ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እየተካሄደ ስላለው ጦርነት ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, HOPR
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ሰሜን ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች ያለው ጦርነት በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ጠየቁ።
መንግሥት አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ጦርነት በምን ያህል ጊዜ አጠናቆ ዜጎች ወደ መደበኛው ኑሯቸው እንደመለሱ ለማድረግ ያለውን ዕቅድ የጠየቁት አራት አባላት ናቸው።
እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን ለምክር ቤቱ አፈጉባኤ ያቀረቡት የአዲሱ ምክር ቤት እንደራሴዎች የሆኑት አራት የኢዜማ ፓርቲ አባላት ሲሆኑ ከጉዳዩ አስቸኳይነት አንጻር ሌሎች አባላትን ለማካተት እንዳልቻሉ ከደብዳቤው ፀሐፊዎች አንዱ ዶ/ር አብረሃም በርታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአገሪቱ ህልውና ላይ አደጋን ጋርጧል ያሉት ጦርነት በዘላቂነት እንዲቋጭ እንዲሁም በጦርነቱ የተጎዱ ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም መንግሥት እያከናወነ ያለውን ተግባርና ዕቅዱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያብራሩ በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል።
የምክር ቤት አባላቱ መንግሥት ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ ጦርነቱ ወደ ሌሎች ክልሎች በመስፋፋቱ "በትግራይ ክልል ከነበረው የዜጎች ሰላም ማጣት በተጨማሪ በአማራና በአፋር ክልል ዜጎች እንዲሞቱ፣ እንዲፈናቀሉና መሠረተ ልማቶች እንዲወድሙ" ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
እንደራሴዎቹ ለምክር ቤቱ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ሕዝቡ መንግሥት"ህወሓት የደቀነውን አደጋ በማያዳግም ሁኔታ ይቀለብሳል" የሚል ዕምነት እንዳለው ገልጾ፣ ነገር ግን እየደረሰ ያለው ጉዳትና ውድመት እየቀነሰ አለመሆኑን በመግለጽ ጦርነቱ ከሰሜን ወሎ ወደ ደቡብ ወሎ መበመስፋፋት አደጋ እያደረሰ ነው ብሏል።
እየተካሄደ ያለው ጦርነት "በአገር ህልውና ላይ የተደቀነ አደጋ" መሆኑን የገለጹት የኢዜማ አባላት፣ ስለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ቀርበው መንግሥታቸው "በምን ያህል ጊዜ ጦርነቱን እንደሚያጠናቅቅ" እና "በግጭቱ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎችን ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ" እያከናወነ ያለውን ተግባር እንዲያብራሩ ጠይቀዋል።
ባለፈው አርብ ጥቀምት12/2014 ዓ.ም ለተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት የገባውን ደብዳቤ ከጻፉት የኢዜማና የምክር ቤቱ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በርታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ደብዳቤው በዋናነት ትኩረት ያደረገው በጦርነቱ እና ጦርነቱ ባስከተለው ጉዳት ላይና በቀጣይ ጉዳዮች ላይ ነው ብለዋል።
አራቱ የኢዜማ አባላት ብቻ ደብዳቤውን ለምክር ቤቱ ቢጽፉም ከሌሎች አባላት ጋር እንደተነጋገሩበትና ጉዳዩ ጊዜ የሚሰጠው ባለመሆኑ ሌሎቹን ሳያካትት ጥያቄው መቅረቡን ያመለከቱት ዶ/ር አብረሃም በጋራ ጉዳዮች ጋር በቀጣይ ከሌሎች እንደራሴዎች ጋር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ባለፈው አርብ ለምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የገባው ደብዳቤን ምላሽ እየተካታተሉ መሆኑን የገለጹት የምክር ቤት አባሉ ምንም እንዳልተባሉና ጉዳዩ "አፈጉባኤው ጋር አለመድረሱን" በመግለጽ በዚህ ሳምንት አንዳች ምላሽ እንገኛለን ብለው እየጠበቁ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እንደራሴዎቹ በደብዳቤያቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ የጠየቁት ጦርነቱ ፍጻሜ ስለሚያገኝበት እና ጉዳት የደረሰባቸውን ነዋሪዎች ስለማቋቋም ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጉዳዮችንም አንስተዋል።
በዚህም በሂደቱ ከኅብረተሰቡና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚጠበቅ ሚና፣ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ስለሚወጡ መረጃዎች ወጥነት፣ ለጦርነቱ ዘላቂ መፍትሔ ስለመስጠት እና እንዲህ አይነቱ ጦርነት በድጋሚ እንዳይከሰት መንግሥት እያደረገ ስላለው ጥንቃቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ዶክተር አብረሃም በርታ ከባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ያቀረቡት ጥያቄ የምክር ቤቱን ደንብ የተከተለ በመሆኑ በዚህ ሳምንት ወይም በሚቀጥለው ሳምንት አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያገኙ ለቢቢሲ አስረድተዋል።












