በተጨማሪ ሌሎች ምርቶች ላይ ማተኮር እንዳለብን እናስባለን።
ወደፊት የሚመጣው ትውልድን ከግምት ውስጥ በማስገባት ማለት ነው'' ብለዋል የድርጅቱ ዋና የማርኬቲንግ ኃላፊ ኪንግስሌ ዊተን ከሬድዮ 4 ጋር ባደረጉት ቆይታ።
ኃላፊው አክለውም ከካናቢስ የሚሰሩ ማንኛውም ምርቶች የወደፊቱ እቅዳቸው እንደሆነ አስረግጠዋል። ድርጅቱ በአሁኑ ሰአት የእንግሊዟ ማንቸስተር ውስጥ ከእጸ ፋርስ የተሰራ ምርት ለሙከራ አቅርቧል።
ባሳለፍነው ወር መጨረሻ ላይ የግማሽ ዓመት ሽያጩን ይፋ ያደረገው ቢኤቲ የ8.1 በመቶ ትርፉ እንደጨመረ ያስታወቀ ሲሆን በቁጥር ሲሰላ ደግሞ እስከ 12.18 ቢሊየን ፓውንድ እንደሆነ ተገልጿል።
ድርጅቱ እንደሚለው ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከፍተኛው ገቢ የሚገኘው እንደ 'ቪዩስ' እና 'ግሎ' ከተባሉ በሙቀት እንጂ በእሳት የማይሰሩ (ቬፕ) ምርቶቹ እንደሆነ አስታውቋል።
የቬፕ ደንበኞቼም ከ2.6 ሚሊየን ወደ 16.1 ሚሊየን ከፍ ብለውልኛል ሲል ድርጅቱ አስታውቋል።
ቢኤቲ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 316 ቢሊየን ሲጃራዎችን መሸጥ የቻለ ቢሆንም ከዚህ በኋላ ግን ጤና ላይ የሚያስከትሉት ጉዳት አነስተኛ የሆኑ እና ለመጪው አዲስ ትውልድ የሚሆኑ አዲስ አይነት ምርቶችን ማዘጋጀት ላይ ትኩረቱ እንደሆነ ገልጿል።
ምንም እንኳን ድርጅቱ ለጤና ጠንቅ ወደማያስከትሉ ምርቶች ፊቴን ማዞር እፈልጋለው ቢልም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ተጥለው የነበሩ ክልከላዎች መላላት መጀመራቸውን ተከትሎ በተለይ ባደጉት አገራት የሲጃራ ሽያጩ አንሰራርቷል።
እንደ ቱርክ፣ ብራዚል እና ፓኪስታን ባሉ አገራት ደግሞ የቢኤቲ ምርቶች የሆኑት ደንሂል፣ ኬንት፣ ላኪ ስትራይክ እና ሮዝማንስ የተባሉት ሲጃራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተቸበቸቡ ነው።
ድርጅቱ በአውሮፓውያኑ 2025 የኒኮቲን አማራጭ ምርቶች ላይ ሙሉ ለሙሉ ለማተኮር ማሰቡ የሚደነቅ ቢሆንም ይህንን ስራ ለማስጀመር የሚያስፈልገው ገንዘብ ግን አሁንም የሚመጣው ከሲጃራ ሽያጭ ነው። ስለዚህ በቀላሉ ለውጥ ለማምጣት ሊቸገር እንደሚችል ባለሙያዎች ተንብየዋል።












