ቀውስ በተባባሰባት ሱዳን ተቃዋሚዎች ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እንዲደረግ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሱዳን ወደ ዴሞክራሲ መሸጋገርን የሚቃወሙ ዜጎች ሠራዊቱ የአገሪቱን የሥልጣን መንበር እንዲቆጣጠር ቅዳሜ ዕለት ጎዳና ወጥተው ጠየቁ።
የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ እየተባባሰ በመጣበት በዚህ ወቅት በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ከፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት ውጪ ተሰብስበው ነበር።
እአአ በ2019 ፕሬዝዳንት ኦማር አልባሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ወታደራዊ እና ሲቪል ቡድኖች ስልጣን ተጋርተው የሽግግር መንግሥት አዋቅረው ነበር።
ይሁን እንጂ ባለፈው መስከረም ወር ላይ የአልባሽር ተከታዮች እንደተካሄደ ከተገለጸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፍ በኋላ ውጥረቱ አይሏል።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ወታደራዊው መሪዎች የፀረ በሽር ተቃውሞዎችን የመራው እና የሽግግር መንግሥቱ ቁልፍ አካል የሆነው ለነፃነት እና ለለውጥ ኃይሎች (ኤፍኤፍሲ) ጥምረት ማሻሻያ እንዲያደርግ እየጠየቁ ነው። የጦር ኃይሉም በካቢኔውን ለውጥ እንዲደረግ ጠይቋል።
ሆኖም የሲቪል መሪዎች በበኩላቸው ጥያቄዎቹ የጦር ሠራዊቱ ሥልጣን ለመንጠቅ የሚያደርገው ጥረት አካል ናቸው በማለት ይቃወማሉ።
ቅዳሜ የጦር ኃይሉ ደጋፊ ሰልፈኞች "የረሃቡ መንግሥት ይውረድ" የሚል መፈክር በማሰማት የጦር ኃይሎች መሪና የሱዳን የጋራ ወታደራዊ - ሲቪል ሉዓላዊ ምክር ቤት መሪ የሆኑት ጄኔራል አብድል ፋታህ አል-ቡርሐን መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ አገሪቱን እንዲቆጣጠር ጥሪ አቅርበዋል።
አንድ ተቃዋሚ ለኤፍፒኤፍ የዜና ወኪል እንደገለጸው "እኛ ወታደራዊ መንግሥት እንፈልጋለን። የአሁኑ መንግሥት ፍትሕ እና እኩልነት ሊያመጣልን አልቻለም" ብሏል።
ከቀደሙት ሰልፎች በተቃራኒ ተቃዋሚዎች ወደ ፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግሥት በሮች እንዲደርሱ የተፈቀደ ሲሆን የተገኙ የፖሊስ አባላት ቁጥርም ጥቂት ነበር።
የመንግሥት ደጋፊዎችም ለቅዳሜው ሰልፍ ምላሽ ሐሙስ ሰልፍ ጠርተዋል።
የሱዳን ሲቪል ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ዓርብ ዕለት በሁለቱ ዓመታት የሽግግር ዘመን የአገሪቱን "አስከፊ እና አደገኛ" ሲሉ የጠሩትን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታት ይረዳል ያሉትን ዕቅድ ይፋ አድርገዋል።
"በዚህ ግጭት ውስጥ እኔ ገለልተኛ ወይም አሸማጋይ አይደለሁም። የእኔ ግልፅ እና ጽኑ አቋም ከሲቪል ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ጋር ሙሉ በሙሉ መሆን ነው" ብለዋል።
የኦማር አልበሽርን የ30 ዓመት አገዛዝ ተከትሎ የተቀሰቀሱ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችን ተንተርሶ በሚያዝያ ወር ጦር ኃይሉ ጣልቃ በመግባት እንዲያበቃ ካደረገ በኋላ ነበር ሐምዶክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ መሐላ የፈጸሙት።
በሐምዶክ የተካሄዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የነዳጅ ድጎማዎች እንዲቀንሱ እና የዋጋ ግሽበት እንዲጨምር በማድረጉ ከቅርብ ወራት ወዲህ የሽግግር መንግሥቱ ድጋፍ ቀንሷል።













