እስራኤል በአፍሪካ ህብረት የታዛቢነት ቦታ ማግኘቷ ደቡብ አፍሪካን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
እስራኤል በአፍሪካ ህብረት ታዛቢነት ቦታ እንድታገኝ መወሰኑ የደቡብ አፍሪካን መንግሥት አስቆጥቷል።
ውሳኔውም እንዳስደነገጠው አስታውቋል።
የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ህብረቱ 55 አባል አገራትን ሳያማክር በተናጠል ወስኗል ሲልም ከሶታል።
"ውሳኔው በፍልስጥኤም ጭቁን ህዝቦች ላይ የቦምብ ናዳ በወረደባቸው አመት መሆኑና መሬታቸው በህገወጥ በተወረረበት ወቅት መሆኑ የበለጠ አስደንጋጭ ያደርገዋል" ሲል የአገሪቱ የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር መምሪያ አስታውቋል።
"እስራኤል የፈጸመቻቸው ኢ-ፍትሃዊ እርምጃዎች የአፍሪካ ህብረት የተቋቋመት አላማና መንፈስን የሚጥስ ነው" ሲል አክሏል።
መግለጫው በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ ለአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ለአባል አገራት ገለፃ እንድትሰጥ ትጠይቃለች ብሏል።
ይህ ውሳኔ የደቡብ አፍሪካውን ተቃዋሚ ፓርቲ የኢኮኖሚ ነፃነት ታጋዮች (ኢ.ፌ.ኤፍ )ንም አስቆጥቷል።
የሊቀ መንበሩ ፋኪ መሃመት ውሳኔ አሳፋሪ እና "በፍልስጥኤም ሰብአዊ መብቶች ላይ የተፈጸመ ጥቃት" በማለት ስልጣናቸውን እንዲለቁ ጥሪ አስተላልፏል።
እስራኤል በአፍሪካ አንድነት ድርጅት የታዛቢነት ቦታ የነበራት ቢሆንም ድርጅቱ በአውሮፓውያኑ 2003 በአፍሪካ ህብረት ሲተካ የታዛቢነት ስፍራዋም ቆሞ ነበር።
ለአመታት ያህልም የታዛቢነት ስፍራ ለማግኘት ብትጥርም በአንዳንድ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ተሰናክሎ ነበር።












