መፈንቅለ መንግሥት በተሞከረባት ሱዳን ሲቪል መሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, AFP
መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ እየተነገረ ባለበት ጊዜ የሱዳን ሽግግር መንግሥት እና ሌሎች የሲቪል መሪዎች በቁጥጥርስ ስር መዋላቸው ተነገረ።
ማንነታቸው ባልተገለጸ ወታደሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል ከተባሉት መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ እንደሚገኙበት ከካርቱም የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ምን እየተካሄደ እንደሆነ ምንም አይነት አስተያየት ያልሰጠ ሲሆን፣ የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ ደጋፊ ቡድኖች ግን ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ እንዲቃወም ጥሪ አቅርበዋል።
በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ በምትገኘው ሱዳን በሁለት ወር ውስጥ ሁለተኛው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተካሄደ መሆኑ የተነገረው ዛሬ ሰኞ ማለዳ ነው።
በዚህም የታጠቁ ወታደሮች በርካታ የአገሪቱ የሽግግር መንግሥት አባላትን በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸው እና የጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክን መኖሪያ ቤትን በወታደሮች መከበቡ ተዘግቧል።
ባለሥልጣናቱን በቁጥጥር ስር ያዋለው ወታደራዊ አካል ማን እንደሆነ አስካሁን በይፋ የታወቀ ነገር የለም።
በአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የፌስቡክ ገጽ ላይ የወጣ መግለጫ እንዳለው ባለሥልጣናቱን በቁጥጥር ስር የማዋል ድርጊት የተፈጸመው "በጥምር ወታደራዊ ኃይሎች" መሆኑንና የተያዙት ሰዎች ያሉት "በማይታወቅ ስፍራ" መሆኑን አመልክቷል።
ጨምሮም ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ መፈንቅለ መንግሥቱን እንዲደግፉ ግፊት ቢደረግባቸውም መቃወማቸውንና ሕዝቡ በሰላማዊ ተቃውሞ "አብዮቱን እንዲከላከል" ጥሪ አቅርበዋል ብሏል።
ከዋና ከተማዋ ካርቱም አቅራቢያ በምትገኘው ኦምዱርማን ከተማ ውስጥ ያለውን የአገሪቱን የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያ ዋና መሥሪያ ቤትን ወታደሮች ጥሰው እንደገቡ የሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተጨማሪም ወታደራዊ ኃይሎቹ በርካታ ቁጥር ያላቸው የተቋሙን ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አመልከቷል።
በከባድ ሁኔታ የታጠቁ ወታደሮች እና የፀጥታ ኃይሎች በካርቱም ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ የተሰማሩ ሲሆን የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ ገድበዋል።
ኤኤፍፒ እንደዘገበው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተካሄደ መሆኑ ከተሰማ በኋላ የሲቪል አስተዳደሩን የሚደግፉ ሰዎች ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ወደ አደባባይ ለመውጣት መሞከራቸውን ተከትሎ ወደ ዋና ከተማዋ የሚያስገቡ ዋና መንገዶችን ወታደሮች ዘግተዋል።
የሱዳን መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት በዋና ከተማዋ ካርቱም ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል።
ልዩ መልዕክተኛዋን ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ወደ ሱዳን ልካ የነበረችው አሜሪካ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትን በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎች "በጽኑ እንዳሳሰባት" ገልጻለች።
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ መንግሥት መልዕክተኛ ሆኑት ጄፍሪ ፌልትማን በሱዳን ውስጥ የሚካሄድ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት "ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እና አሜሪካን የምትሰጠውን ድጋፍ አደጋ ላይ የሚጥል ነው" ሲሉ ትዊተር ላይ ጽፈዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ከሥልጣን እንዲወርዱ ያደረገውን ሕዝባዊ ተቃውሞ የመራው የሱዳን የሠራተኞች ማኅበር፣ ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ ወታደራዊ መፈንቀለ መንግሥትን እንዲቃወም ጥሪ አቅርቧል።
የሱዳንን የሽግግር መንግሥትን በጋራ በሚመሩት ወታደራዊ እና የሲቪል ባለሥልጣናት መካከል አለመግባባት ከተፈጠረ ወራት ተቆጥረዋል።
ባለፉት ሳምንታት ወታደራዊ መሪዎቹንና የሲቪል አስተዳደሮቹን የሚደግፉ ሰልፎች በአገሪቱ ውስጥ ሲካሄዱ ነበር።
ወታደራዊውን መሪዎች የሚደግፉት ሰልፈኞች ጦር ሠራዊቱ መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ የሲቪል አስተዳደሪዎችን ከሥልጣን እንዲያስወግድ ጥሪ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ባለፈው ሐሙስ ዕለት የሲቪል አስተዳደሩን የሚደግፉ ሱዳናውያን አደባባይ ወጥተው አገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንድተሸጋገር ለሲቪል መሪዎቹ ድጋፋቸውን ገልጸው ነበር።
ዛሬም ሰልፈኞች ሠራዊቱ ሥልጣን ለመያዝ የሚያደርገውን ሙከራ በመቃወም እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመደገፍ ወደ ጎዳናዎች ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ትናንት እሁድ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ጄፍሪ ፌልትማን ከጦር ኃይሉ እና ከሲቪል መሪዎቹ ጋር ተገናኝተው አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር አንዲያሸጋግሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ባለፈው መስከረም ወር በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮ መክሸፉ የሚታወስ፣ ይህንንም ተከትሎ የሽግግር አስተዳደሩን በሚመራው ሉአላዊ ምክር ቤት አባላት መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።
አገሪቱን ለረጅም ዓመታት በበላይነት የመሩት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ ሠራዊት፣ በሲቪሎች እና ተቃውሞውን በመሩት ቡድኖች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መደረጉ ይታወሳል።
በዚህም ሲቪሉን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን አብደላ ሐምዶክ የያዙ ሲሆን ከሠራዊቱ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር በመሆን ሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሐን ከፍተኛውን ቦታ ይዘዋል።
ነገር ግን የሱዳንን የሽግግር አስተዳደር በሚመሩት ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናት መካከል ያለው ግንኙነት የሰከነ ሳይሆን ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የደኅንነት ሁኔታ እየተዳከመ የመጣ ሲሆን፣ ምክንያቱም ወታደራዊ መሪዎቹ ሥልጣን የሚያስረክቡበት ወቅትን ለማስተጓጎል ነው ሲሉ ተቺዎች ይናገራሉ።
በሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው ኃያሉ የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ለሲቪሎች ሥልጣኑን በመጪው ኅዳር እንዲያስተላልፍ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለታል።













