በኢትዮጵያ ቲቪና ራዲዮ ጣቢያዎች ለሚያጫውቷቸው ሙዚቃዎች የሚከፍሉት እንዴት ነው?

የፎቶው ባለመብት, PM Images
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች የኮፒራይት መብታቸው እንዲከበር ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል፣ ለአገር መሪዎች አቤቱታ አሰምተዋል፣ በማኅበር ተደራጅተዋል፣ ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ወስደዋል ወዘተ. ..
ድምጻዊ፣ ግጥምና ዜማ ደራሲ ወይም አቀናበሪ ታመው መታከሚያ ሲያጡ፣ ለቀብር ሥነ ሥርዓት መዋጮ ሲሰበሰብ ማየት የተለመደ ነው።
ይህ ቁጭት ከአምስት ዓመታት በፊት ኤልያስ መልካን ጨምሮ ሌሎችም በዙሪያው ያሉ ሙዚቀኞች ከፍተኛ ንቅናቄ እንዲጀምሩ አነሳስቷቸዋል።
ያኔ ወደ 17 የሚደርሱ የሮያሊቲ ክፍያን ለማስከበር የተቋቋሙ የኪነ ጥበብ ማኅበሮች ነበሩ። ከነዚህ መካከል ሙዚቃ ተነጥሎ ወጣ።
ከብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ደጅ ጥናትና ትግል በኋላ የኢትዮጵያ የሙዚቃ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር ተመሠረተ ይላል ድምጻዊ ኃይለሚካኤል ጌትነት (ሀይሌ ሩትስ)።
ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ ከቀጣዩ ዓመት መስከረም ጀምሮ የቴሌቭዥን እና ራድዮ ጣቢያዎች ለሚያጫውቷቸው ሙዚቃዎች ሮያሊቲ መክፈል እንደሚጀምሩ ተናግሯል።
የክፍያ ተመን የወጣው እንዲሁም ሮያሊቲው ተሰብስቦ ለሙዚቀኞች የሚከፋፈለው በጋራ አስተዳደር ማኅበሩ በኩል ነው።
ሮያሊቲ እንዴት ይሰበሰባል? እንዴትስ ይከፋፈላል?
የቅጂና ተዛማጅ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር የወጣው አዋጅ ቁጥር 410/1996 ወቅታዊ ሁኔታን እንዲያማክል ማሻሻያ ተደርጎበት አዋጅ ቁጥር 872/2007 ሥራ ላይ ውሏል።
በሙዚቃ ውስጥ የመብት ባለቤት የሆኑት ድምጻዊ፣ ዜማ ደራሲ፣ ግጥም ደራሲ፣ አቀናባሪ እና ፕሮዲውሰር ናቸው። ከሚገኘው ጥቅም እያንዳንዳቸው 20 በመቶ ድርሻ ይወስዳሉ።
በሕይወት ሳሉና ከሞቱ በኋላ ደግሞ እስከ 50 ዓመት ድረስ መብት አላቸው። ከዚያ የወራሾች መብት ነው።
ሙዚቃ በድጋሚ ሲሠራ የሙዚቃው የመጀመሪያ ባለቤት ተጠቃሚ ይሆናል። ሙዚቃው ቀለም ሲጨመርበት (ሪሚክስ ወይም ፊቸሪንግ ሲሠራ) የሙዚቃው ባለቤትና አዲስ ቀለም የጨመረበትም ይከፈላቸዋል። የጨመረው ሙዚቀኛ የሚከፈለው የባለቤቱን መብት ለመጋራት እስከተፈራሙበት ጊዜ ድረስ ነው።
የጋራ አስተዳደር ማኅበሩ ሮያሊቲ መሰብሰብ የሚጀምረው ከመገናኛ ብዙኃን ነው። በቀጣይ ሆቴሎች፣ ባርና ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና ሌሎችም ሙዚቃ የሚጠቀሙ ሮያሊቲ የሚከፍሉበት መዋቅር ይዘረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የጋራ አስተዳደር ማኅበሩ፤ የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማኅበርን ጨምሮ ከሌሎችም የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች ጋር በሮያሊቲ ተመን ላይ ተነጋግሯል።
"ያስቀመጥነው ተመን የተጋነነ አይደለም። አሁን የምንፈልገው የሮያሊቲ ክፍያ አሠራር እንዲጀመር ስለሆነ ክፍያው በሳንቲምና በአንድ ብር ደረጃ የተሰላ ነው" ይላል ኃይሌ ሩትስ።
ክፍያው በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ነው። የመገናኛ ብዙኃንን የመክፈል አቅም እና የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ከግምት ያስገባ እንዲሆንም ይጠበቃል።
በዚህ መርሕ መሠረት ተመኑ ሲሻሻል የጋራ አስተዳደር ማኅበሩ እና መገናኛ ብዙኃን (ወይም በቀጣይ ሮያሊቲ መክፈል የሚጀምሩ ሌሎች ዘርፎች) በዋጋው መስማማት አለባቸው።
ሁለቱ አካላት ስምምነት ላይ ሲደርሱ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ የስምምነት ሰነዱን ያጸድቃል። ሮያሊቲ በአግባቡ መሰብሰቡንና ለባለሙያዎች መከፋፈሉንም ይቆጣጠራል።
አይበለውና ሙዚቃ አስተላልፎ ሮያሊቲ አልከፍልም የሚል ተቋም ካለ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ የሚዳኝበት ልዩ ፍርድ ቤት አለው።
የዘገየው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ሮያሊቲ
የሙዚቃ ሮያሊቲ ክፍያ ካልጀመሩ ጥቂት አገራት አንዷ ናት ኢትዮጵያ።
በሌሎች አገራት ሮያሊቲ የሙዚቀኞች መተዳደሪያ፣ መጦሪያ፣ ለልጆቻቸው ውርስ ጭምርም ነው።
ዘ ሂል ሲስተርስ እአአ በ1893 ያወጡት 'ሀፒ በርዝደይ' 50 ሚሊዮን ዶላር ሮያሊቲ በማስገባት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው። የጆን ሌነን እና ፖል ማክርኒ 'የስተርደይ' እአአ ከ1965 ወዲህ ወደ 30 ሚሊዮን ዶላር ሮያሊቲ አግኝቷል።
ጎረቤት አገር ኬንያ እንዲሁም ሌሎችም የአፍሪካ አገራት የሮያሊቲ ክፍያ አሠራራቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻሉ መጥተዋል።
ሀይሌ ሩትስ እንደሚለው፤ በቀጣይ ዓመት የሚጀመረው የሮያሊቲ ክፍያ የዓመት (ብላንኬት ላይሰንስ) እና ጊዜያዊ (ቴምፖረሪ) በሚል ተከፍሏል። ጊዜያዊ ማለት ለአውደ ዓመት ወይም ለሌላ ሁነት ለተወሰነ ጊዜ የሚሰጥ ፍቃድ ነው።
ዩቲዩብ እና ሌሎችም የበይነ መረብ ሙዚቃ ማሰራጫዎች ካላቸው ተመልካችና የገቢ መጠን አንጻር ቀመር ወጥቶላቸዋል።
መገናኛ ብዙኃን በርካታ አድማጭ ወይም ተመልካች የሚያገኙበት (ፕራይም ታይም) እና መደበኛ የስርጭት ጊዜ (ሬጉላር ታይም) ከግምት ይገባል።
በሌሎች አገራት የሙዚቃ ሮያሊቲ ሲሰላ ታሳቢ የሚደረጉ ነገሮች እነዚህ ብቻ አይደሉም። በኢትዮጵያም በሙዚቀኞችና ሙዚቃውን በሚያስተላልፉ መካከል የሚደረገው ስምምነት በጊዜ ሂደት እየተከለሰ እንደሚመጣ ኃይሌ ሩትስ ያስረዳል።
የጋራ አስተዳደር ማኅበሩ ሙዚቀኞች እና ሥራዎቻቸውን በመመዝገብ የመረጃ ቋት እያዘጋጀ ነው።
"የቱ የማን ሥራ ነው የሚለው እየተመዘገበ ነው። የሞቱ ሙዚቀኞች ቤተሰቦች ማኅበሩ ሮያሊቲውን ያስተዳድርልን ብለው እያስመዘገቡ ነው። በሕይወት ለሌሉ ሙዚቀኞች ሮያሊቲውን ለቤተሰብ እንሰጣለን" ይላል።
የመረጃ ቋቱ ሲደራጅ ሮያሊቲውን ለማከፋፈልም እንደሚቀል ያምናል።
ወራሽ ወይም ባለቤት የሌለው ሙዚቃ፤ ሮያሊቲው ለአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ገቢ ተደርጎ ሙያውን ለመደገፍ ይውላል።
በመገናኛ ብዙኃን ምን ያህን ሙዚቃ ተላለፈ? አንድ ሙዚቃ ስንቴ ተጫወተ? የሚሉትን ለማወቅ መተግበሪያ እንደተዘጋጀ ኃይሌ ሩትስ ይናገራል።
መገናኛ ብዙኃን ያጫወቱትን ሙዚቃ ስብስብ (ፕለይሊስት) ለማኅበሩ እንዲልኩ ይደረጋል። ማኅበሩም በቴሌቭዥን እና ራድዮ የሚተላለፉ ሙዚቃዎችን በመተግበሪያው ይመዘግባል። ከዚያም ክፍያው ይሰበሰባል።
ሮያሊቲ እውን እንዲሆን አንድ ትውልድ መስዋዕትነቱን ከከፈለ በመጪው ዓመታት ፈር ይይዛል የሚለው ኃይሌ ሩትስ፤ "ሙዚቃ በራድዮ እየተጫወተ፣ ባር እያሻሻጠ እስካሁን አለመደራጀታችን ጎድቶናል። አሪፍ አዋጅ አለን። መተግበር ነው ያቃተን" ሲል ያስረዳል።
ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ሲወያዩ እንከፍላለን፣ አንከፍልም የሚል ክርክር እንዳልገጠማቸው ያክላል።

የፎቶው ባለመብት, SEAN GLADWELL
ሮያሊቲ "እንደ እርዳታ ሳይሆን እንደ ኃላፊነት መቆጠር አለበት። [ሳይከፈል ሲቀር] የሰውን መብት እንደመጋፋት መቆጠር አለበት። ለድምጻዊ፣ ለዜማና ግጥም ደራሲ ላባቸው ነው" ይላል ድምጻዊው።
መገናኛ ብዙኃን ምን አሉ?
መገናኛ ብዙኃን ሙዚቃን ያለ ክፍያ በማስተዋወቅ፣ ሕዝብ ጋር በማድረስ ለዘመናት አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ሙዚቀኞች ደግሞ መገናኛ ብዙኃንን የማሞቅ፣ የማድመቅ ሚና አላቸው። ሁለቱ ዘርፎች ተመጋጋቢ ናቸው።
ጥያቄው ሁለቱንም የማይጎዳ የክፍያ መጠን ምን ያህል ነው? በመካከላቸው የሚኖረው ስምምነትስ ምን መምሰል አለበት? የሚለው ነው።
14 አባላት ካሉት የኢትዮጵያ ብሮድካስተሮች ማኅበር ቢቢሲ ያናገረው የኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ ዋና ኃላፊ አማን ፍስሐጽዮን፤ የሮያሊቲ ክፍያ ሐሳብን ቢደግፍም ሁለት መጥራት አለባቸው የሚላቸውን ጉልህ ነጥቦች ያነሳል።
አንደኛው፤ የጋራ አስተዳደር ማኅበሩ መገናኛ ብዙኃን ያጫወቱትን ሙዚቃ የሚቆጣጠርበት ሁነኛ መንገድ እንዲዘረጋ ነው።
ሁለተኛው፤ የሙዚቀኞችን ሮያሊቲ የሚሰበስቡ የጋራ አስተዳደር ማኅበራት ከአንድ በላይ ሆነው መገናኛ ብዙኃን ለማን እንክፈል? የሚል ውዝግብ ውስጥ ይገባሉ የሚለው ስጋት ነው።
"የኛ ሙዚቃ አድጎ የሚገባው ቦታ አልደረሰም። በፊት ያሉትም የአሁኖቹም ተጠቃሚ ሆነው አናይም። ስለዚህ ተጠቃሚነታቸውን እንደግፈዋለን። ያጫወትነውን ሙዚቃ የሚቆጣጠሩበት ሥርዓት ካልተተገበረ ግን ወደ ጭቅጭቅ እንገባለን። ማኅበራቱ ከአንድ በላይ ሆነው መጥተው ክፍያ ከጠየቁም አስቸጋሪ ይሆናል" ሲል ያስረዳል።
ኢቢኤስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ከዋናው ጣቢያ በተጨማሪ ኢቢኤስ ሙዚቃ የሚባል ሙዚቃ ብቻ የሚተላለፍበት እህት ጣቢያ አለው።
ሙዚቀኞች ዘፈናችንን አጫውቱልን ብለው ኢቢኤስን ጠይቀው ጣቢያው ያስተላልፍላቸዋል። ይህ ጣቢያ ታዲያ "ገቢ የለውም" ይላል አማን።
አማን እንደሚለው፤ የሮያሊቲ ተመን ፍትሐዊ መሆን እንዲሁም ማሻሻያ ሲደረግበትም የመገናኛ ብዙኃንን ነባራዊ ሁኔታ የሚያገናዝብ ሊሆን ግድ ይላል።
ከዓመታት በፊት የተመሠረቱ መገናኛ ብዙኃን እና ጀማሪ ጣቢያዎች እንዴት ይስተናገዳሉ? የሚለው ጥያቄ እንዲመለስም ይፈልጋል።
"በግሌ በቀረበው ዋጋ ችግር የለብኝም። የራድዮ ያንሳል። የቴሌቭዥን ይጨምራል። አብዛኛው መገናኛ ብዙኃን ከሮያሊቲ ሐሳብ ጋር ችግር የለበትም። የተማከለ አሠራር ተፈጥሮ በድርድር መሥራት ነው ያለብን" ይላል።
የተማከለ አሠራር ካልተዘረጋና ሙዚቃ ማጫወትን ተከትሎ የሚመጣው የክፍያ ሂደት ውጥንቅጡ የወጣ ከሆነ መገናኛ ብዙኃን ሙዚቃ ማስተላለፍን እንዲተው ሊገፋፋ እንደሚችል ስጋት አለው።
"ብርቅዬዎቹ ይህንን ቀን ሳያዩ ማለፋቸው ያሳዝናል"
ሙዚቀኞችም ይሁኑ መገናኛ ብዙኃን ሕዝብን የመድረስ የጋራ አላማቸውን ታሳቢ በማድረግ፤ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ ምክክር አድርገው ውሳኔ እንዲያሳልፉ ነው አማን የሚፈልገው።
ኃይሌ ሩትስ ከመገናኛ ብዙኃን ቀና ምላሽ መገኘቱን በመጥቀስ፤ በዋናነት የሮያሊቲ ክፍያ መጀመርን ተስፋ ያደርጋል።
መሀላቸው ሆኖ ሂደቱን የሚያሳልጠው አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሁለቱ ስምምነት ላይ ሲደርሱ አጽድቆ፣ አተገባበሩን ይከታተላል።
በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ፤ የጋራ አስተዳደር ማኅበራት ድጋፍና ክትትል መሪ አዲስ ስዩም ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ የሮያሊቲ ክፍያ ሲተገበር፤ ሙዚቃ ሲጫወት ጥቅም የሚያገኙ አካላት ጥቅሙን የሚጋሩበት አሠራር ይዘረጋል።
የክፍያ ተመኑ የማኅበረሰቡን፣ የከፋዩን ተቋም እና የአገሪቱን አቅም ወይም ነባራዊ ሁኔታ እንዲያገናዝብ እንደሚፈለግ ያክላል።
"ሙያውን ይደግፋል። ባለ መብቶቹንም ይደግፋል። ባለሙያው ሥራው ላይ ብቻ እንዲያተኩር ያደርጋል። ዘርፉን ያሳድጋል። አገርም ይጠቅማል" ይላል።
ከዚህ ባሻገር ኢትዮጵያ የበርን ስምምነት (በርን ኮንቬንሽን) እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ስትፈርም በተጨማሪም የዓለም ንግድ ተቋምን የመሰሉ ድርጅቶችን ስትቀላቀል፤ የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ውጤቶች በሌሎች አገሮች የኮፒራይት መብታቸው ይጠበቃል። በምላሹም የተለያዩ አገሮች የኪነ ጥበብ ውጤቶች በኢትዮጵያ ኮፒራይታቸው እንደሚከበር ይታመናል።
ኃይሌ ሩትስ፤ በዚህ ጊዜ በኖረና ይህን ውጤት ባየ የምትለው አንድ ሰው ጥራ? ሲባል ሳያንገራግር ስም ጠራ። ኤሊያስ መልካ!
የኢትዮጵያ የሙዚቃ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር እንዲፈጠር ከታገሉ መካከል ዋነኛው የነበረው ኤልያስ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ሁለት ዓመታት አልፈዋል።
ዛሬ በሕይወት ኖሮ የትግሉን ፍሬ ቢያይ ሲል ኃይሌ ሩትስ ይመኛል።
"ከሐሳብ አንስቶ በዚህ ትግል ውስጥ ብዙ አሳልፈናል። መተዳደሪያ ደንቡ እየወጣ ሳለ ነው ሕይወቱ ያለፈው" ይላል በስሜት።
"ትግሉ ማሸነፉን ሳያይ. . . በዚህ ሰዓት ባለመገኘቱ አዝናለሁ። ታላቆቻችን፣ ብርቅዬዎቹ ይህንን ቀን ሳያዩ ማለፋቸውም ያሳዝናል። ቢኖሩ ብሎ ያስቆጫል. . . "














