የሱዳን ጸረ-መንግሥት ተቃውሞ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ተካሄደ

ሱዳናውያን ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ትናንት እሁድ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ጸረ-መንግሥት ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል።

ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ በተመሳሳይ በርካታ ሱዳናውያን የሽግግር መንግሥቱን በመቃውም ጦሩ መፈንቅለ መንግሥት እንዲያደርግ ጠይቀው ነበር።

ትናንት ቀጥሎ በተካሄደው የተቃውሞ ስለፍም ዜጎች በጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የሽግግር መንግሥት እንዲፈርስ ጠይቀዋል።

ሰልፈኞች የሽግግር መንግሥቱ አገሪቱን ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ውስጥ ከቷታል ይላሉ።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልባሽር በፈረንጆቹ 2019 ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ወታደራዊ እና ሲቪል ቡድኖች ሥልጣን ተጋርተው የሽግግር መንግሥት ማዋቀራቸው ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ባለፈው መስከረም የአልባሽር ደጋፊዎች ካደረጉት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፍ በኋላ በሱዳን ወጥረት አይሏል።

የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ፤ በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ "እጅግ አስቸጋሪና አደገኛ ቀውስ" ሲሉ ገልጸውታል።

ትናንት በተካሄደው የታቀውሞ ሰልፍ ላይ ሰዎች "አንድ ጦር፤ አንድ ሕዝብ" በማለት ለሱዳን ጦር ያላቸውን ድጋፍ በቤተ-መንግሥት ፊት ለፊት አሰምተዋል።

በተመሳሳይ ቅዳሜ ተካሂዶ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የጦር ኃይሉ ደጋፊ ሰልፈኞች "የረሃቡ መንግሥት ይውረድ" የሚል መፈክር በማሰማት የጦር ኃይሎች መሪና የሱዳን የጋራ ወታደራዊ - ሲቪል ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ የሆኑት ጄኔራል አብድል ፋታህ አል-ቡርሐን መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ አገሪቱን እንዲቆጣጠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

አንድ ተቃዋሚ ለኤፍፒኤፍ የዜና ወኪል "እኛ ወታደራዊ መንግሥት እንፈልጋለን። የአሁኑ መንግሥት ፍትሕ እና እኩልነት ሊያመጣልን አልቻለም" ሲል ተናግሯል።

ይህ በእንዲ እንዳለ የሱዳን የሽግግር መንግሥት ደጋፊዎች ትናንት እና ከትናንት በስቲያ ለተካሄዱት የተቃውሞ ሰልፎች ምላሽ ለመስጠት የፊታችን ሐሙስ ለመንግሥት ድጋፍ የሚገልጹበት ሰልፍ ጠርተዋል።

የሱዳን ሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ዓርብ ዕለት በሁለቱ ዓመታት የሽግግር ዘመን የአገሪቱን "አስከፊ እና አደገኛ" ሲሉ የጠሩትን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ይረዳል ያሉትን ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።

"በዚህ ግጭት ውስጥ እኔ ገለልተኛ ወይም አሸማጋይ አይደለሁም። የእኔ ግልፅ እና ጽኑ አቋም ከሲቪል ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጋር ሙሉ በሙሉ መሆን ነው" ብለዋል።