የሱዳንን 'አደገኛ' ፖለቲካዊ ቀውስ ለማርገብ አብደላ ሐምዶክ ኮሚቴ አቋቋሙ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በሱዳን ለተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል "የቀውስ ጊዜ ኮሚቴ" ማቋቋማቸው ተነገረ።
ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሁለት ዓመት በፊት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን የገጠማት "በጣም አደገኛ" ፖለቲካዊ ቀውስ ነው ያሉትን ችግር ለመፍታት ነው ቡድኑን ያዋቀሩት ሲል የአገሪቱ ዜና ወኪል ሱና ዘግቧል።
ትናንት ሰኞ ካርቱም ውስጥ በተካሄደው አስቸኳይ የካቢኔ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ነው የቀውስ ጊዜ ኮሚቴውን ማቋቋማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ያስታወቁት።
ሱዳን ለገጠማት ከባድ ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ ለማፈላለግና የተጀመረውን የሽግግር ሂደት ለማሳካት በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችም መካተታቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የሚደረገውን ጥረት ወደኋላ የመመለስ ስጋትን ፈጥሯል ያሉትን ለሳምንታት የዘለቀ ፖለቲካዊ ውጥረትን ለማርገብ ሁሉም ችግሩን ከሚያባብሱ እርምጃዎች ተቆጥበው ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ሐምዶክ ይህንን ያሉት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጠንካራ ተጽእኖ ባለውን የአገሪቱ ጦር ሠራዊት የተደገፈና የሽግግር አስተዳደሩ እንዲወገድና ጦሩ አገሪቱን እንዲመራ የሚጠይቁ ሰልፍ በፖሊስ መበተኑን ተክትሎ ነው።
ባለፈው ቅዳሜ የጀመረው የተቃዋሚዎቹ ሰልፍ በርካታ የጦር ኃይሉ ደጋፊ የሆኑ ሱዳናውያን የተሳተፉበት ሲሆን፣ በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አካባቢ በመሰባሰብ ጦር ሠራዊቱ ሥልጣን እንዲጨብጥ ጥሪ አድርገው ነበር።
ከኦማር አልበሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ሱዳን በሲቪልና በወታደሮች ጥምረት በተመሰረተ ሉአላዊ ምክር ቤት አማካይነት በሽግግር መንግሥት እየተመራች ትገኛለች።
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የአገሪቱን የሽግግር ሂደት ለማደናቀፍ ሙከራ የሚያደርጉ ያሏቸውን አካላት አስጠንቅቀው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት የአገሪቱን የሽግግር አስተዳደር በሚመራው ሉአላዊ ምክር ቤት ውስጥ ባሉ ወታደራዊና ሲቪል መሪዎች መካከል ያለው አለመግባባት እየተባባሰ ባለበት ጊዜ ነው።
ነገር ግን አገሪቱን በሚመራው ሉአላዊ ምክር ቤት ውስጥ ሱዳን በታቀደው መሰረት ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ለመቀልበስ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ የጎላ ተጽእኖና ተሰሚነት ያላቸው የሠራዊቱ አባላት መኖራቸው ይነገራል።
ባለፈው መስከረም ወር በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ ተሞክሮ ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ የሽግግር አስተዳደሩን በሚመራው ሉአላዊ ምክር ቤት አባላት መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።
አገሪቱን ለረጅም ዓመታት በበላይነት የመሩት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ ሠራዊት፣ በሲቪሎች እና ተቃውሞውን በመሩት ቡድኖች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መደረጉ ይታወሳል።
በዚህም ሲቪሉን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን አብደላ ሐምዶክ የያዙ ሲሆን ከሠራዊቱ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር በመሆን ሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሐን ከፍተኛውን ቦታ ይዘዋል።
ነገር ግን የሱዳንን የሽግግር አስተዳደር በሚመሩት ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናት መካከል ያለው ግንኙነት የሰከነ ሳይሆን ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የደኅንነት ሁኔታ እየተዳከመ የመጣ ሲሆን፣ ምክንያቱም ወታደራዊ መሪዎቹ ሥልጣን የሚያስረክቡበት ወቅትን ለማስተጓጎል ነው ሲሉ ተቺዎች ይናገራሉ።
በሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው ኃያሉ የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ለሲቪሎች ሥልጣኑን በመጪው ኅዳር እንዲያስተላልፍ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለታል።













