ሙዚቃ፡ ‘ዓለም አቀፍ የሬጌ አርቲስት ሆኜ መውጣት ነው የምፈልገው’- ድምጻዊ ዮሐና

የፎቶው ባለመብት, Yohana
ድምጻዊ ዮሐና በቅርቦ ሁለተኛ የሙዚቃ ሰንዱቁን (አልበሙን) ለአድማጮች አድርሷል። የመጀመሪያ የሙዚቃ ሥራውን ከሦስት ዓመት በፊት ነበር ለአድማጭ ያቀረበው። ዮሐና በመጀመሪያውም በአዲሱ የሙዚቃ ሥራው ላይ የተለያዩ ሰዎች አብረውት አቀንቅነዋል።
በዚህ 'ዕረፍት' በተሰኘው የሙዚቃ ሥራው ላይ ካስማሠ፣ ፓምፋሎን እነዲሁም ሔዋን ገብረወልድ አብረውት አቀንቅነዋል።
ዲጄ ሚላ ባቀናበረው በዚህ የሙዚቃ ሥራው ላይ በርካታ የሙዚቃ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ዮሐና ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ወቅት ተናግሯል።
ቢቢሲ- ሙዚቃ እንዴት እንደጀመርክ እስቲ ንገረን
ዮሐና- እንደማንኛውም ሙዚቀኛ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው ፍላጎቱ የነበረኝ። ትምህርቴን የተከታተልኩት ሥላሴ ነው፤ አራት ኪሎ። በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤትም አገለግል ነበር። እና ትምህርት ቤት እዘፍናለሁ፤ ሰንበት ትምህርት ቤት ስሄድ ደግሞ እዘምራለሁ። (ሳቅ) ከዚያ እያልኩኝ እያልኩኝ ዩኒቨርስቲ ስገባ፤ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ነበር የደረሰኝ። እና ሙዚቃ 'ፕሮፌሽናሊ' የጀመርኩት መቀሌ ዩኒቨርስቲ እያለሁ ነው።
ቢቢሲ- መቀሌ ዩኒቨርስቲ ያጠናኸው ምን ነበር?
ዮሐና- ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ።
ቢቢሲ- የሙዚቃ ትምህርት ክፍል አላቸው አይደል መቀሌ?
ዮሐና- አላቸው፤ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ሦስተኛ ዓመት ሆኜ፤ ሙዚቃ ትምህርት ክፍል ሄጄ አመለከትኩኝ፤ እና የተወሰኑ ኮርሶች ወሰድኩኝ። እንደውም በጣም ጥሩ ውጤት ነው ያመጣሁት። እና ወደ ትምህርት ክፍሉ ልገባ ስል የእኛ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሁለት ዓመት ስላለፈህ አይቻልም፤ አለቅህም አለኝ። በዚያ ምክንያት ዩኒቨርስቲ ሙዚቃ የማጥና ፍላጎቴ ሳይሳካ ቀረ እንጂ መቀሌ ዲፓርትመንቱ ነበር።
ቢቢሲ- ታዲያ የመማር ፍላጎቱ ከነበረህ ከዚያ ስትወጣ አልቀጠልክበትም?
ዮሐና- ከዚያ ወጥቼማ ተማርኩኝ፤ አፍሪካን ጃዝ (ጃዝ አምባ) ስኩል ተማርኩኝ።
ቢቢሲ- ምን አጠናህ ጃዝ አምባ?
ዮሐና- ሊድ ጊታር
ቢቢሲ- ከዩኒቨርስቲ ወጥተህ በሙዚቃ ነው መቀጠል የምፈልገው ስትል የገሰጸህ ሰው የለም?
ዮሐና- የሚገርምህ ነገር እስካሁን ድረስ ዲግሪዬን ከዩኒቨርስቲ አልወሰድኩም፤ ልመረቅ የስድስት ወር የሥራ ላይ ልምምድ እና የስድስት ወር ፕሮጀክት ሲቀረኝ ወደ ቤት መጥቼ ለእናቴ ፍላጎቴን ተናገርኩ።
ከልጅነቴ ጀምሮ በትምህርቴ የደረጃ ተማሪ ነበርኩ፤ እነርሱ እንዳይከፋቸው በማለት ወለም ዘለም ሳልል ነው የተማርኩት፤ መጨረሻ ላይ ግን አሁን ለራሴ ጊዜ ስጡኝ አልኳቸው፤ ስድስት ወር የስራ ላይ ልምምድ ወጥቼ፣ ስድስት ወር ፕሮጀክት አጠናቅቄ ወደ ሙዚቃው ለመምጣት ተነሳሽነቱ ይኖረኛል ብዬ አላሰብኩም፤ ድንገት ሲደብረኝ ጥዬው ወደ ምህንድስና ሙያዬ የምመለስ ነው የመሰለኝ።
ስለዚህ አንድ ዓመት ስጡኝ አልኳቸው፤ ልሞክር ጊዜ ስጡኝ አልኳቸው፤ በጣም ቅር ቢላቸውም ግን እንደምንም ብዬ አሳመንኳቸው፤ እግዜር ይስጣቸው እነርሱም እሺ አሉኝ። ይሳካለታል ብለው ብዙ ያሰቡ አይመስለኝም፤ (ሳቅ) ያው ይሞክረውና ይመለሳል ብለው መሰለኝ፤ ያም ነው በየባንዱ ያሯሯጠኝ።
ቢቢሲ- ግን ቃል እንደገባኸው በዓመት ውስጥ ለውጥ አሳየሃቸው?
ዮሐና- አዎ በዓመት ውስጥ ክለቦች ውስጥ ሰራሁ፤ በጣም እድለኛ ነበርኩ በዓመት ከስድስት ወሬ ደግሞ አውሮፓ የሙዚቃ ትርዒት ለማቅረብ ሄድኩ፤ አልበም ሳልሰራ፣ ሲንግል [ነጠላ ዜማ] እንኳ ሳይኖረኝ ማለት ነው፤ ክለብ ውስጥ በጣም ብዙ ሙዚቃዎችን እጫወት ነበር፤ ዘፈን በደንብ አጠና ነበር።
እና ስቲል ፐልስ [Steel Pulse] የሚባል የሬጌ ባንድ እና ሮሃን ማርሊ [Rohan Marley] የምሰራበት ክለብ መጥተው አይተውኝ ወደዱኝ፤ ከብዙ ድምጻውያን ጋር አውሮፓ የሙዚቃ ትርዒት ለማቅረብ ከትልልቅ ድምጻውያን ጋር ይዘውኝ ሄዱ። ያኔ ቤተሰቦቼ ይህ ልጅ እውነቱን ነው ማለት ነው ብለው እድል ሰጡኝ። እኔም አላሳፈርኳቸውም ብዬ አስባለሁ። (ሳቅ)
ቢቢሲ- አሁን እናትህ በደረስክበት ደስተኛ ናቸው?
ዮሐና- አዎ፤ በጣም።
ቢቢሲ- ሙዚቃ ላይ የእነማን ተጽዕኖ አለብህ?
ዮሐና- ከእኛ አገር የእነ እዮብ የእነ ጆኒ ራጋ፤ መድረክ ላይ አማርኛ ተጫውቼ የማውቀው የእነርሱን ነው፤ ከዚያ ውጪ የእነ ቦብ ማርሌን የእነ አልፋ፣ ዚጊ ማርሌን ዘፈኖች ነበር የምጫወተው።
ቢቢሲ- አዲሱ አልበምህን ሳደምጥ ሬጌን ዘመናዊ አድርገህ፣ ማለትም ለአሁኑ ዘመን ቅርብ አድርገህ፣ የኤሌክትሮኒክ፣ የፖፕ ስልት ተካቶበት ነው የሰራኻቸው። ለዚህ ምክንያትህ ምን ነበር?
ዮሐና- ቀዳሚው የምሰማቸው ሙዚቃዎች ናቸው፤ ሌላው ነገር ሙዚቃ በራሱ ሳይንስ ነው። በየጊዜው የሚያድግ ነገር ነው። ስለዚህ ሙዚቃ እንዳጠና፣ እንዲሁም የቅርብ ጊዜ ሙዚቃዎችን እንደሚያደምጥ ሰው የእኔ ትውልድ በሙዚቃው ረገድ ማደግ አለበት ብዬ አምናለሁ። የምሰማውን ሙዚቃ ዓይነት መስራት አለብኝ ከሚል ነው የተነሳሁት።
ከዚህ በኋላ ያለኝን የሙዚቃ እውቀት ከአቀናባሪው ጋር በመሆን በተቻለን መጠን በአሁን ሰዓት ዓለም ላይ ሬጌ እየተደመጠ ያለበት ደረጃ ላይ ያሉ ሙዚቃዎችን እንዲመስል ወይንም ቀረብ እንዲል ጥረት አድርገናል።
ቢቢሲ- በዚህ አልበም ውስጥ ልታስተላልፍ የፈለግከው ዋነኛ መልዕክት ምንድን ነው?
ዮሐና- በአልበም ደረጃ አንድ መልዕክት እንዲያስተላልፍ ማድረግ ይከብዳል። በውስጡ የተለያዩ መልዕክቶች የያዙ ሙዘቃዎች አሉ። ግን በአጠቃላይ በአልበም ደረጃ እኔ ዕረፍት መስጠት ነው የፈለግኩት። ለዚያም ነው የአልበሙን መጠሪያ 'ዕረፍት' ያልኩት። አሁን ካለው ነገር ዕረፍት የምናገኝበት። ወደ ዩቲዮብ ቻናሌ ሲመጡ ቢያንስ ለአርባ ደቂቃም ቢሆን እረፍት ያገኛሉ። በዚህ አልበም ዕረፍት መስጠት ነው የፈለግኩት።
ቢቢሲ- ግጥሞቹን የጻፍካቸው አንተ ነህ?
ዮሐና- አዎ ግጥሙንም ዜማውንም የሰራሁት ራሴው ነኝ።
ቢቢሲ- ሌላው በሥራዎችህ ያስተዋልኩት አንድ ቃል ወስዶ የመጫወት እና እርሱን ይዞ ዜማውን የማዜም ነገር ነው፤ ለዚህ መነሻ ምክንያት ነበረህ?
ዮሐና- እኔ መጀመሪያ ግጥም አልጽፍም፤ ለዚያ ነው ቃላት ላይ በነጻነት መጫወት የቻልኩት። ቅድሚያ የምሰራው ዜማውን ነው። ከዚያ ሃሳቡን እጽፈዋለሁ። ለዚያ ነው የቀለለኝ።
. . . በነገራችን ላይ ይህንን ስል ግጥም ላይ በጣም ትኩረት እሰጣለሁ። ነገር ግን እንደተለመደው የግጥም አጻጻፍ የወል፣ የሰንጎ መገን ቤት እያልኩ አልጽፍም፤ ያ ሲሆን ያስርሃል። ለኔ፣ ለምትሰማቸው ግጥሞች በቃላት ለመጫወት ነጻነት የሰጠኝ ዜማው ነው።

የፎቶው ባለመብት, Yohana
ቢቢሲ- ግጥሞችህ ላይ ሴትን ልጅ ማክበር አያለሁ፤ ሰቆቃ ሮሮ ብቻ አይሰማም።
ዮሐና- ለምን መሰለህ እኔ ያደግኩት ከእናቴ ጋር ብቻ ነው። እናቴ ለብቻዋ ነው ያሳደገችኝ። ስለዚህ ግጥሞቼን ስጽፍ ሴት ልጅ በደለችኝ እያሉ ወቀሳ መደርደር ይከብደኛል። ከአስተዳደጌ፣ ካሳለፍኩት ሕይወት የተነሳ ማለት ነው። እናቴን ስላየሁኝ ማለት ነው። ለዚያ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ በመደበኛ ሕይወቴም ላይ እንደዛው ነኝ። መላከፍ ራሱ የሚያናድደኝ ዓይነት ሰው ነኝ። ይህንን ስል ደግሞ 'ፌሚኒስት' ነህ እንዳትለኝ (ሳቅ)
ቢቢሲ- በዚህ አልበም ላይ ሦስት ወጣት ድምጻውያን ከአንተ ጋር ያቀነቅናሉ። ማለቴ ፊቸሪንግ ገብተዋል። ከአዳዲስ ሙዚቀኞች ጋር መስራት ፈልገህ ነው።
ዮሐና- ሁሉም ሙዚቀኞች ጓደኞቼ ናቸው። ከሁሉም ጋር ተባብሬ በፍቅር ነው የምሰራው። ይህ ክለብ መስራት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ያለ ነው። የመጀመሪያ አልበሜ ላይም እንዲሁ ሦስት ድምጻውያን 'ፊቸሪንግ' ገብተዋል። አንዷ እንደውም ትንሽ ልጅ ናት፤ የጓደኛዬ ልጅ ናት። እዚህኛውም ላይ ሦስት ደምጻውያን አሉ። ይህንን እንደ ዓላማ የያዝኩት ነገር ነው።
ቢቢሲ- የመጀመሪያው አልበምህ መቼ ነበር የወጣው?
ዮሐና- ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት፤ አሁን የካቲት ሲመጣ ሦስት ዓመት ይሞላዋል።
ቢቢሲ- ሁለተኛ አልበምህን ቶሎ ነው የወጣኸው።
ዮሐና- እንደውም ቃል ገብቼ የነበረው በየዓመቱ አልበም እለቃለሁ ብዬ ነበር።
ቢቢሲ- ይቻላል ግን በየዓመቱ አልበም ማሳተም?
ዮሐና- ይቻላል፤ በነገራችን ላይ፤ ዓለም ላይ በየስድስት ወርም አልበም ይለቀቃል።
ቢቢሲ- አልበም ከወጣ በኋላ ኮንሰርቶች ላይ መሳተፍ፤ ወደ ባሕር ማዶ በመሄድ ከአድናቂ ጋር መገናኘት ስላለ ብዬ ነው።
ዮሐና- እኔ ምቾት የሚሰማኝ ስቱዲዮ ውስጥ ነው። አሁን ለምሳሌ ዛሬ ከሰዓት ስቱዲዮ ነው የምሆነው፤ ሌሎች ደግሞ ግጥም እና ዜማ የምሰራላቸው ጓደኞቼ አሉ። ስለዚህ ሁሌም ስቱዲዮ ውስጥ ነኝ። ይህ ሕይወቴ ነው። ለዚያ ነው ቀላል ነው የምልህ። እኔ ለኔም ባይሆን በየቀኑ ዘፈን እጽፋለሁ።
ቢቢሲ- የመጀመሪያ አልበምህ ተቀባይነቱ ምን ያህል ነበር?
ዮሐና- በጣም ሃሪፍ ነው። ብዙ ከተሞች ተጉዤ አድናቂዮቼን አግኝቼበታለሁ። ሁለቱንም አልበሞቼን በነጻ በራሴ ዩቲዩብ ቻናል ላይ ስለለቀቅኩኝ፤ ከሽያጭ ያገኘሁት ነገር የለም። ነገር ግን በቱር፣ በኮንሰርት በጣም ብዙ ፍቅር ከአድናቂዮቼ አግኝቼበታለሁ።
ቢቢሲ- ሦስተኛ አልበምህን ከዓመት በኋላ እንጠብቅ ወይስ ከሦስት ዓመት በኋላ?
ዮሐና- ሦስት ዓመት አይፈጅብኝም፤ ነገር ግን አሁን እኔ ኢንተርናሽናል [ዓለም አቀፍ] አልበም የመስራት ፕሮግራም ላይ ነኝ። ከዚህ በፊት የጀመርኳቸው ሙዚቃዎች አሉ፤ ጃማይካ ከዚህ በፊት 'ቡክ' አድርገውን በኮሮና ምክንያት የቀረ ኮንሰርት አለ እና እዚያ ስሄድ እሰራቸዋለሁ ብዬ የያዝኳቸው ሥራዎች አሉ። አሁን ደግሞ እንደ አልፋ፣ እንደ ላኪ ዱቤ፣ ከኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሬጌ አርቲስት ሆኜ የመውጣት ፍላጎት አለኝ። ሦስተኛ አልበሜ እንደዚያ የሚሆን ይመስለኛል።
ቢቢሲ- ከምትሰራበት ስቱዲዮ ጋር ግንኙነቶችን ጀምረሃል?
ዮሐና- አዎ፤ እንደውም ሥራዎቼን ለመቅረጽም ፕሮግራም ይዤ ነበር። እንዳልኩህ በኮሮና ምክንያት ተሰርዞ ነው እንጂ ኮንሰርት ነበረኝ፤ ጃማይካ። እኔን ቴዲ አፍሮን ናቲ ማንን ጨምሮ ማለት ነው።
ቢቢሲ- ዕረፍት የተሰኘው የአሁኑ አልበምህ ድንገት ነው የተለቀቀው፤ አድናቂዎችህ ምላሻቸው ምን ይመስላል።
ዮሐና- ከጠበቅነው በላይ ነው፤ አልበሙ ይወጣል ብለን ምንም ዓይነት ማስታወቂያ አልሰራንም፤ ከዚህ በፊት 'በየዓመቱ እለቃለሁ ብለህ ምን ሆነክ ነው' የሚሉ ጥያቄዎች ይቀርቡልኝ ስለነበር ድንገት ነው በዩቲዩቤ ላይ የለቀቅኩት። አልበሜን ስጨርስ የሚወጣበት ጊዜ ብዬ ለማስተዋወቅ አልፈለግኩትም። ደግሞም 'ሰርፕራይዝ አልበም' ይሰራል ወይ የሚለውን ለመፈተን ፈልገን ነበር። ጓደኞቼም አያውቁም ነበር። አሁንም ጥሩ እየተደመጠ ነው።
ቢቢሲ- ሙዚቀኞችስ ሥራህን ሰምተው ምን አስተያየት ሰጡህ?
ዮሐና- እንደውም ከአድማጮች በፊት አስተያየት የሰበሰብኩት ከሙዚቀኞች ነው። አልበሜ ከመውጣቱ በፊት በርካታ ሙዚቀኞችን ስቱዲዮ ጠርቼ አሰምቼያቸው ነበር። መቼ እንደሚወጣ ሳልነግራቸው እንደሚሰሙት አድርጌያለሁ፤ በጣም ብዙዎቹ የለፋንባቸውን ነገሮች ወድደዋቸዋል።
ቢቢሲ- እንደሙዚቀኛ አሻራህ ሆኖ እንዲያልፍ የምትፈልገው ምንድን ነው? አድናቂዎችህ እንዲያስታውሱህ የምትፈልገው በምንድን ነው?
ዮሐና- እኔ በጣም በታታሪ ሠራተኝነት ቢያስታውሱኝ ደስ ይለኛል፤ ሙዚቃን 'ለሙድ' ሳይሆን ዮሐና ታታሪ ሙዚቀኛ ነበር ብለው ቢያስታውሱኝ ደስ ይለኛል። መጀመሪያ ሙዚቃ ስጀምር ሙያው ውስጥ ምንም ማውቀው ሰው አልነበረም፤ እንደመጣሁ ናይት ክለብ [ምሽት ክበብ] ዞሬ መዝፈን እችላለሁ፣ ሞክሩኝ ብዬ፣ ሁሉንም ባንዶች አናግሬያለሁ። ወደ ሃያ ምናምን ባንድ ሰርቼያለሁ እስካሁን ድረስ።
ቢቢሲ- ስለዚህ ሙዚቀኛ ለመሆን ለሚፈልጉ ወጣቶች የምትመክራቸው ትጉ ሠራተኛ ሁኑ ነው?
ዮሐና- እዚህ ለመድረስ ምንም አቋራጭ መንገድ የለውም፤ እከሌ ጓደኛዬ ነው፤ ብለው ወደ ባንድ የመጡ እዚያው ቀርተዋል፤ መንገዱ ቀጥ ያለ ነው፤ ምንም ዓይነት አቋራጭ መንገድ የለውም፤ መዝፈን የሚፈልግ ተሰጥኦ አለኝ የሚል ሰው ቀጥ ያለውን መንገድ ቢጠቀም የፈለገበት መድረስ ይችላል። በየሙዚቃ ባንዶች በመሄድ መዝፈን እንደሚችል በመንገር እንዲሞክሩት መጠየቅ ይቻላል።
ሁሉም ባንዶች ቆንጆ ዘፋኝ ይፈልጋለሁ፤ ሁሌም አዳዲስ ሰው ሲመጣ ይሞክራሉ። ሁሌም ይህንን ያደርጋሉ፤ ባንዱ ደግሞ ድክመት ካለ ያስተካክላል፤ ሰዎች የማያውቁት ባንዶች ጋር ሁሌም አዳዲስ ሰው መሞከር እንዳለ ነው። ሙዚቃ በትውውቅ በዘመድ የሚሆን አይደለም፤ ስለዚህ ሙዚቃ ምንም ዓይነት አቋራች መንገድ የለውም። ቀጥ ያለ ነው መንገዱ፤ እርሱን መንገድ ተጓዙት ነው የምለው። ይደረሳል።














