በማጣሪያ ከተወዳደሩት 5 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 3ቱ ለቀጣይ ዙር አለፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቶኪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድሮች የወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል እና የሴቶች የ800 ሜትር ማጣሪያ ውድድሮች ተካሂደዋል።
በእነዚህ ርቀቶች ከተወዳደሩት አምስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሦስቱ ማጣሪያውን ማለፍ ችለዋል።
የ3ሺህ ሜትር መሰናክል
በዚህ ርቀት አገራቸውን ወክለው የተሳተፉት ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለ እና ታደሰ ታከለ ነበሩ።
የማጣሪያ ውድድሩ በሦስት ቡድን ተከፍሎ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊት 9፡30 እስከ 4፡05 ድረስ ተካሂዷል።
በመጀመሪያው ቡድን የነበረው ለሜቻ ግርማ በ8:09.83 ሰዓት የጃፓን እና የኬንያ አትሌቶችን አስከትሎ 1ኛ በመውጣት ማጣሪያውን አልፏል።
በሁለተኛው ቡድን ውስጥ የተደለደለው ጌትነት ዋለ በ8:12.55 ሰዓት 2ኛ በመውጣት ማጣሪያውን አልፏል።
በሦስተኛ ቡድን ውስጥ የነበረው ታደሰ ታከለ 8ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቁ ማጣሪያውን ሳያልፍ ቀርቷል።
አትሌት ለሜቻ ግርማ እና ጌትነት ዋለ የሚሳተፉበት የወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል የፍጻሜ ውድድር የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 9፡15 ላይ ይካሄዳል።
የሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ
የሴቶች 800 ሜትር ማጣሪያ በስድስት ቡድን ተከፍሎ ከሌሊት 10፡25 እስከ ንጋት 11፡05 ድረስ ተካሂዷል።
በሦስተኛ ቡድን ውስጥ የነበረውችው አትሌት ሀብታም ዓለሙ 2:01.20 በሆነ ሰዓት 2ኛ በመውጣት ማጣሪያውን አልፋለች።
በአራተኛው ቡድን ውስጥ የነበረችው አትሌት ነፃነት ደስታ ግን በ2:01.98 ሰዓት 4ኛ በመውጣቷ ማጣሪያውን ማለፍ ሳትችል ቀርታለች።
ዛሬ የሚካሄዱ ሌሎች ውድድሮች
ዛሬ ዓርብ ከሚካሄዱ ሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል የወንዶች 10 ሺህ ሜትር ፍጻሜ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በዚህ መስክ በሰለሞን ባረጋ፣ በዮሚፍ ቀጄልቻ እና በበሪሁ አረጋዊ የምትወከል ሲሆን፤ ውድድሩም ከቀኑ 8፡30 ላይ እንደሚካሄድ የቶኪዮ ኦሊምፒክ መርሃ ግብር ላይ ተመልክቷል።
ከዚህ በተጫመሪ የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ማጣሪያ 7 ሰዓት ይጀምራል።












