በካናዳ ተጨማሪ የ182 ሕጻናት ጅምላ መቃብር መገኘቱ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በካናዳ የነባር ሕዝቦች ልጆች አጽም የተቀበረበት እንደሆነ የሚገመት የ182 ሕጻናት ጅምላ መቃብር መገኘቱ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡
መቃብሩ የተገኘው በብሪቲሽ ኮሎምቢያ አውራጃ አንድ ቀድሞ አዳሪ ትምህርት ቤት በነበረበት ሰፈር አቅራቢያ ነው፡፡
የቀደምት ሕዝቦች ማኅበር እንዳለው የተገኙት መቃብሮች ሁሉም የቀድሞ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው ብሎ ለመደምደም ጊዜው ገና ነው፡፡
ሆኖም ይህ መቃብር መገኘቱ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ከተገኙ መቃብሮች ጋር የሚያያዝ ታሪክ ሊኖረው እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የዚህ መቃብር ስፍራ መገኘት ጁላይ 1 የሚከበረውን የካናዳ ብሔራዊ ቀን በአንዳንድ ቀበሌዎች መርሀ ግብሮች እንዲሰረዙ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ግምት አሳድሯል፡፡
የጀምላ መቃብሮች በተከታታይ መገኘታቸው ብሔራዊ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡
ምርመራው ሲቀጥል ምናልባትም ሌሎች በርካታ የተደበቁ መቃብሮች ሊገኙ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡
ይህ አሁን ተገኘ የተባለው መቃብር ሴይነት ዩጂን ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ታስተዳድረው በነበረ የአዳሪ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ነው በምርመራ የተገኘው፡፡
ይህ ትምህርት ቤት እንደ አውሮጳዊያኑ ከ1912 ተከፍቶ እስከ 1970 የቆየ ነበር፡፡
በመላው ካናዳ 130 ተመሳሳይ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የነበሩ ሲሆን ዋንኛ ተግባራቸው የነባር ሕዝቦችን ቋንቋ፣ ባሕልና ታሪክ ደምስሶ ማጥፋት ነበር፡፡
ትምህርት ቤቶቹ በካናዳ መንግሥት ገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸውና በካቶሊክና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የሚተዳደሩም ነበሩ፡፡
በነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ሕጻናት ከወላጆቻቸው በአስገዳጅ ተቀምተው አዳሪ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ይደረግ ነበር፡፡
ከአውሮፖውያኑ ከ1863-1998 በነበረው ጊዜ ከ150 ሺህ በላይ የሚሆኑት ሕፃናት በተመሳሳይ ሁኔታ ከቤተሰቦቻቸው በአስገዳጅ ተነጥቀው ተወስደው በነዚህ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ይማሩ ነበር።
ባለፈው ግንቦት በተመሳሳይ 215 የጅምላ የሕጻናት መቃብሮች በብሪቲሽ ኮሎምቢያ አውራጃ ካምሉፑስ ውስጥ ተገኝተው ቁጣን መቀስቀሱ ይታወሳል፡፡
ከዚያ በኋላም ባለፈው ሳምንት 751 ሌሎች መቃብሮች መገኘታቸው ይፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ይህም ሳስካቸዋን በተባለው አዳሪ ትምህርት ቤት በነበረበት አቅራቢያ መሆኑ ተገልጧል፡፡
የአሁኑ ጅምላ መቃብር የካናዳ ብሔራዊ ቀን ሊከበር ዋዜማ ላይ መገኘቱ በበዓሉ አስፈላጊነትና ብሎም ትርጉም ላይ ጭምር ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል፡፡
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ የነዚህ መቃብሮች መገኘት በታሪካችን በነባር ሕዝቦች ላይ የተፈጸመው ግፍ እንድናሰላስል የሚያደርገን ነው ብለዋል፡፡












