ካሥማሰ፡ "ቅር የሚያሰኙ ጉዳዮች ስለነበሩ ክብር ለማስመለስ ነው የሠራሁት"

ካሥማሰ በማለዳ የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ከተሳተፉ ሰዎች ጋር

የፎቶው ባለመብት, Maranata tegegne

ካሥማሰ የመድረክ ስሙ ነው። እናት አባቱ ያወጡለት፣ መዝገብ የያዘው ስሙ ደግሙ ፍቅሩ ሰማ ይሰኛል። አዲስ 'ግማሽ አልበም' ለሙዚቃ አድማጮች አቅርቧል። ይህ ግማሽ የሙዚቃ ሰንዱቅ፣ ወይንም አልበም፣ ሰባት ሥራዎችን ይዟል። ካሥማሰ ሥራውን ያቀረበው በሂፕ ሆፕ የሙዚቃ ስልት ሲሆን በርከት ያሉት ሥራዎቹን ከቀደሙ ሥመ ጥር ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ስራ ጋር አዋህዶ ሰርቷቸዋል።

ድምጻዊ ካሥማሰ እነዚህ ስራዎቹን በአንድ ያሰናዳበትን ሰንዱቅ፣ ማለዳ ብሎ የጠራው ሲሆን በነጻ ለአድማጮች እንዲደርስ መደረጉን ይናገራል። ማለዳ፣ ቀና ልብ፣ አንደኛ፣ ውበት፣ አመለወርቅ፣ ነገን ለትዝታ፣ ትናንቷን የተሰኙ ስራዎችን የያዘው ይህ አልበም ስለ አገር፣ ስለ አዲስ አበባ እንዲሁም ሌሎች ግዘፍ ሃሳቦችን አንስቶባቸዋል። ካሥማሰ በአገርኛ አንደበት ስላቀነቀናቸው ስራዎች ከቢቢሲ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ!

ቢቢሲ- ውልደትህና እድገትህ የት ነው?

ካሥማሰ- የተወለድኩት አዲስ አበባ ውስጥ ነው። መገናኛ አካባቢ ነው ተወልጄ ያደግኩት። ከዚያም ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት። ከዚያም ወደ ንግድ ሥራ ኮሌጅ፣ ኮሜርስ ገባሁ። ማርኬቲንግ ነው የተማርኩት። ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ጊዜዬን የሰጠሁት ለሙዚቃ ነው። ከኔ ጋር ሙዚቃውን ከሰራው፣ ካቀናበረው ይኩኖአምላክ ጋር አብረን ጥሩ ጊዜ አሳለፍን። ያው አብረውኝ የሚሰሩ ጓደኞችም ነበሩኝ በሰዓቱ። ውበት ላይ የተሳተፈ ልጅ አለ፤ ሰምተኸው ከሆነ። ለሶስት ነው የዘፈንነው ውበትን። ይኩኖ አምላክም ተሳትፎበታል፣ ሙዚቃውን ያቀናበረው ልጅ።

ቢቢሲ- ተወልጄ ያደግኩት አዲስ አበባ ነው ብትለኝም ሥራዎችህ ላይ ግን ቤተ ክህነት ውስጥ ያደገ ሰው ድምጽ ይሰማል። ይህንን ያደረግከው ሆን ብለህ ነው?

ካሥማሰ - የበፊት የሙዚቃ ሥራዎችን፤ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች የሰሯቸውን ሙዚቃዎችን ነው የማዳምጠው። ከፕሮዲውሰሩም ጋር አብረን ስንሆን እንደዚህ አይነት የድሮ ሙዚቃዎችን ነው የምንሰማው። ከዚያ ውጪ ደግሞ አዲስ አበባ ስናድግ ከተለያየ ክፍለ ሃገር ብዙ ሰዎች ይመጣሉ እና የሁሉንም አንደበት መጋራት ችለናል ብዬ አስባለሁ። ከዚያም ደግሞ ቤተሰቦቼ በሚያወሩት በእነዚህ ሁሉ የተቃኘ ነው ብዬ የማስበው።

ቢቢሲ- ስለዚህ ሆን ብለህ ሳይሆን ያደመጥካቸው ሙዚቃዎች ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል ማለት ነው?

ካሥማሰ- እንደዚያም ማለት እንችላለን። ሆን ብዬ ላደርገውም አስቤ አውቃለሁ። ሁሉም ሥራ ላይ ወጥ እንዲሆን ያደረግኩበት ምክንያት ወደ ነበረው ማንነት ለመመለስ ስለሆነ፤ ጥረቱ የኛንም አንደበት የእነርሱንም አንደበት በአንድ ላይ ብሌንድ በማድረግ፣ በማዋሃድ ነው የመጣሁት።

ቢቢሲ- በአገራችን የሂፕ ሆፕ ሙዚቃ ባለመድነው መልኩ በግጥም ፍሰትም በመልዕክትም ደረጃ ጠንከር ያሉ ግጥሞች ስራዎችህ ውስጥ ይሰማል። ማን ነው የጻፋቸው?

ካሥማሰ- ግጥሞቹን እኔው ነኝ የጻፍኳቸው ዜማዎቹን ጭምር። ሥራውን ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት፣ ኮሜርስ ትምህርት ቤት እያለሁ ነው የጀመርኩት። የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ነው ወደዚህ ዓይነት ነገር ማዘንበል የጀመርኩት። ሃሳቦቹም የብዙ ዓመት ሃሳቦች ናቸው። በአንድ ላይ ጠርቀምቀም አድርጌ፣ ስለ አስተዳደጌም የነበረውን ለራሴ እንደ ቴራፒ ነበር የምሰራው።

ከትምህርት ቤት ከወጣሁ በኋላ ግን ያው ሃሳቡ መተላለፍ አለበት፣ በእኛ በወጣቶች ሁኔታ ቅር የሚያሰኙ ጉዳዮች ስለነበሩ ክብር ለማስመለስ ነው የሰራሁት። እና ከእኛ ከወጣቶች የማይጠበቅ ሊመስል ይችላል ግን እንደምንችል ለማሳየት ነው። አንድ ሰው ይህንን ማድረግ ከቻለ ሌሎችስ ምን ይላሉ እንዲባል ነው።

ካሥማሰ በማለዳ የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ከተሳተፈ ድምጻዊ ጋር

የፎቶው ባለመብት, yonas Tadesse

ቢቢሲ- ሥራዎቹን የሰራሃቸው ለራሴ እንደ ቴራፒ ነው ብለሀኛል፤ ከየትኛው ነገር ውስጥ ለመውጣት ነው እንደቴራፒ የተጠቀምክበት?

ካሥማሰ- ቴራፒ ልል የቻልኩበት ምክንያት በልጅነቴ የሥዕል ፍላጎት ነበረኝ። በዚያን ጊዜ ግድግዳ ላይ የሚሳሉ ሥዕሎች ይስቡኝ ነበር። እናም ብዙ ጊዜዬን የማጠፋው ቃላቶችን በመሳል ነበር። ስለዚህ እነዚያን ስዕሎች አንድ ቃል ያለውን ትልቅ ሃሳብ በማየት፣ የፊደሎቹን ቅርጽ ሁኔታ በመገንዘብ፣ እያንዳንዶቹን ቃላት በምስልበት ጊዜ አንዱ ቃል ከሚገልፀው በላይ ሃሳብ አሉት። የእኛ አገር ቃላት ሲጠብቁ ሲላሉ፣ ስትበትናቸውም የተለያዩ ሃሳቦች ይይዛሉ። አንዱ ቃል ብቻ ከአንድ በላይ ሃሳብ የመጣ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እነርሱን በማሰብ ለማጠናከር ሲባል፣ የምስላቸውንም ስዕሎች በደንብ ለመረዳት ስል ሃሳቦችን በመጨመር ቀስ እያልኩ ወደ ግጥሙ ገባሁኝ። ከሥራዬ ጋር ከአርቱ ጋር በአግባቡ ለመቀራረብ ስል ነው ይህንን የደረግኩት። ቴራፒም ያልኩት ለዚያ ነው።

ቢቢሲ- ክብርን ማስመለስ የሚል ነገር አንስተሃል። ከማን ነው ክብርን የምታስመልሰው?

ካሥማሰ- ክብር ማስመለስ ስል ደግሞ ሁልጊዜም ስለ ኢትዮጵያኖች ሲነገር፣ ሲዘከር፣ በድሮ በድሮ ነው። ስለ ድሮው እየተነሳ ነው ሃሳብ የሚሰጠው። ስለ ድሮው እየተነሳ ነው ይህች አገር ክብር የሚሰጣት። እኛስ የለንላትም እንዴ? እኛ አለን አይደል እንዴ? ሲባል ነው። ስለ ስምንተኛው ሺህ እና ስለ ወጣቶችብዙ ይባላል። ተስፋም ወኔም ለመቀስቀስ ብዬ ያደረኩት ነገር ነው። ወጣት ስለሆንኩኝ።

ቢቢሲ -በቅንብር ውስጥ እነማን ተሳተፉ?

ካሥማሰ- ሙዚቃውን ያቀናበረው ይኩኖአምላክ የሚባል ጓደኛዬ ነው። ሚክስና ማስተር ያደረገው ደግሞ ኬኒ አለን ነው። በርካታ ስራዎች ነበሩን፣ ግን ሃሳቡ ራሳችንን እንዴት እናስተዋውቅ በሚል ስለ ነበር በዚህ ዓመት ነው እንቅስቃሴውን የጀመርነው። ከመስከረም ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ እስኪለቀቅ ድረስ ይህን ያህል ጊዜ ፈጅቷል።

ቢቢሲ -ቅድም ግጥሙን ስትጽፍ ዜማውን ስታደራጅ አምስት ዓመት ፈጅቷል አልከኝ።

ካሥማሰ- አይ እንደዚያ ማለቴ ሳይሆን ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ሥራው ውስጥ ስለነበርኩኝ ካሉት ለመምረጥ ነው ይኸኛው ጊዜ የፈጀው። ራስን ለማስተዋወቅ የትኛው ስራ ይቅደም በሚል።

ቢቢሲ- ሰባት ሥራዎችን በአንድ ጊዜ ለአድማጮች አድርሰሃል፤ በነጻ

ካሥማሰ- አዎ

ቢቢሲ- ለምን በነጻ መሥጠት ፈለግህ?

ካሥማሰ- የሙዚቃ ስልቱ አዲስ ስለሆነ፣ እኛም በቶሎ አድማጮች ሃሳቡን እንዲይዙት ስለፈለግን፣ እንዲሁ ለማስተዋወቅ እንዲቻል፣ የተለያየ ሃሳብ ገልፀን ለእያንዳንዱ ሃሳብ ያለንን ምልከታ እንዲያዩት ስለፈለግን ነው። አንድ ሃሳብ ብቻ እንዳንሰጣቸው፤ ስለተለያዩ ሃሳቦች ጠቅለል አድርገን ማለዳ ነው፣ ጅማሬ ነው፣ በዚህ መልኩ ነው የጀመርነው ለማለት ነው።

ቢቢሲ- ለዚያ ነው የሥብስቡን መጠሪያ ማለዳ ማለት የወሰንከው?

ካሥማሰ- ትክክል፤ እንዲሁም እንዳልኩህ ክብር ከማስመለስ ጋር፤ ማነው ባለእዳ አንደማለት ነው በሌላ አነጋገር። ማን ነው ለእዳ፣ ማለዳ፣ እዳው ለማን ነው ለማለት ነው።

ቢቢሲ- ስለዚህ የክብር ማስመለሱ ጥያቄም እዚህ ተመልሶ ይመጣል?

ካሥማሰ- አዎ

ቢቢሲ- ባለ እዳ ነን ብለህ ታስባለህ? እናንተ ወጣቶች?

ካሥማሰ- አዎ በደንብ አስባለሁ።

ቢቢሲ- ማን ነው ማንን ባለዕዳ ያደረገው?

ካሥማሰ- የድሮዎቹ ኢትዮጵያውያንን እንቀናባቸዋለን። እናደንቃቸዋለን። ሁሌም የተለየ ክብር ነው ያለን ለእነርሱ። ራሳችንን ከእነዚህ ከቀደምት ኢትዮጵያውያን ጋር ስናነጻጽር አንደራረስም ብለን ነው የምናስበው። እነርሱ ብቻ ናቸው ኢትዮጵያዊ የሚመስሉት። እኛ ከብዙ ከብዙ የተዳቀልን ነው የሚመስለው። እርሱ ነው አንዱ ሃሳብ።

ቢቢሲ- ስለዚህ እኛም ኢትዮጵያዊ ነን ነው?

ካሥማሰ- በትክክል ለማለት ነው። እንደውም አዲሶቹ ነን ለማለት ነው።

ካሥማሰ

የፎቶው ባለመብት, yonas tadesse

ቢቢሲ- ሙሉ ስምህ ፍቅሩ ሰማ መሆኑን ሰምቻለሁ አንድ ቪዲዮህ ላይ። ካሥማሰ የሚለውን የመድረክ ስም የመረጥክበትን ምክንያት ምንድን ነው?

ካሥማሰ- ካሥማሰ የተመረጠው ሁሉም ሰው የመድረክ ስም ቢኖረው ይሻላል፣ በመድረክ ስሙ ቢታወቅና ስራውንና የመደበኛ ሕይወቱን ለመለየት ያስችላል ብዬ ስላሰብኩነው። የመድረክ ስሜ ደግሞ ካሥፈለገ ነው፣ አዲስ ነገር ስለሆነ ካስፈለገ ይህንን አቅርበንላችኋል። የኛን ምልከታ የኛን አስተያየት ለማለት ነው። ካሥማሰ ማለት ካስፈለገ ማለት ነው።

ቢቢሲ- ማለዳ የሙዚቃ ቪዲዮው እንደ ለመድናቸው የሙዚቃ ቪዲዮዎች ዓይነት አይደለም። የዚህ የሙዚቃ ቪዲዮ ሃሳብ አሁን በቀረበበት መልኩ እንዲደራጅ ያደረገው ማን ነው?

ካሥማሰ፡ የሙዚቃ ቪዲዮውን ዳይሬክት ያደረገው ማራናታ ነው። አብረን ነው የምንሰራው። ሁለቱንም ሥራዎቼን የሰራቸው እርሱ ነው። ወደፊትም ከእርሱ ጋር አብሬ ነው የምሰራው ብዬ አስባለሁ። ከማራናታ ጋር ተመካክረን ነው ቀለል ብሎ ህዝብ ጋር እንዲደርስ፣ ጫና ሳይፈጥር ያለንበትን ሁኔታ ለማስረዳት ስለሆነ፣ ቀለል ብሎ እንዲቀርብ፣ ለዓይን እንዳይከብድ ብለን ስላሰብን ነው።

ቢቢሲ- እንዲህ ዓይነት በርከት የሙዚቃ ቪዲዮዎች በብዛት የሉንም፤ ግርግር ያልበዛባቸው

ካሥማሰ- ይኖሩናል ግን

ቢቢሲ፤ ባንተ በኩል ነው ወይስ በሌሎችም ማለትህ ነው?

ካሥማሰ - እንግዲህ እየተመሳሰልን እንሄዳለን ብዬ ነው የማስበው። አዲስ ሃሳብ ሲመጣ ሁሉም ይጋራዋል ብዬ ነው የማስበው። ሃሳቦችን እየተጋራን ስለሆነ የምንሄደው እነርሱም አቋማችንን ይጋራሉ። እኛም ወይ የእነርሱንም አቋም እንጋራ ይሆናል።

ቢቢሲ- ሳምፕል ስላደረግካቸው ስራዎች ደግሞ እናውራ። "Under African skies" ከሚለው የቢቢሲ ዶክመንተሪ ላይ ሳምፕል ወስደህ በሙዚቃህ ያካተትከው ለምንድን ነው?

ካሥማሰ- ቪዲዮውን እኛ ስናየው በጣም የተለየ ስሜት ነው የሚሰጠን። እና ይኼ ሳምፕል ያደረግነው ንግግር የምሁራኖቹ ክርክር ነበር። እኛ በእነርሱ ዘመን ብንሆን ምን ልንል እንችላለን? ወይም ምን እናድርግ እንላለን? ብለን ነው ያሰብነው እና ከእነርሱ ንግግር ጀምረን ነው ማጣራት የጀመርነው። ንግግሩን ከሰማኸው በሰዓቱ ለዓለም ሙዚቃ ምን እናድርግ? ምን አስተዋጽኦ እናበርክት? የሚል ውይይት ነው የነበረው። ስለዚህ ያልተቋጨ ውይይት ነው ብለን ነው ያመንነው። ከዚያ በኋላ ውይይቱ በዚያው ነው የተቋጨው፤ ወደ ውሳኔ የተገባ አመልመሰለኝም። እኔ አይመስለኝም በግሌ። ስለዚህ እኛ የግላችንን ሃሳብ እንጨምርበት በሚል ነው። ሲያልቅ ከሰማኸው ስለ ብሬክ ዳንሲንግ እያወራ ነበር የጨረሰው። እና ብሬክ ዳንሲንግ እኛ ጋር የለም እንግዲህ በዚያን ጊዜ ስለ ብሬክ ዳንስ ማወራት ከቻሉ እኛስ አሁን ስለ ብሬክ ዳንስ እንዴት አላወራንም በሚል ነው መጀመሪያ ሃሳቡ የተጠነሰሰው። ስለዚህ እዚያ ላይ ሀሳብ ለማከል ብለን ነው።

ቢቢሲ- 'ወርቃማው ዘመን' የሚባለው ዘመን ሙዚቀኞች፤ አለማየሁ እሸቴ፣ አስቴር አወቀ ለምን በሥራዎችህ ተካተቱ? በቀደመውና በአሁኑ ዘመን ድልድይ እየፈጠርኩ ነው ብለህ ታስባለህ?

ካስማሰ- በትክክል ይህ ነው ሃሳቡ፤ አሁን ካሉት ሙዚቃዎች የበፊቱ ስራ የነበረው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ከፍተኛ ነው ብለን ነው የምናስበው። እና እኛ እነዚህን ስራዎች ምን ያህል እንደምናከብራቸው እንዴት እንደምናያቸው እንዲመለከቱት ብለን ነው። እኛ እነርሱን እያየን ነው። ይህንን ሁሉ ብንሰራ ሃሳባችን እንዲደርሳቸው በማሰብ ነው።

ቢቢሲ -ማለዳ የተሰኘው ስራህ ስለ አገር ነው። ውበት ደግሞ ስለአዲስ አበባ። ስለ አገር አንድነት፣ አንድ ሆኖ ወደፊት ስለመጓዝ በሙዚቃዎችህ ታነሳለህ፤ ለመሆኑ ኢትዮጵያን እንዴት ትገልጻታለህ? ስለ አንድነት ስታወራ ማየት የምትፈልገውስ ምን አይነት አገር ነው?

ካሥማሰ- ቅድም እንዳልከው ድልድይ ለመሆን ነው። ድልድዩ መሰራት የሚችለው ደግሞ ትክክለኛ የሆነ የእውቀት ሽግግር ሲኖር ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ እኛ ከታላላቆቻችን ምርቃት መቀበል አለብን። ይኹን ሊሉን ይገባል። እነርሱም ሃሳባቸው፣ ሲመኙት የነበረው ያልተቋጨ ነገር ካላቸው ለእኛ ነግረውን እኛ የምናሳካው ይሆናል ማለት ነው። ልጆች ደግሞ እንዲወዱትና ለነገ ጥሩ ተስፋ እንዲይዙ ነው። ወደ ሌላ እንዳይሄዱ ወደራሳቸው እንዲመለሱ ለመተባበር ነው። ስለዚህ እኔ ድሮ እንደነበረው ስሟ እንዲገን፣ እንዲመለስ ነው የምፈልገው። ያኔ እኔም አብሬ ክብር ይሰጠኛል ብዬ ስለማስብ። ለአገራችን ክብር ሲሰጥ ለእኛም ክብር ይሰጣል ብዬ አስባለሁ።

ቢቢሲ- ሂፕ ሆፕን ከኢትዮጵያ ሙዚቃ (በዋነኛነት እንተ ከመረጥከው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ስልት) ጋር የሚያስተሳስረው ነገር አለ?

ካሥማሰ- ሂፕ ሆፕ እኛ አስተዳደግ ላይ የተሻለ ተጽዕኖ አድርጎ ነበር። ስለዚህ ብዙዎች ወጣቶች ከዚሁ ጨዋታ ጋር ስለሆነ የተያያዙት፣ እኛም እዚሁ ጨዋታ ላይ ስለሆነ ያለነው እኛ ለየት እናድርገው እስቲ፣ እኛ ወደ ራሳችን እንመለስ በግላችን እንሞክረው የሚል ነገር ነው ያለኝ።

ቢቢሲ- የማን ተጽዕኖ አለብህ ከአገር ውስጥ ከውጪ?

ካሥማሰ- ከባድ ጥያቄ ነው. . . አንድ ስራ ልጥራ ብል ከውጪ ቦብ ማርሌ ከአገር ውስጥ ደግሞ የሙላቱ አስታጥቄን ሰራዎች በጣም ነው የምሰማቸው።

ቢቢሲ- ግማሽ አልበም ማለት በእንጀራ ቢታሰብ እንጎቻ እንደማለት ነው። ሙሉውን መቼ እንጠብቅ?

ካሥማሰ- (ሳቅ) በዚህ ቀን ማለት ባልችልም ከወራቶች በኋላ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ።