ሜሮን ሐደሮ አኮ ኬይን ሽልማትን በማሸነፍ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሆነች

የፎቶው ባለመብት, Meron Hadero
ሜሮን ሐደሮ ስመ ጥሩውን አኮ ኬይን የተባለው የአፍሪካ ስነ ፅሁፍ ሽልማትን በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሁናለች።
" በፍፁም ደስተኛ ነኝ በድንጋጤ ውስጥ ነኝ - በራሱ መታጨቱ ትልቅ ክብር ነበር ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ያሸነፈችበት አጭር ፅሁፍ ጌቱ ስለተባለ አንድ ኢትዮጵያዊ ታዳጊ የሚተርክ ነው።
ታዳጊው በአዲስ አበባ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የውጭ ዕርዳታዎች ያላቸውን የሐይል ጫና ለማለፍ የሚያደርገውን ጥረት የሚያሳይ ነው።
ታሪኩ ዳኞችን ያስደነቃቸው ሲሆን እስከዛሬው ድረስ ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ የተፃፈ ነው ብለዋል።
ሜሮን በዚህ ሽልማት 13 ሺህ ዶላር አሸንፋለች።
ከዶክተር ቤተሰቦች በኢትዮጵያ የተወለደችው ደራሲዋ ሜሮን ያደገችው በአሜሪካ ነው።
የታዋቂዋ ሙዚቀኛ መክሊት ሃደሮ እህት ስትሆን ለስኬቷም እህቷ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረገችላት ሜሮን ትናገራለች።
መሰደድ፣ መፈናቀልና፣ የመፈናቀል አደጋ ተጋላጭነቶች ታሪኮች ሁልጊዜም ለስራዋ ዋና የስሜት ማዕከል እንደሆኑም ትናገራለች።
ሜሮን ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ እንደተናገረችው "በርካቶች በሚፈናቀሉበት ሁኔታ እሱም የተወለደበትንና ያደገበትን ቤትን ሊያጣ ነው። ዋናውም ታሪክ እሱ ነው። ይህንንም ለማስቀረት ይሞክራል" ትላለች።
በርካታው የታሪኩ ክፍል የሚያጠነጥነው ጌቱ በአዲስ አበባ በሚገኘው ሸራተን ሆቴል በተጋበዘበት ወቅት ነው።
"በሱ አይን በምንመለከትበት ወቅት ሸራተን መግባት ማለት ከፍተኛ የባህል መጋጨትን የሚፈጥር የሚያስደነግጥ ነው" ትላለች ሜሮን
"በፅሁፌ ላይ ያንን ንፅፅር፣ ቅራኔ ማሳየት ፈለግኩኝ ፣ ተደራሽነት ምንድን ነው? ሁሉም ክፍት ነው ሲባል እንዴት ይታያል? ዋነኛው ጥያቄም ይሄ ነው። ሁሉም የተከፈቱ በሮች የሚወክሉትስ ምንድን ነው የሚለው ነው" በማለትም ትጠይቃለች
አጫጭር ታሪኮችን መፃፍ ለፀሃፊዋ ለረዥም ዘመናት የቆየ ጥልቅ ፍቅር ነው።
ቀጣዩ ስራዋ የመጀመሪያዋ ልብ ወለድን መፃፍ ነው ነው "በእውነቱ በተለየ መንገድ መሥራት አስደሳች ነው። መጨመር፣ መቀነስና መፈተሽ ነውም" ትላለች።
የ አኮ ኬይን ሽልማት የአፍሪካ ስነ ፅሁፍ ስም የተመዘገበ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሲሆን ዓላማውም ዓመታዊውን የስነፅሁፍ ሽልማትን በመጠቀም የአፍሪካን ፅሁፍ ወደ ሰፊ ተመልካቾች ማድረስ ነው።












