የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር በአገሪቱ የወሲብ ንግድን አስቆማለሁ አሉ

የስፔን ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የስፔን ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ

የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ የወሲብ ንግድን ከመላ አገሪቱ አስወግዳለሁ ሲሉ ትናንት እሁድ ቃል ገቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቫሌንሺያ ውስጥ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር የወሲብ ንግድ "ሴቶችን ባርነት ውስጥ የሚከት ነው" ብለዋል።

ስፔን በአውሮፓውያኑ 1995 ላይ የወሲብ ንግድ በሕግ አያስጠይቅም ስትል አውጃ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት እአአ 2016 ላይ በሰራው አንድ ጥናት መሰረት ስፔን ውስጥ የወሲብ ንግድ ዘርፍ እስከ 4.2 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ካፒታል ያንቀሳቅሳል።

በ2009 በተሰራ ሌላ ጥናት መሰረት ደግሞ ስፔን ውስጥ ከሚገኙ ሦስት ወንዶች አንደኛው ለወሲብ ንግድ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚከፍል ያሳያል።

በዚያው ተመሳሳይ ዓመት በተሰራ አንድ ጥናት ደግሞ ቁጥሩ ከተጠቀሰውም በላይ እንደሚሆን እና 39 በመቶ ሰዎች የወሲብ ንግድ ቋሚ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ያሳያል።

የተባበሩት መንግሥታትም ከታይላንድ እና ፖርቶ ሪኮ በመቀጠል ስፔን በወሲብ ንግድ ከዓለማችን ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጿል።

በአሁኑ ጊዜ ስፔን ውስጥ ሕዝብ በሚሰበሰብበት አካባቢ አይፈጸም እንጂ በወሲብ ንግድ ላይ ምንም አይነት ቁጥጥር አይደረግም። ነገር ግን በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን እና ደንበኞችን የማገናኘት ሥራ የተከለከ ነው።

ስፔን 1995 ላይ የወሲብ ንግድ ከዚህ በኋላ ወንጀል አይደለም ማለቷን ተከትሎ ዘርፉ በእጅጉ ያደገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት እስከ 300 ሺህ የሚደርሱ ሴቶች በዘርፉ ተሰማርተው እንደሚገኙ ይገመታል።

2019 ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ፓርቲ ለምርጫ ባዘጋጀው ማኒፌስቶ ላይ የወሲብ ንግድን እንደሚያስወግድ ገልጾ ነበር። በዚህም በርካታ ሴት ደጋፊዎችን ለማፍራት ታስቦ ነበር።

በወቅቱም ፓርቲው የወሲብ ንግድን "የድህነት መገለጫ እና በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጭካኔ እንዲፈጸም የሚያደርግ ነው" በማለት ገልጾት ነበር።

ነገር ግን ፓርቲው ከተመረጠ ከሁለት ዓመታት በኋላ እስካሁን ምንም አይነት ሕግ አልወጣም ነበር።

የዚህን ፓርቲ አቋም የማይደግፉት በበኩላቸው የወሲብ ንግድ ለበርካታ ሴቶች የገቢ ምንጭ እንደሆነና ሕይወታቸውን ለማስተካከል እንደረዳቸው በመግለጽ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ ይቃወማሉ።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለወሲብ ንግድ እየተባለ ከመኖሪያ ቀያቸው እየታፈኑ የሚወሰዱ ሴቶች ቁጥር የመጨመር ጉዳይ በርካቶችን እያሳሰበ የሚገኝ ነው።

በአውሮፓውያኑ 2017 ላይ የስፔን ፖሊስ እንዳስታወቀው 13 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች በዚሁ ምክንያት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ሲደረጉ መያዙን አስታውቋል።

ከእነዚህ መካከል ደግሞ ቢያንስ 80 በመቶ የሚሆኑት ከፍላጎታቸው ውጪ በሦስተኛ ወገን ተገድደው ነው ወደ ወሲብ ንግድ እንዲገቡ የሚደረጉት።