ኬንያ እና ዩናይትድ ኪንግደም አልሻባብን ለመዋጋት ስምምነት ላይ ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬንያ እና ዩናይትድ ኪንግደም በሶማሊያ ጂሃዲስት ቡድን አል-ሸባብ እያደረሰ ያለውን ስጋት ለመቀነስ የሚረዳ አዲስ የመከላከያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሁለቱ አገራት ከአልሻባብ ጋር የሚደረገውን ትግል ጨምሮ በመላው ምስራቅ አፍሪካ የጋራ የፀጥታ አደጋዎችን ለመቋቋም ያለመ የአምስት ዓመት የመከላከያ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ተገልጿል።
በመከላከያ ሚኒስትሮች መካከል በለንደን የተካሄደውን ስብሰባ ተከትሎ እንግሊዝ የፀረ ሽብርተኝነት እና ወታደራዊ ድጋፏን ማጠናከር እንደምትፈልግ አስታውቃለች።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኬንያ የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር ሞኒካ ጁማ እና የእንግሊዝ የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋልስ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡሁሩ ኬንያታ ወደ እንግሊዝ የሶስት ቀናት ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው።
ሁለቱም አገራት ለኬንያ ተጨማሪ የተጠናከረ የፀረ-ሽብርተኝነት ድጋፍ በሚቻልበት ሁኔታ እና በባህር ዳርቻዎች እና በሌሎች ቁልፍ አካባቢዎች አክራሪነትን ለመከላከል የእንግሊዝ መርሃግብሮች መስፋፋት ላይ ተወያይተዋል።
ይህም ለኬንያ የመጀመሪያ የሽብርተኝነት ፍርድ ቤት የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ራሱን የቻለ የባህር ላይ ደህንነት መኮንን መሾምን ያካተተ ነው ፡፡
ዩናይትድ ኪንግደም እና ኬንያ በየዓመቱ ከ 1ሺህ በላይ የኬንያ የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮችን የምታሠለጥንበት የመከላከያ ስምምነት አላቸው።
እነዚህም ወታደሮች በረሃማ ወደሆኑ ግጭት አካባባቢዎች ለማሰማራት በሚል ነው ስልጠናውን የሚወስዱት።
በተጨማሪም ስምምነቱ ዩኬ በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የብሪታንያ ወታደራዊ ልምምዶችን በምታከናውንበት ናኒኪ ውስጥ ትልቁን የእንግሊዝ ጦር ማሰልጠኛ ክፍል ኬንያ (BATUK) ተቋም እንድትሠራ ያስችላል።
ኬንያ ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ አልሻባብን ለመዋጋት ሰራዊቷን ወደ ጎረቤት ሶማሊያ ከላከች በኋላ የአልሻባብ ኢላማ ሆናለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኬንያ የብሪታንያ ወታደሮች በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ሲሠለጥኑበት በነበረው ጥበቃ የተሰጠው የተከለለ ስፍራ ላይ ቃጠሎ መነሳቱን ተከትሎ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዷል።
ፍርድ ቤቱም በቅርቡ የእንግሊዝ ጦር በዚህ በከፋው የእሳት ቃጠሎ ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰድበት የሚለው ላይ ብያኔ ይሰጣል።












