ሙዚቃ፡ በሦስት ሳምንት ውስጥ ከ3 ሚሊየን በላይ ተመልካቾች ያገኘው ዲሽታግና

ድምጻዊ ታሪኩ ጋንኪሲ

የፎቶው ባለመብት, Nahom Records inc FB

የልጆች ለቅሶ፣ የእናቶች ሃዘን፣ የአባቶች ተስፋ መቁረጥ በበረታበት ወቅት ድንገት የመጣ የፍቅር ጥሪ።

ከልጅ እስከ አዋቂ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ መልዕክቱ ደርሷቸው አጣጥመውታል። እንደ ወጀብ ጠዋት ማታ እየበጠበጣቸው ካለው መጥፎ ዜና ትንሽ እፎይታን ያገኙበት ይመስላል።

የእንዋደድ መልዕክቱ ምናለ ምድር ላይ ቢወርድ፣ ብንዳንስሰው፣ ብንጨብጠው፣ ሁል ጊዜ ብንኖረው ሲሉ የተመኙም ብዙ ናቸው- ዲሽታግናን።

ዲሺታግና አዲስ ነጠላ ዜማ ነው። ድምጻዊው ታሪኩ ጋንኪሲ ይባላል። በዩትዩብ ከተለቀቀ የተቆጠሩት ሦስት ሳምንታት ብቻ ናቸው።

በሦስት ሳምንታት ውስጥ ከ3 ሚሊየን በላይ ተመልካቾችን አግኝቷል። በርካቶች በማሕበራዊ ሚዲያ ተቀባብለውታል።

ዲሺታግና በተከፈተ ቁጥር ባለበት የማይወዛወዝ ማግኘትም ዘበት ነው።

ዲሺታግና

ዲሽታግና የአሪ ብሔረሰብ አዲስ ዓመት ወይም ዘመን መለወጫ ነው። ዲሽታግና አብረን እንብላ፣ አብረን እንጠጣ፣ የተጣሉትን እናስታርቅ ፣ ለሌላቸው እንስጥ፣ እንደጋገፍ ማለት ነው።

ክብረ በዓሉ "12 ወራትን በድካም፣ በልፋት፣ በደስታና በሃዘን አሳልፈናል። አሁን ደግሞ 12 ወራት ወደ ፊት ይጠብቀናል። ስለዚህ በጥል ማሳለፍ ሳይሆን በፍቅር ፣ በሰላም፣ በመደጋገፍና ያጡትን በመርዳት እናሳልፍ" የሚል የመተሳሰብ መልዕክት የሚሰበክበት፤ በተግባርም የሚታይበት ነው።

ታሪኩ ሙዚቃውን ለመሥራት የተነሳውም ይህ ፍቅር አዘልና አስታራቂ ባህል ቢኮረኩረው ጊዜ ነው። ታዲያ በደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘው የአሪ ልማት ማሕበር ገፋፊነትም ሳይዘነጋ ነው።

"ይህንን ሥራ እኛ ብቻ ከምናውቀው ሰው ሁሉ ይወቀው" ሲል ማሕበሩ ጠርቶ እንዳነጋገረው የሚናገረው ታሪኩ፤ የሙዚቃ ሥራውንም እንደ ማሕበረሰቡ ባህል ተደጋግፈው እንደሠሩት ይናገራል።

ማሕበሩ ምንም እንኳን አቅሙ ያልጠና ቢሆንም ለዚህ ሙዚቃ ግን አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነበር ይላል ታሪኩ።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ገብሬ ይንቲሶም ድጋፍ ቀላል አይደለም። ግጥሞቹን በማስተካከልና በማረም አግዘውታል።

"የተሳሳትኩት ነገር ካለ ብዬ ሰግቼ ነበር፤ ፖለቲካ ከሆነ እንዳልጠፋ ብዬ አስቤ ነበር" ይላል።

በእርግጥ የራሱን ስሜት ለመግለፅ ያህል እንጂ እንዲህ ዓይነት ተቀባይነት አገኛለሁ ብሎ አላሰበም ነበር።

"እኔ ራሴን የገለፅኩበት ለካስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅር ይፈልግ ነበር። እንዲህ ዓይነት ፍቅር ይፈልግ ነበር፤ ተወደደ።" ይላል።

ታሪኩ "የሰው ልጅ ሲሠራ ያገኛል፤ እኛ ይዘን የመጣነው የለም፤ ወደፊትም ይዘነው የምንሄደው ነገር የለም፤ እስካለን ለምን እንጣላለን? ሲልም ይጠይቃል። በርግጥስ የሚያጣላን ምን ይሆን?

ድምጻዊው ለዚህ ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣል። ራስ ወዳድነትንና ፈጣሪን አለመፍራት።

"የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈጣሪን የሚፈራ ነው። አሁንም የሚያወጣን ፈጣሪን መፍራት ነው" ይላል ታሪኩ።

"ይህችን ምድር የተቀላቀልነው ባዷችንን ነው፤ የምንመለሰውም እንደዚያው" የሚለው ታሪኩ፤ ከሰውነት የወጡ ተግባራት የሚፈፀሙት ይህንን ማሰብ የዘነጋን ጊዜ እንደሆነ ይናገራል።

ድምጻዊው እንደሚለው ራስ ወዳድ የመሆንም ውጤቱ እርስ በርስ መናከስ ነው።

"ራስ ወዳድ ስትሆኝ ጠባብ ትሆኛለሽ፤ ሰው ትጠያለሽ፣ ከሰው ትርቂያለሽ፤ ጭንቅላትሽ የሚመግበው አንቺ የምታደርጊው ላንቺም ለሰውም እንደሚመች ነው" ሲል ያስረዳል።

"እኔን እንኳን ይህችን ሰራህ ብለው 'አንተ ጀማሪ ነህ ከማን ትበልጣለህ' ሲሉ ሞራሌን የሚነኩ አሉ" የሚለው ታሪኩ፤ ወደዚች አለም መጥተን የምንሄድበት ትኬት እስኪቆረጥ ድረስ ምናለ በፍቅር ብንኖር ይላል።

በስንኞቹም እንዲህ ገልጾታል።

". . . ያ ባቢሎን እኛን በታተነን

ይሄው እስከ ዛሬ የእውነት ፍቅር አጣን . . .

እኔ አና አዳም አንድ አባቴ

አንችና ሄዋን አንዱ አጥንቴ . . ."

በሙዚቃው ግጥም በአማርኛ ቋንቋ የተገለፁት ስንኞች የሰው ልጅ አመጣጥን የሚገልፁ ናቸው። ግንዱ አንድ ነው እሱም አዳም(አደም) የሚል። በአሪኛ ቋንቋ የተሰናሰሉት ስንኞችም የሚገልፁት ይህንኑ ነው።

ሙዚቃው ተወዳጅነትን ያግኝ እንጂ በገቢ ደረጃ ግን ያገኘው እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይናገራል።

ታሪኩ "ዘፈኑ የተሸጠበትን ዋጋ ሚዲያ ላይ ማውራት ሰዎችን ያስቀይማል" ሲል አሃዝ ከመጥቀስ ተቆጥቧል።

ነገር ግን " ትንሽ ብር ናት በጣም አዝኘ ነው የወሰድኩት" ብሏል ታሪኩ ጋንኪሲ።

ታሪኩ ጋንኪሲ ማን ነው?

ትውልድ እና እድገቱ ከደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ጂንካ 20 ኪሎ ሜትር በምትርቀው በርቃ ቀበሌ ነው። የተቃኘውም በዚሁ ዞን ከሚገኙ ብሔረሰቦች መካከል አንዱ በሆነው አሪ ብሔረሰብ።

የውትድርና ሕይወትን ተቀላቅሎ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተዋግቷል።

ለ6 ዓመታት ያህልም ነዋሪነቱን በአዲስ አበባ አድርጎ ነበር።

በቆይታው በቀን ሥራና በጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወቱን ገፍቷል።

ታሪኩ አዲስ አበባ በቀን ሠራተኝነት ተቀጥሮ ሲሰራ "የሚከፈለኝ በቀን ሰባት ብር ነበር" ብሏል።

የሕይወት ውጣ ውረድን አይቷል። ሕይወቱን ለማሻሻል ያልሰራው ሥራ የለም። ሳይክልና ጆተኒም ያከራይ ነበር።

እየቆየ ሲሄድ ግን የከተማ ሕይወት ከእርሱ ነፍስ ጋር የተስማማ አልመስልህ አለው።

የከተማ ኑሮ በቃኝ ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ኑሮውን ጂንካ አደረገ። የእርሻ ሥራም መተዳደሪያው ሆነ።

"የጫካ ሕይወት አሪፍ ነው። ጫካ አይናገር ፣ አይሳደብ፣ ከየት መጣህ አይል? እዚያው መኖር ነው። ሳሩም መድሃኒት ነው። ከተማው ግፊ በዛበት" ይላል ታሪኩ።

ከተማ ውስጥ ያለው መገፋፋት፣ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሽኩቻ ሰላም ቢነሳው ጊዜ " በመጣሁበት ጭንቅላቴ ወደ አገሬ ተመልሼ ብሔድ ይሻላል" ሲል ውሳኔ ላይ መድረሱን ተናግሯል።

ታሪኩ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነው።

ከአባይ የተጋባው የኦሞ ወንዝ ቁጭት

በአፈር ያደፈ ወንዝ በጸጥታ ይጓዛል። በርቀት ለሚያየው ከመሬት የፈለቀ አንዳች ቡናማ ቀለም እንጂ የሚፈሰው ውሃ አይመስልም።

ከወንዙ ዳርቻ ታሪኩ ፣ አንድ ወንድና አንድ ሴት ቆመው ይጨዋወታሉ። ስለ ወንዙ መሆኑ ነው።

"ይህ ወንዝ እንጨት ፣ ሳር፣ አፈር ይዞ ሲሄድ 'ትርፍ ጭኗል ?' ብሎ የጠየቀው አለ?" ሲሉ መንግሥትንም፣ ሕዝቡንም፣ አፈሩንም ይወቅሳሉ።

ይህ ጭውውት የሚታየው በማሕበራዊ ሚዲያ በተለቀቀ አንድ አጭር ተንቀሳቃሽ ምሥል ነው።

ታሪኩ እንዳለው ምሥሉ የተቀረፀው የደቡብ ኦሞና ኬንያ ድንበር ላይ ነው። ጊዜው ደግሞ ከሁለት ወይም ከሦስት ዓመታት በፊት። ሃሳቡ ይህ ወንዝ እያለ እንዴት እንራባለን፣ እንዴት የእርዳታ እህል እንለምናለን? የሚል ነው።

"ውሃው ለልማት መዋል እየቻለ ያንጋቶም፣ ዳሰነች፣ ሃመር የእርዳታ እህል ነው የሚበሉት እና ባለሃብቶች እዚያ ላይ ቢያለሙ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር በጨዋታ መልክ የሠራነው" ሲል ያስታውሳል።

ቪዲዮውን ለተመለከተው ታሪኩ የትወና ችሎታ እንዳለው መገመት ቀላል ነው።

እርሱም እንደሚለው ድራማ ይሞክራል። ግን ዕድሉን ብዙም አላገኘም።

" ትልቅ ሞያ ያለው እያለ ትንሽ ሞያ ያለው በዘመድ አሊያም በሌላ ነገር ይገባል። ስለዚህ ዕድሉን ፈጣሪ እስከሚያመጣ መጠበቅ ነው። ችሎታን ይዞ ወደ አፈርም መግባት ይቻላል፤ እርሱንም ሰጥቶ ወደ አፈር መግባት ይቻላል። ዞሮ ዞሮ ሁለቱም ወደ አፈር ይገባሉ" ሲል ሰው ያለውን አበርክቶ ቢያልፍ የተሻለ መሆኑን ያስረዳል።

ጥቂት ስለአሪ ብሔረሰብ

ደቡብ ኦሞ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ነው። በውስጡም የተለያየ ባህል፣ ቋንቋና አኗኗር ያላቸው 16 ብሔረሰቦች ይኖራሉ።

ከእነዚህ ብሔረሰቦች መካከል የአሪ ብሔረሰብ አንዱ ነው።

በአሪ ብሔረሰብ ከሕዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ የዘመን መለወጫ በዓል ይከበራል። በብሔረሰቡ አቆጣጠር የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ተደርጎ የሚቆጠረው ታኅሳስ ወር ነው።

በመሆኑም ታኅሳስ 1 የብሔረሰቡ አዲስ ዓመት ወይም የዘመን መለወጫ ሆኖ በድምቀት ይከበራል።

የዘመን መለወጫው በዓል በብሔረሰቡ ቋንቋ ዲሽታግና ይባላል።

ይህ የብሔረሰቡ የጊዜ አቆጣጠር 'ሎንጋ' ተብሎ ይጠራል።