በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል ላለው የድንበር ችግር ምን መፍትሔ አለ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ወደ ጎረቤት ክልሎች ተስፋፍቶ ቀጥሏል።
ይህ ጦርነት የተጀመረው የህወሓት አማጺያን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በነበረው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ በሰጡት ትዕዛዝ ነበር።
መንግሥት የሕግ ማስከበር ያለው እርምጃ በመከላከያ ኃይሉ በተወሰደበት ወቅት ለረዥም ዓመት ከትግራይ ክልል ጋር የድንበር ይገባኛል ጥያቄ የነበረው የአማራ ክልል ከፌደራል መንግሥት ጎን ተሰልፏል።
የፌደራል መንግሥቱ ለስምንት ወራት ሲያካሄድ የነበረውን ጦርነት በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ከትግራይ ክልል ወጥቷል።
ይኹን እንጂ ጦርነቱ በትግራይ አማጺያን ወገን የተያዙብን ስፍራዎች እስኪለቀቁ በሚል ቀጥሏል።
የህወሓት አማጺያን ጦርነቱን ላለማቆም ከሚያነሷቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በትግራይ ክልል ስር የነበሩት አንዳንድ አካባቢዎች በአማራ ኃይሎች ተይዘዋል የሚል ነው።
የአገሪቱ ሕግ ምን ይላል?
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት፣ በሁለት ክልሎች መካከል የድንበር ይገባኛል ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ጣልቃ በመግባት መፍትሔ ለመስጠት ስልጣን የተሰጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 48/1 ላይ በሁለት ክልሎች መካከል የድንበር ይገባኛል ግጭት ሲነሳ የፌዴሬሸን ምክር ቤት የሕዝቦች አሠፋፈር ሁኔታን እና ፍላጎትን በማጤን የመፍትሔ ሃሳብ ያስቀምጣል።
የሰላም ግንባታ፣ ዲሞክራሲ እና ሕገመንግሥት አማካሪ የሆኑት እና በኔዘርላንድስ የሚኖሩት አደም ካሴ (ዶ/ር) እንዲህ አይነት ግጭቶችን ለመፍታት ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የሰጠው ለፌደሬሸን ምክር ቤት መሆኑን ይናገራሉ።
"ይኹን እንጂ ይህንን ችግር በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለመፍታት በህወሓት ወገን በፌደሬሸን ምክር ቤት ላይ አመኔታ ስለሌለ፣ አሁን መፍትሔ ያመጣል ብዬ አላስብም" ይላሉ።
ይህ የድንበር ግጭት በሕገ መንግሥት አካሄድ መሠረት ይፈታ ካልን የወቅቱን የፖለቲካ ሁኔታ ካለማገናዘብ የመነጨ ሊሆን ይችላል ሲሉም ተናግረዋል።
ሌላኛው የሕግ ባለሙያ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደርን በመተቸት የሚታወቁት ሔኖክ ገቢሳ (ዶ/ር)፣ ይህንኑ የአደምን ሃሳብ በመደገፍ "ይህንን አለመግባባት በሕግ እና በሕገ መንግሥት መሰረት መፍታት ይቻል የነበረው ወደ ጦርነት ከመገባቱ በፊት ነበር" ይላሉ።
አክለውም ሁለቱ ወገኖች ወደ ጦርነት ገብተው ብዙ ሕይወት ከጠፋ በኋላ ሕግ ሥራ ላይ ይውላል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ እንደሚሆን ሔኖክ (ዶ/ር) ያምናሉ።
ከጅማሮው ይህ አለመግባባት በሕግ አግባብ መፍትሔ እንዲገኝለት ተፈልጎ ቢሆን ኖሮ፣ ወደ ጦርነት ሳይገባ በፊት በውይይት እና ክርክር መፍትሔ ይበጅለት ነበር ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
"ይህ እድል ደግሞ ከዘጠኝ ወራት በፊት አልፏል" የሕግ ባለሙያው ጨምረውም ሲያብራሩ "ችግሩ በፊት ከነበረው የፖለቲካ አመለካከት የመነጨ ነው፤ ቢሆንም ግን ጦርነት ለሁሉም ወገን መፍትሔ ሊሆን አይችልም" ይላሉ።
ጦርነት የፖለቲካ ልዩነትን ወይም የድንበር ግጭትን ይፈታል ብዬ አላምንም የሚሉት ሔኖክ (ዶ/ር) "በጦርነቱ አሸናፊው ቡድን፣ በወቅቱ መሬቱን አስመልሶ ሥርዓቱን ገንብቶ፣ ስልጣን ሊይዝ ይችል ይሆናል። ይኹን እንጂ ተሸናፊው አካል የደረሰበት ጉዳት አመርቅዞ ወደ ፊት ለሌላ ጦርነት ራሱን የሚያዘጋጅ ስለሆነ ጦርነት ዘላቂ መፍትሔ አይሆንም።''

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ከወዴት አለ?
በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚከሰቱ የወሰን ጥያቄና ግጭቶችን በተለየ ሁኔታ እንዲያይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋማቸው ይታወሳል።
በወቅቱ የትግራይ ክልል ምክር ቤት የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅ ውድቅ እንዲሆን የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ አጽድቋል። ምክር ቤቱ የኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁን ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነው ብሎት ነበር።
የፌደራል መንግሥት በበኩሉ የኮሚሽኑ መቋቋም፤ በክልሎች የአስተዳደር ወሰን፣ ራስን በራስ ማስተዳደርና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ የሚታዩ ተደጋጋሚ ችግሮችን በማያዳግም መንገድ ለመፍታት ያስችላል ይላል።
እስካሁን ባለው ሁኔታ ይህ ኮሚሸን ግን ለተቋቋመለት ዓላማ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ እምብዛም አልታየም።
አደም ካሴ (ዶ/ር) "በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተቋቋመው ኮሚሽንም ሆነ የፌደሬሽን ምክር ቤት አሁን የተነሳውን የድንበር ችግር ለመፍታት አሁን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ የሚፈቅድ አይደለም። ያለው ችግር ያንን ሁኔታ ስላለፈ፣ ሁለቱ አካላት መግባባት መፍጠር አለባቸው ብዬ አምናለሁ" ይላሉ።
በአጠቃላይ ሁለቱ ክልሎች የድንበር ግጭታቸውን በኃይል ይፈታል የሚል እምነት የለኝም ሲሉም አክለዋል።
"የድንበር ግጭት በኃይል ይፈታል ብዬ አላምንም፣ የትኛውም አካል አሁን በጦርነት ቢያሸንፍ እንኳ ሌላኛው ወገን አንድ ቀን ጠብቆ በመነሳት ጦርነት ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው" ይላሉ።
ሁለቱ አካላት ምን ይሻላል በማለት በሠላማዊ መንገድ ከተነጋገሩ በኋላ፣ የተስማሙባቸውን ጉዳዮች በመፈራረም እና ወደ ሕግ በመቀየር፣ እንዲፀድቅላቸው ወደ ምክር ቤት ማቅረብ መፍትሔ ይሆናል ሲሉም ይመክራሉ።
"በአሁኑ ጊዜ በሕግ አካሄድ መተማመን ስለሌለ መፍትሔ ይሆናል ብዬ የማስበው ይህንን ነው" ብለዋል።
ሔኖክ (ዶ/ር) በበኩላቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሦስት ዓመት በፊት የተቋቋመው ኮሚሽን የተቋቋመለትን ሥራ እንዳያከናውን ሁለት ጉዳዩች እንቅፋት እንደሆኑበት ይናገራሉ።
"የመጀመሪያው የኮሚሽኑ አባላት የፖለቲካ አመለካከት የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ከሚያስቀምጠው አመለካከት ጋር የሚሄድ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩነት ያላቸው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች አሉ። የኮሚሽኑ አባላት ደግሞ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በዚህ ላይ በሚለው ላይ ችግር ያለባቸው ናቸው" ይላሉ።
ሁለተኛውን ነጥብ ሲጠቅሱም "ኮሚሽኑ የተቋቋመው ሕገ መንግሥትን መሠረት አድርጎ ሳይሆን "በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግል ስልጣን መሰረት መሆኑ ነው። በመሆኑም እነዚህ አባላት ሕገ መንግሥቱ እንደሚለው ለመስራት አይችሉም" በማለት ምክንያታቸውን ያስቀምጣሉ።
አሜሪካ ሜሪላንድ የሚኖሩት እና በወልቃይት እና አካባቢው ላይ ጥናት ማካሄዳቸውን የሚናገሩት አቶ አቻምየለህ ታምሩ ደግሞ አደም ካሴ (ዶ/ር) ሁለቱ አካላት በመፈራረም ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው የሚሉትን ይቃወማሉ።
"በአሁኑ ሰዓት አማራ ክልል እየጠየቀ ያለው መሬት በፊቱኑም ቢሆን፣ በኃይል የተወሰደበት ስለሆነ በኃይል እርምጃ መመለሱ ትክክል ነው" በማለት ያስረዳሉ።
አቶ አቻምየለህ "የኢትዮጵያ ታሪክ መጻፍ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በፍፁም የትግራይ ወሰን የተከዜን ወንዝን ተሻግሮ ይዞታቸው ሆኖ አያውቅም። በደቡብ በኩል ደግሞ የትግራይ ወሰን የአሸንጌ ሐይቅ ነው" ይላሉ።
"ህወሓት ትግል ላይ በነበረበት ወቅት ትግራይን እንደ አገር ለማዋቀር በማሰብ ወደ ሱዳን የሚያሻግረውን መንገድ ፍለጋ፣ ላለፉት 30 ዓመት በጉልበት የያዘው ነው" የሚሉት አቶ አቻምየለህ "አሁንም ቢሆን ጉዳዩ በውይይት መፍትሔ ያገኛል ብዬ አላምንም" ይላሉ።
አደም ካሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የፌደሬሸን ምክር ቤት አወቃቀር ሥርዓት ተመሳሳይ የፖለቲካ አመለካካት ባላቸው ሰዎች መሆኑን እና እንደ ፍርድ ቤት ያሉ የፍትህ ተቋማት ደግሞ ገለልተኛ ባለመሆናቸው ለእንዲህ ዓይነቱ ችግሮች በሕግ አግባብ መፍትሔ ለመስጠት አቅሙም ሆነ ፍላጎት እያሳዩ አልነበሩም ብለዋል።
"አሁን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አዲስ ሥርዓት ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ በክልሎች መካከል ያለው ድንበር ቋንቋን እና ዘርን መሰረትን ያደረገ ነው፣ ወይስ ሌላ መኖር አለበት በሚለው ላይ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት" ብለዋል አደም (ዶ/ር)።
ምክንያታቸውን ሲያብራሩም፣ በፊት በነበረው ሁኔታ ይቀጥል ከተባለ ከበፊቱ ጀምሮ ሲነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ተገቢ መልስ ለመስጠት አዲስ ሥርዓት ስለሚያስፈልግ ነው ይላሉ።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ዛሬም በፊትም በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ስለሆነ ያለው፣ ከዚህ ስር በመውጣት ነጻ በሆነ ሥርዓት መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ነው የሚሉት አደም (ዶ/ር)፣ አሁን ባለው የአገሪቱ ሁኔታ ደግሞ ፌደሬሽን ምክር ቤት ላሉት ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ አይደለም ያለው።
ለዚህ ደግሞ በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል በምክር ቤቱ ውስጥ ተወካይ የሌለው መሆኑን እንደ ምክንያት ያስቀምጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የተካረረ አቋም
የአማራ ክልል በትግራይ ክልል "የሕግ ማስከር ዘመቻው" ከተጀመረ በኋላ በኃይል የተወሰደበትን መሬት በኃይል ማስመለሱን መናገሩ ይታወሳል።
የሕግ ባለሙያው አደም ካሴ (ዶ/ር) የአማራ ክልል ለረዥም ዓመታት የድንበር ጥያቄ ሲያነሳ ቢቆይም እንኳ በጦርነት ለማስመለስ ያቀደው እቅድ እንዳልነበር ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ፣ አሁን ሁለቱ ክልሎች እየተወዛገቡበት የሚገኙት አካባቢዎች፣ ለአማራ ክልል ለብዙ ዓመታት ትልቅ የፖለቲካ ራስ ምታት ሆኖ መቆየቱን ያስታውሳሉ።
ሰኔ 30/2013 ዓ.ም የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አገኘሁ ተሻገር በሰጡት መግለጫ "ወልቃይት ጠገዴን እና ራያን መልሶ ለመያዝ የሚካሄደው እንቅስቃሴ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። የወልቃይት ጥያቄ የአማራ ሕዝብ የ30 ዓመት የማንነት ጥያቄ ነው" በማለት ምን ያህል ጉዳዩ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ስር የሰደደ ጥያቄ እንደሆነ ማንሳታቸው አይዘነጋም።
በሌላ በኩል ደግሞ የህወሓት መሪ ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) "አማራ ክልል በጉልበት የወሰደብንን መሬት ለቅቆ የማይወጣ ከሆነ፣ ተዋግተን እናስመልሳለን" በማለት ሐምሌ 6/2013 በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜም በትግራይ ክልል ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልል ተስፋፍቷል።
አሸባሪ ከተባለ ቡድን ጋር ውይይት መቅረብ. . .
በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የነበረው ግጭት መጠናከሩን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን አሸባሪ በማለት ፈርጇል።
በትግራይ ክልል ለስምንት ወራት ሲካሄድ ከቆየው ጦርነት በኋላ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ወታደሮቹን ከመቀለ አስወጥቷል።
ይሁን እንጂ አብዛኛውን የትግራይ ክልል የተቆጣጠሩት የትግራይ ኃይሎች የፌደራል መንግሥት ያወጀውን የተቁስ አቁም ከመቀበል ይልቅ የራሳቸውን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል።
በመቀጠልም የትግራይ ኃይሎች በአማራ እና በአፋር ድንበሮች አካባቢ ጦርነትን ማካሄድ ቀጥለዋል።
የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊ ድጋፍ መንገድ ለማስከፈት እና ቅድመ ሁኔታቸውን የፌደራል መንግሥቱ እንዲቀበለው ተጽዕኖ ለማሳረፍ ጦርነቱን መቀጠላቸውን የትግራይ ኃይሎችን እየመሩ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ጄነራል ጻድቃን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ከፌደራል መንግሥት ወገን፣ የዲሞክራሲ ግንባታ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብርሃ በጄነራል ጻድቃን የተነሳው ሃሳብ ላይ ለቢቢሲ ምላሻቸውን ሲሰጡ የፌደራል መንግሥቱ በህወሓት የተቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ እንደማይቀበል እና መንግሥታቸው ከቡድኑ ጋር ሳይሆን ትግራይን ከሚወክሉ ሌሎች አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ ፍላጎት እንዳለው ተናግረው ነበር።
ለመሆኑ በሕግ አሸባሪ ከተባለ አካል ጋር ውይይት ማድረግ ይቻላልን የሚለውን ጥያቄ ያቀረብንላቸው አደም (ዶ/ር) "በሕግ አካሄድ አሸባሪ ከተባለ አካል ጋር ለውይይት መቀመጥ የሚመች አይደለም። ነገር ግን ውይይት ማድረግ ከተፈለገ ውሳኔውን ያስተላለፈው ፓርላማ ውሳኔውን ማንሳት ይችላል" ይላሉ።
ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ፣ "ከህወሐት ጋር ሳይሆን ከትግራይ ኃይሎች ጋር በማለት ውይይት መጀመር ይቻላል። ቢሆንም ግን የህወሓትን ኃይሎች ውጪ በማስቀረት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ማሰብ በራሱ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል" በማለት ያሉትን አማራጮች ያስቀምጣሉ።
በህወሓት ውስጥ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች መኖራቸው በራሱ ሌላ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል የሚያነሱት የሕግ ባለሙያው "ፍላጎት ካለ ግን ይህንንም የሕግ ጉዳይ ማለፍ የሚቻልበት መንገድ ይኖራል" ብለዋል።
በመጀመሪያ ደረጃ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ ስምምነት ላይ ከተደረሰ ለውይይት አመቺነት በፓርላማ ውሳኔውን ማንሳት ይቻላል የሚሉት አደም (ዶ/ር)፤ አሁን ችግሩ የአማራ እና የትግራይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክልሎችም የፀጥታ ኃይላቸውን በመላክ የተሳተፉበት በመሆኑ ተኩስ ለማቆምም ሆነ ለሌላ እርምጃ መጀመሪያ ሁሉም አካላት መስማማት አለባቸው ይላሉ።
በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ላለፉት ዘጠኝ ወራት ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በሺዎች ለሚቆጠሩ ሕይወት መጥፋትና ለሚሊዮኖች ደግሞ መፈናቀል መንስኤ መሆኗል።












