ቻይና የኒውክሌር ኃይሏን በድብቅ እያሳደገች ነው መባሉ አሜሪካን አስግቷታል

የቻይና ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቻይና ኒውክሌር የማከማቸትና የመተኮስ ኃይሏኝ እያጠናከረች ነው ሲሉ የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ተናገሩ።

ምዕራባዊ የሃገሪቱ ክፍል ከምትገኘው ዢንጂያንግ ግዛት የተገኙ የሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩት ቻይና የኒውክሌር ሚሳዔል ማብላያ ጣቢያ እየገነባች ነው።

ይህን መረጃ ይፋ ያደረገው የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ፌዴሬሽን ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት የቻይና ኒውክሌር መሣሪያ ማብላላት እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

ቻይና አዲስ እየገነባች ያለችው ሁለተኛ የኒውክሌር ሚሳዔል ማብላያ ጣብያ ግንባታው ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በምዕራቡ ክፍል እንደተጀመረ ተሰምቷል።

ጣቢያው ቢያንስ ከመሬት በታች የተገነቡና ሚሳዔል ለመተኮስ የሚረዱ 110 ማብላያዎችን ማቀፍ እንደሚችል ተነግሮለታል።

ባለፈው ወር ዋሺንግተን ፖስት የተሰኘው ጋዜጣ 120 ማብላያዎች ዩመን በተሰኘው የጋንሱ ግዛት በረሃማ ሥፍራ ታይተዋል ሲል ፅፎ ነበር።

የሳይንቲስቶቹ ፌዴሬሽን ባለፈው ሰኞ ባወጣው ዘገባ ከዩመን 380 ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚገኘው አዲሱ ጣቢያ ግንባታው በቅርቡ የተጀመረ ነው ብሏል።

ባለፈው ዓመት ፔንታገን ቻይና የኒውክሌር ክምችቷን እጥፍ ለማድረግ እየሠራች ነው ብሎ ነበር።

ይህ የቻይና ሚሳዔል ማብላላት ዜና ብቅ ያለው አሜሪካና ሩስያ ስለ ጦር መሣሪያ ቁጥጥር ለመወያያት ዕቅድ በያዙበት ወቅት ነው።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ምክትል ኃላፊ ዌንዲ ሼርማን እና የሩስያ አቻቸው ሰርጌ ርያብኮቭ የሚያደርጉት ውይይት ቆሞ የነበረውን የኒውክሌር ወሬ ያስቀጥለዋል የሚል ግምት አለ።

ነገር ግን ቻይና እስካሁን በጦር መሣሪያ ቁጥጥር ዙሪያ በሚደረጉ ስምምነቶች ላይ ተሳትፋ አታውቅም።

ስትራቴጂክ ኮማንድ የተሰኘው የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር አካል የሆነው ቢሮ በቻይና ድርጊት ሐሳብ እንደገባው በትዊተር ገፁ ይፋ አድርጓል።

ቻይና ኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ይፋ የሆነው ፕላኔት በተሰኘው የሳተላይ ምስሎችን በሚሸጥ ድርጅት ሳቢያ ነው።

የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር መቀመጫ የሆነው ፔንታጎን ቻይና 200 የኒውክሌር መሣሪያ አሏት፤ እሱን እጥፍ ለማድረግ እየሠራች ነው ማለቱ ይታወሳል።

አሜሪካ 3800 ገደማ የኒውክሌር ሚሳዔሎች እንዳሏት ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።