የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሱዳን የሽግግር መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በወታደሮች ቁጥጥር ስር ውለው በአገሪቱ ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ ጄነራል አል ቡርሐን አስቸኳይ ጊዜ ማወጃቸውን ተከትሎ ነው መግለጫውን ያወጣው።
በሱዳን በተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክና ሚኒስትሮቻቸው በወታደሮች የተያዙ ሲሆን የአገሪቱ የሽግግር ምክር ቤት ተበትኗል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ከዚህ ቀደሙ ከሱዳን ሕዝብ ጎን እንደሚቆም ገልጿል። ይህም የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ለዘመናት ካላቸው ጠንካራ ትስስር የመነጨ ነው ብሏል።
በሱዳን ሲቪልና ወታደራዊ አባላትን ያካተተ የጥምር መንግሥት እንዲመሰረት እንዲሁም ለሽግግር ጊዜ የሚሆን ሕገ መንግሥታዊ ሰነድ በማዘጋጀት የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው መግለጫው አስታውሷል።
በመሆኑም ሁሉም ወገኖች በመረጋጋት እና ሁኔታዎችን በማርገብ የተፈጠረው ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
መግለጫው አክሎም የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን ወደ ዲሞክራሲ የምታደርገውን ሽግግር እንደሚደግፍ እንዲሁም ለሽግግር ጊዜ ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ሰነድ እንደሚያከብር ገልጿል።
ኢትዮጵያ የሱዳን ሕዝብ የሚፈልገውን ሉዓላዊነት እንዲከበር ፍላጎት እንዳላት የገለፀች ሲሆን በሱዳን የውስጥ ጉዳይ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ አለመግባታቸው አስፈላጊ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥታለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሱዳን ሕዝብ የገጠመውን ተግዳሮት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አቅሙ እንዳለው እምነት እንዳለውም ገልጿል።
የሱዳን ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፍላጎት እንዲሟላ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከጎናቸው እንደሚቆሙም መግለጫው አስታውቋል።
በሱዳን በወታደሮችና በሲቪሎች የሚመራ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም እና አገሪቱ እንድትረጋጋ ኢትዮጵያ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የሱዳን ሠራዊት በኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች ተይዘው የነበሩትን የድንበር አካባቢዎች ወሮ ከያዘ በኋላ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል።
በሕዳሴው ግድብ ግንባታ እና ውሃ ሙሌት ዙሪያ በቆየው አለመግባባትም ሁለቱ አገራት ሲወቃቀሱ መቆየታቸው ይታወሳል።
ባለፈው መስከረም ወር በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮ መክሸፉ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ የሽግግር አስተዳደሩን በሚመራው ሉአላዊ ምክር ቤት አባላት መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።
ዛሬ ሰኞ ጠዋት የአገሪቱ ጦር ሠራዊት የሽግግር መንግሥቱን ጠቅላይ ሚኒስትርና ሲቪል አባላትን በቁጥጥር ስር በማድረግ አስተዳደሩን የበተነ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አውጇል።
አገሪቱን ለረጅም ዓመታት በበላይነት የመሩት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ ሠራዊት፣ በሲቪሎች እና ተቃውሞውን በመሩት ቡድኖች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መደረጉ ይታወሳል።












