የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ በትግራይ የተመለከቱት ነገር ልባቸውን እንደሰበረው ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, OCHA
አዲሱ የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ በትግራይ የተመለከቱት የጥፋት መጠን ልባቸውን እንደሰበረው ተናገሩ።
አስተባባሪው በትግራይ ክልል ለሁለት ቀናት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን አስከፊ የሰብዓዊ ሁኔታ መመልከታቸውንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
መግለጫው በጦርነቱ ህይወታቸው የተገመሰቃቀለ ዜጎችም ጋር ተወያይተዋል ብሏል።
"በጦርነቱ ምክንያት የነበራቸውን ሁሉ ያጡ ሰዎች አግኝቻለሁ። መኖሪያቸውንና የእርሻ መሬታቸውን እንዲሁም መንደሮቻቸውንና ከተማቸውን ጥለው የተሰደዱ። በሃውዜን ቤታቸው ተቃጥሎ ሰብላቸው የተዘረፈ ቤተሰብ ጎብኝቻለሁ። እስካሁን ድረስ መጠለያም ሆነ ምግብ የሌላቸውም ቤተሰቦችን ማየትም ሆነ የጥፋቱን መጠን መመልከት ልብ ይሰብራል" ብለዋል።
የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊው በትግራይ ጉብኝታቸው ወቅት አሰቃቂ ጥቃት የደረሰባቸውን ግለሰቦችንም ማናገራቸው ተጠቅሷል።
ከዚህም በተጨማሪ የዜጎች መሰረታዊ ልማት የሆኑ እንደ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታልና ውሃ አገልግሎቶች ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዴት እንደወደሙም በአይናቸው ታዝበዋል ተብሏል።
በመቀለ እና ፍሬወይኒ ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊው ለሳምንታት ያህል የተደፈሩትን ጨምሮ አሰቃቂ የሚባሉ ወሲባዊ ጥቃቶች የተፈፀመባቸውንም ሴቶችን ማናገራቸው ተገልጿል።
እነዚህ ሴቶች ሁለንተናዊና ሁሉን አቀፍ አገልግሎቶች ቢሹም "አብዛኛው የጤና ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ አይደለም። ልክ በሃውዜን እንደ ጎበኘሁት ሆስፒታል ያልተነካው ግድግዳው ብቻ ነው ሁሉም የህክምና ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች መተካት አለባቸው" ብለዋል።
የመገናኛ ተደራሽነት፣ ነዳጅና እና የባንክን የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ አስከፊውን ሁኔታ እያባባሰው መሆኑንም መናገራቸው በመግለጫው ተጠቁሟል።
በትግራይ ከ5.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ የህይወት አድን እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 400 ሺህ የሚሆነው ህዝብ በረሃብ አፋፍ ላይ ነው።
ጦርነቱ ወደ አጎራባች ክልሎች አፋርና አማራ በመዛመቱ ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታዎችም አስፈላጊ ናቸው ተብሏል።
ከትግራይ ባለፈ በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት፣ መፈናቀል እና ድርቅ የተጋረጠባቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በመርዳት ላይ የሚገኙ ግብረሰናይ ድርጅቶች ከግጭት ጋር ተያይዞ ከሚፈጠረው መፈናቀል አንፃር አሁን በአማራ እና በአፋር ያለውን ሕዝብ ለመርዳት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።
ጦርነቱ እየሰፋና ዕርዳታ የመድረሱ ችግር እየገፋ ከመሄዱም ጋር ተያይዞ የተደራሽነት ሁኔታው መቀየር እንዳለበትና ጦርነቱም መቆም እንዳለበት ኃላፊው አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊው በስድስት ቀናት በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ከፌደራል መንግሥቱ፣ ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ፣ ከአፍሪካ ሕብረት እና ከሰብአዊ እና ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ጋር ገንቢ ስብሰባዎችን ማካሄዳቸውም ተገልጿል ።
ማርቲን ግሪፊትስ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የሰላም ሚኒስትሯን ጨምሮ ከሌሎች ቁልፍ የመንግሥት በለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ በአገሪቱ ሰብአዊ እርዳታ ሁኔታ እና የረድዔት ድርጅቶች ለኢትዮጵያውያን እርዳታ በሚያቀርቡበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመወያየት ዕድል አግኝተዋል።
ኃላፊው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ለትግራይ ኃይሎች ያደላሉ እንዲሁም ያስታጥቃሉ ማለታቸው "አደገኛ" ነው ብለዋል።
ኃላፊው ማክሰኞ ዕለት የእርዳታ ድርጅቶች ላይ የተቃጣው "መሠረተ ቢስ ወቀሳ" ሊቆም ይገባል ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
"ማስረጃ ካለ በማስረጃ ሊደገፉ ይገባል፤ እውነት ለመናገር ግን ይህ አካሄድ አደገኛ ነው" ብለዋል ኃላፊው።












