የሃጫሉ ሁንዴሳ አዲስ አልበምና የዓለም አቀፍ ሽያጭ ደረጃን መቆጣጠር

የፎቶው ባለመብት, Facebook/Hachalu Hundessa
በባለፈው ዓመት የተገደለው ሙዚቀኛ ሃጫሉ ሁንዴሳ በኢንተርኔት ሙዚቃን በሚሸጠው አይቲዩንስ መቶ አልበሞች ውስጥ በአለም አቀፍ ሽያጭ ሰንጠረዥ ሦስተኛ ደረጃን በትናንትናው ዕለት ይዞ ነበር።
የአይቱዩንስ የዓለም የሙዚቃ ሰንጠረዥ (ወርልድ ቻርት) በየሰዓቱ የሚቀያየር ሲሆን ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል።
በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት የሃጫሉ አልበም በዓለም አቀፍ ሽያጭ ሰንጠረዥ በ12ኛ ደረጃ መቀመጡን ከድረ-ገጹ ባገኘነው መረጃ መረዳት ተችሏል።
እንዲሁም ቢቢሲ በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ እንደተከታተለው አልበሙ በምርጥ 40 የአሜሪካ የፖፕ ሙዚቃ ዘርፍ በአይቲዩንስ በሽያጭ አንደኛ ደረጃ መቆጣጠሩን አመልክቷል።
ከትናንት በስቲያ ሰኔ 22/2013 ዓ.ም የወጣው ይህ አልበም 'ማል ማሊሳ' የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን ትርጉሙም "መፍትሄው ምንድን ነው?" የሚል ነው።
ማል ማሊሳ አስራ አራት ዘፈኖችን የያዘ አልበም ሲሆን የሙዚቀኛው ባለቤት ወይዘሮ ፋንቱ ደምሶ ከቢበሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ህይወቱ ከማለፉ በፊት የሰራቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህ አልበም ላይ አራቱ ከዚህ ቀደም ከሰራቸው ሁለት አልበሞች ተሻሽለውና የተሰሩ አስር አዳዲስ ሙዚቃዎች ተካተውበታል።
ከአዳዲሶቹም ሙዚቃዎች ውስጥ የተወሰኑት ያልተጠናቀቁም እንደነበር ቢቢሲ የተረዳ ሲሆን ሃጫሉ ከሞተ ከአምስት ወራት በኋላ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ተገናኝው ሥራዎቹን በማሰባሰብ አልበም እንዲሆን ተደርጓል።
በዚህ አልበም ውስጥ የተካተቱት ዘፈኖች ግጥም ይዘት የፍቅር ዘፈኖችን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን ይዳስሳል።

የፎቶው ባለመብት, Itunes chart
የአልበሙ መጠሪያ የሆነው ማል ማሊሳ ባለፉት መቶ ዓመታት የኦሮሞ ሕዝብ ያሳለፈውን ታሪክ፣ ትግል፣ መስዋዕትነት የሚዳስስ ሲሆን በአሁንም ወቅት መቀጠሉ "መፍትሄው ምንድን ነው?" የሚል ጥያቄ እንዳጫረበት በሙዚቃው መልዕክቱን አስተላልፏል።
በዚህ ዘፈን ላይ በርካቶች ሞተው፣ ታግለው ሕዝብ ከጭቆና ሊላቀቅ ያለመቻሉን ጠቅሶ መቋጫ የሌለው ነገር እንዴት ሊሆን ቻለ በማለት ይጠይቃል።
ነገር ግን በሚሊኒየም አዳራሽ ላይ በአንድ ወቅት አቅርቦት የነበረውን ቀረርቶም በዚህ ሙዚቃ ላይ በማካተት ወጣቱ (ቄሮ) የሕዝቡ ተስፋ አንተ ስለሆንክ ትግሉ መቀጠል አለበት ይላል።
በመጀመሪያ አልበሙ ላይ "ኦልማንኬ" (የአንቺ ውለታ) ብሎ የዘፈነላት ባለቤቱ ፋንቱ በዚህም አልበምምም ላይ "ሃደ ወቢ' (የወቢ እናት) በሚልም ምስጋናውን አቅርቦላታል።
ወቢ የሚለው የኦሮምኛ ቃል ዋስ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን የመጀመሪያ ልጁም መጠሪያ ነው። በዚህም ሙዚቃው ልጁን በፀጋ እንደሰጠችውና እንዲሁም ዋስ እንደሆነችው በድርብ ትርጉም አካትቶታል።
ከዚህም በተጨማሪ የህይወቴ ምሰሶ፣ መሰረቴ ነሽ ይላታል።
ይህንን አልበም የሰሙ ሰዎች አስተያየት እንደሚሰጡት በዚህ አልበም የፍቅርን ዘፈን ጨምሮ፣ ነፃነት፣ ትግልና በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን ወላጅ አልባ ህፃናትንም አስታውሷል።
"ኢልመ ነማ" የተሰኘውና (የሰው ልጅ) በአልበሙ ላይ የተካተተው ይህ ሙዚቃ ህፃናቱ አባትና እናት አልባ መሆናቸው አምላክ ያደረገው ነገር በሆንም ህፃናቱን መርዳትና ማስታወስ እንደሚያስፈልግ ምክሩን ይለግሳል።
በዚህም የአልበም ሥራው ላይ በርካታ ሙዚቀኞች የተሳተፉ ሲሆን ዘጠኙን በማቀናበር በርካታ የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን የሚያቀናብረው ዳዊት ታደሰ ተሳትፎበታል።
ከእሱም በተጨማሪ ካሙዙ ካሳ፣ ዲንቄሳ ደበላ፣ አብርሃም ኪዳኔ በአቀናባሪት የተሳተፉ ሲሆን አስራ አራቱንም ሙዚቃዎች ሚክስና ማስተር ያደረገው አበጋዝ ክብረ ወርቅ ሺዎታ ነው።
በባለፈው ዓመት የተገደለው ሃጫሉ ሁንዴሳ የኦሮሞ የትግል ሙዚቃዎችን በመዝፈን በርካቶችን ማነሳሳቱን እንዲሁም ጭቆናን በሙዚቃው የታገለ፤ ለነፃነት የሠራ በማለት ይመሰክሩለታል።












