ሙዚቃ፡ ድንገት ብቅ ያለችው ትውልደ ኢትዮጵያዊት የቤልጂየም ሙዚቃ ኮከብ

መስከረም ሜስ

የፎቶው ባለመብት, MESKEREM MEES

የምስሉ መግለጫ, መስከረም ሜስ

ለመጀመሪያ ጊዜ ሙዚቃዋን ለሰማ የማይረሳ ትዝታን ታሳርፋለች ይላሉ ሙዚቃዋን የሰሙ። መድረክ ላይ ባላት የመዝፈን ችሎታም ሆነ ለስለስ ብሎ በሚስረቀረቀው ድምጿ የብዙዎችን ቀልብም መሳብ ችላለች።

የሙዚቃ ተችዎችም በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ውስጥ ብሩህ ተስፋ ሊኖራት እንደሚችሉም ከወዲሁ እየተናገሩ ነው።

መስከረም ሜስ ትባላለች።

በጥቅምት ወር ይህች ዝናን እያተረፈች ሙዚቀኛ በሮክ ባንዶች መካከል የሚደረገውን የሁሞ ሮክ ራሊ ውድድር ማሸነፍ ችላለች።

ውድድሩ ከአውሮፓውያኑ 1978 ጀምሮ በቤልጂየሙ መፅሔት ሁሞ የሚካሄድ ነው። የመድረክ አያያዟ፣ ጊታር አጨዋወቷና ድምጿ ብዙዎችን ያስደመመ ሲሆን፤ በሙዚቃው ኢንዱስትሪ አዲስ ኮከብ ልትወጣ መሆኑ ማሳያ ነው ተብሏል።

ዓመታዊው ሮክ ራሊ የዘንድሮው ዝግጅት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ጥቂቶች የታደሙበት ሆኗል። መስከረም በጓደኞቿና በቤተሰቦቿ ታጅባ ይህንን ውድድር ማሸነፏ ዝናን እንድትጎናጸፍ ከማድረጉ በላይ ህይወቷንም ቀይሮታል።

መስከረም ሜስ ማን ናት?

ትውልዷ ኢትዮጵያ ሲሆን ገና የአስር ወር ጨቅላ እያለች የቤልጂየም ዜግነት ባላቸው ቤተሰቦቿ በማደጎ ወደ መሄዷን ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ ተናግራለች።

ያደገችውም በወደብ ከተማዋ ጌንት አቅራቢያ በምትገኝ ሜሬንድሬ በምትባል ትንሽ ከተማ ነው።

ገና በጨቅላነቷ ከኢትዮጵያ በመውጣቷ የአፏን የፈታችው በደች ቋንቋ ነው፤ ስለ ኢትዮጵያም የምታስታውሰው ምንም ነገር የለም።

"ከህፃናት ማሳደጊያ ቤት ነበር ወደ ቤልጂየም በማደጎ የመጣሁት" የምትለው መስከረም የወላጇቿንና ቤተሰቦቿን ማንነትም አታውቅም።

በጉዲፈቻ ያሳደጓት ቤተሰቦቿ የነገሯት ነገር ቢኖር አዲስ አበባ ከሚገኝ የማሳደጊያ ቤት መወሰዷን ነው። ህይወት በማደጎ በወሰዷት ቤተሰቦቿ ቤት ውስጥ በእንክብካቤ የተሞላና የልጅነት ህይወቷም "መልካም መሆኑንም" ታስረዳለች።

ካደገችም በኋላ ቢሆን ይህ ነው የሚባል ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር እንደሌላት ትናገራለች። መስከረም ከሙዚቃ ችሎታዋም በተጨማሪ ደች፣ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ አቀላጥፋ የምትናገር ሲሆን "የትኛውንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መረዳትም ሆነ መናገር አልችልም" ትላለች።

ሆኖም ስሟ መስከረም ምን ማለት እንደሆነ ታውቅ እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበላት ጥያቄ ምላሿ "አዎ" ነበር። ስሟን የምትናገርበት የቋንቋ ቅላፄም ለየት ያለ ነው።

መስከረም (ከቀኝ መጀመሪያዋ) ወደ ኢትዮጵያ በጣችበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, MESKEREM MEES

የምስሉ መግለጫ, መስከረም (ከቀኝ መጀመሪያዋ) ወደ ኢትዮጵያ በጣችበት ጊዜ

መስከረም ታዳጊ እያለች በጉዲፈቻ ከወሰዷት ቤተሰቦቿና ከሁለት ወንድሞቿ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት እድሉን አግኝታ ነበር።

ስለነበራትም ቆይታ መስከረም እንዲህ ትላለች "በጣም ነው ኢትዮጵያን የወደድኳት። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያየሁዋቸውን ቆንጆ አበቦች አሁንም ፊቴ ላይ ድቅን ይላሉ። ህንፃው ራሱ ገራሚ ነው። በእውነቱ የኢትዮጵያ ጉብኝቴ ለየት ያለ ነበር" ትላለች።

ኢትዮጵያን ስትጎበኝ የመጀመሪያ ጊዜዋ እንደመሆኑ "የቱሪስት አይነት ጉብኝት የነበረ ሲሆን" እንዲሁም ገና ታዳጊ በመሆኗም ከአገሪቷ ጋር ይህ ነው የሚባል ግንኙነት እንዳትመሰርት ምክንያት እንደሆነ ትጠቅሳለች።

ነገር ግን መቼም ቢሆን የማትዘነጋው ጉዳይ "የሕዝቡ ደግነት፣ ቀናነትና እንግዳ ተቀባይነትን ነው" ትላለች።

የመስከረም የሙዚቃ ህይወት

የመስከረም የሙዚቃ ህይወት የሚጀምረው ገና በልጅነቷ ነው። ተማሪ እያለች ነበር የአውሮፓውያኑን ክላሲካል ሙዚቃ ተብሎ የሚጠራውን ነው ያጠናችው። ስመ ጥር የሚባሉ የሙዚቃ አቀናባሪ የሆኑትን የባህ፣ የሞዛርትና የቤትሆቨንን ሥራዎችን አጥንታለች።

ይህም የራሷን የሙዚቃ ስልት እንድታዳብር መነሻ እንደሆናት ትናገራለች።

ምንም እንኳን ትምህርቷ የክላሲካል የሙዚቃ ስልት ቢሆንም ስታድግ አባቷ ይጫውተው የነበረው የ40ዎቹና የ50ዎቹ ፎክሎር የተሰኘው የሙዚቃ ስልት ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳርፎባታል።

በተለይም በ1960ዎቹ በማኅበራዊ ፍትህ ዘርፍ ትልቅ ሚና የተጫወተው እንደ አሜሪካዊው ቦብ ዲለን ያሉ ሙዚቀኞች በእሷ የሙዚቃ ህይወት ትልቅ ስፍራ እንዳላቸው ትናገራለች።

የራሷን የሙዚቃ ስልት በተመለከተም እንዲህ በአንድ የማይወሰን እንደሆነና ሰፊ መሆኑንም ትገልጻለች።

"ስዘፍን ራሴን የተለየ ዓለም ውስጥ አገኘዋለሁ። ሙዚቃ ውስጤን የምገልፅበት፣ ከህሊናዬ ጋር የማወራበት ነው" ትላለች።

መስከረም መሰንቆ ለመጫወት ስትሞክር

የፎቶው ባለመብት, MESKEREM MEES

የምስሉ መግለጫ, መስከረም መሰንቆ ለመጫወት ስትሞክር

መስከረም በራሷ የሙዚቃ ምህዋር ላይ ብቻ የምትዞር ሳይሆን ለአንዳንዶች ምናልባት 'አይዲያሊስት' ትመስላለች።

"'አይዲያሊስት' ነኝ ብለሽ ታስቢያለሽ?" ከቢቢሲ የቀረበላት ጥያቄ ነበር "ምን ማለት እንደሆነ አላውቀውም። ትልቅ ቃል ነው። ገና 21 ዓመቴ ነው። ገና ዓለምን መፈተሽ መጀመሬ ነው" ትላለች።

መስከረም በአሁኑ ወቅት መኖሪያዋን በትልቋ ከተማ ጌንት አድርጋለች "ነፃነቴን ምናልባት በከፍተኛ ሊባል በሚችል ሁኔታ እየተደሰትኩበት ነው። የምመለስ አይመስለኝም። ዓለምን ለማየት ተዘጋጅቻለሁ፤ ዓለምም እየጠበቀኝ ነው" ትላለች።

ነገር ግን ከእሷ ጋር በሃሳብም የሚመሳሰሉ ሰዎችን ማግኘት ቀላል እንዳልሆነ ታስረዳለች። "የእኔ ዓለም ከሌሎች ጋር የሚገጣጠመው እንዴት ነው" በማለት ራሷን በተደጋጋሚ የምትጠይቅ መሆኑንም ትገልጻለች።

በተለይም በአሁኑ ወቅት ባገኘችው ድንገተኛ ዕውቅና፣ ታዳሚዎቿን ማግኘት፣ ሕዝቡን ማየት እንዲሁም ሚዲያው እንደሚያስፈራት አልደበቀችም።

"አስፈሪ እንዲሁም አስደሳች ሆኖ ነው ያገኘሁት። ቀላል አይደለም። እንደነዚህ አይነት እሳቤዎች ያነሳሱኛል። ሙዚቃየም ከእነዚህ ሃሳቦች ነው የሚነሱት" ትላለች።

በኢንተርኔት ላይ ብዙ ስለ መስከረም መረጃ የሌለ ሲሆን ምናልባት ይህ ሆን ብላ ያደረገችው እንደሆነ በቢቢሲ ተጠይቃ ምላሿም ትንሽ እንደምታፍርና የግል ህይወቷንም ብዙ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደማታጋራ ትናገራለች።

መስከረም እንደምትለው በፀጥታ የተሞላና የተገለለ ህይወትን ትመርጣለች። ሆኖም በአሁኑ ወቅት ባለው የዓለም ሁኔታ እንዲሁም በጥበብ ኢንዱስትሪው ውስጥ ላሉ እንደሷ አይነት ሰዎች ከማኅበራዊ ሚዲያ መራቁ እንደማይቻልም ታስረዳለች።

ከወረርሽኙ በኋላ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ለማዘጋጀት አስባ እንደሆነ ስትጠየቅ "አዎ! በእንግሊዝ በተለይ የሙዚቃ ዝግጅቶችን ማድረግ እፈልጋለሁ፤ ምክንያቱም የሙዚቃዎቼ መነሻ ስለሆነ" ትላለች።

መስከረም ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች በአንደኛው ምናልባትም በአማርኛ ወደፊቱ ለትዘፍን ሃሳቡ እንዳላት ስትጠየቅ በሰጠችው ምላሽ "ይሄ ለኔ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን ምናልባት አንድ ቀን የማልሞክርበት ምክንያት የለም" ብላች።

ዩቲዩብ ላይ የሚገኙትን የመስከረምን ሙዚቃዎች ለሰማ የምትዘፍነውን የሙዚቃ ስልት በአንድ አይነት ማስቀመጥ ከባድ ይሆናል።

ሙዚቃዋ ከፎክ፣ ጃዝ፣ ፖፕና ክላሲካል የተጣመሩ ስልቶችን የያዘ ሲሆን፤ ለሰስ ያለና የመንቆርቆር ስሜት አለው። ግጥሞቿም ጥልቅ ናቸው። ለስለስ ባለ ድምጿና በጊታሯ ለየት ያሉ ዜማዎችን መፍጠር ችላለች።

"ጆ" በተሰኘው ዘፈኗ የሙዚቃ ሰንጠረዥን መቆጣጠር የቻለችው መስከረም በቅርቡ አልበሟን ለማውጣት በዝግጅት ላይ እንደሆነችና ከሌሎች አርቲስቶችም ጋር የመጣመር እቅድ እንዳላት ታስረዳለች።