በደሴ ከተማ ላይ በተፈጸመ የመድፍ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል ሦስት ቆሰሉ

ደሴ ከተማ

በደቡብ ወሎ ዞን መዲና በደሴ ከተማ ላይ በተተኮሱ የመድፍ አረሮች ምክንያት አንድ ሰው ሲገደል ሦስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የከተማዋ ከንቲባ ለቢቢሲ ተናገሩ።

የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል ለቢቢሲ እንደገለጹት ትናንት ሐሙስ ጥቅምት 18/2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ "የህወሓት ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ በመድፍ በፈጸሙት ጥቃት ነው የሞትና የመቁሰል አደጋ የደረሰው።"

እየተካሄደ ስላለው ጦርነት የተረጋገጠ ማረጃ ማግኘት አዳጋች ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በደሴ ከተማ አቅራቢያ ባሉ ስፍራዎች በመንግሥት ኃይሎችና በህወሓት ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ እየተዘገበ ነው።

ከንቲባው ለቢቢሲ እንደገለጹት መድፎቹ ወደ ደሴ ከተማ የተተኮሱት ከሰዓት በኋላ በግምት 9፡30 ላይ ሲሆን ሦስት የተለያዩ ቦታዎች የጥቃቱ ኢላማ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ቢቢሲ ያናገራቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የከባድ መሳሪያ ፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውንና በሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን እንደሰሙ ገልጸዋል።

አማጺያኑ በአጠቃላይ አምስት የመድፍ አረሮችን በከተማዋ ላይ የተኮሱ ሲሆን፤ ሁለቱ መናፈሻ በሚባለው የከተማዋ አካባቢ፣ ሁለቱ ዳውዶ በሚባለው ስፋራ እንዲሁም ቀሪው አንድ ደግሞ እርሻ ሰብል ከሚባለው ቦታ ላይ ወደቀዋል ሲሉ አቶ አበበ ተናግረዋል።

በተለይ እርሻ ሰብል እና መናፈሻ በተባሉት የከተማዋ ስፍራዎች ላይ ያረፉት አረሮች ሰላማዊ ነዋሪዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ እንደሆነና ዳውዶ በተባለው አካባቢ ላይ የተተኮሰው መድፍ በሰው ላይ ጉዳት ሳያደርስ ሜዳ ላይ መውደቁን ከንቲባው አመልክተዋል።

የመድፍ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ በጦርነቱ ምክንያት ከሰሜን ወሎ ዞን የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉበትና እርዳታ የሚያገኙበት ስፍራ እንደሚገኝበት ከንቲባው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከደሴ ከተማ ውጪ ከሚገኝ ስፍራ በህወሓት ኃይሎች በከተማዋ ላይ ተፈጸመ በተባለው በዚህ የከባድ መሳሪያ ጥቃት የተገደለውና የቆሰሉት ንፁሃን ሰዎች መሆናቸውን አቶ አበበ ገብረ መስቀል ተናግረዋል።

በሰዎች ላይ ሞትና የመቁሰል ጉዳት የደረሰው እርሻ ሰብል እና መናፈሻ በተባሉት ሁለት ስፍራዎች ላይ ሲሆን "በአንደኛው ቦታ ሦስት ንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ከእነዚህም መካከል አንዱ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉን" ከንቲባው ገልጸዋል።

በሌላኛው ስፍራ ላይ በተተኮሰው የመድፍ አረር ደግሞ አንድ ሰው መቁሰሉን ጨምረው አቶ አበበ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በዚህ የመድፍ ጥቃት የሞተው ግለሰብ እና የቆሰሉት ሰዎች የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ወይም ተፈናቅለው ከሚገኙት ሰዎች መካከል እንደሆኑ ለመለየት የከተማዋ ባለሥልጣንት እያጣሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በትግራይ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ወደ ሰሜን ወሎ አካባቢዎች ሲስፋፋ የተፈናቀሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በደሴ ከተማ ያሉ ሲሆን፤ ተፈናቃዮቹ በከተማዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ስፍራዎች ተጠልለው ይገኛሉ።

ባለፉት ቀናት በደሴ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ስፍራዎች በህወሓት አማጺያን እና በአገሪቱ የከመከላከያ ሠራዊት እና አጋሮቹ መካከል ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የደሴ ከተማ ከንቲባ እና የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከቅርብ ቀናት ወዲህ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ድምጽ ሲሰማ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎች፤ ይህም በከተማዋ ነዋሪ ላይ በፈጠረው ስጋት ሳቢያ የተለየ እንቅስቃሴዎች እንዲቀዛቀዙ ማድረጉን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከንቲባው አቶ አበበ ገብረ መስቀልም በተለያዩ የወሎ ግንባሮች ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን አረጋግጠው፤ ነገር ግን የከተማው ነዋሪ መደበኛ ሕይወት መቀጠሉን ተናግረዋል።

ሐሙስ ዕለት ለተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታ ሲሰጥ መዋሉን የተናገሩት ከንቲባው የከተማዋ የተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተለመደ ሥራቸውን ሲያከናውኑ መዋላቸውን አብራርተዋል።

መንግሥት በአሸባሪ ድርጅትነት የፈረጀው የህወሓት ሊቀመንበር ሆኑት ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ረቡዕ እለት ቡድናቸው በሰሜን ወሎ ስለሚያደርገው እንቅስቃሴ በተናገሩበት ጊዜ ተዋጊዎቻቸው "በሕዝብ ላይ የሚፈጽሙት ቂም በቀል የለም" በማለት የደሴና ኮምቦልቻ ነዋሪዎች እንዲረጋጉ ጠይቀው ነበር።

ከንቲባው አቶ አበበ የህወሓት ታጣቂዎች ወደ ደሴም ሆነ ኮምቦልቻ ሊገቡ እንደማይችሉ ጠቅሰው፣ አሁን ከተማዋ ፍፁም ሰላማዊ መሆኗን ተናግረዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አፋርና አማራ ክልል የተስፋፋው ጦርነት ጋብ ብሎ ቆይቶ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ አገርሽቶ አሁን ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የህወሓት ኃይሎች ከሰሜን ወሎ ተሻግረው ወደ ደቡብ ወሎ በመዝለቅ የዞኑ ዋና ከተማ በሆነችው ደሴ እና የኢንዱስትሪ ከተማ በሆነችው ኮምቦልቻ ላይ ትኩረት አድርገዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እንዲሁም ከሌሎች አካባቢ የተወጣጡ ኃይሎች ሁለቱን ከተሞች በመከላከል ከአካባቢው አማጺያኑን ለማስወጣት እየተዋጉ ነው።