የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የአገሪቱን ሽግግር ለማደናቀፍ ይሞክራሉ ያሏቸውን አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የአገሪቱን የሽግግር ሂደት ለማደናቀፍ ሙከራ የሚያደርጉ ያሏቸውን አካላት አስጠነቀቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት የአገሪቱን የሽግግር አስተዳደር በሚመራው ሉአላዊ ምክር ቤት ውስጥ ባሉ ወታደራዊና ሲቪል መሪዎች መካከል ያለው አለመግባባት እየተባባሰ ባለበት ጊዜ ነው።
የሱዳን የሽግግር አስተዳደር የተቋቋመው ሰላሳ ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ አገሪቱን በፈላጭ ቆራጭነት ሲያስተዳድሩ የነበሩት ኦማር ሐሰን አልባሽር ከሁለት ዓመት በፊት በሕዝባዊ አመጽ ከሥልጣናቸው ከተወገዱ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አደገኛ ያሉትን በአገሪቱ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ቀውስ ለማርገብ ብቸኛው መንገድ በውይይት ብቻ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ነገር ግን አገሪቱን በሚመራው ሉአላዊ ምክር ቤት ውስጥ ሱዳን በታቀደው መሰረት ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመሸጋገር የምታደርገውን ጥረት ለመቀልበስ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ የጎላ ተጽእኖና ተሰሚነት ያላቸው የሠራዊቱ አባላት መኖራቸው ይነገራል።
ባለፈው መስከረም ወር በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ ተሞክሮ ከከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ የሽግግር አስተዳደሩን በሚመራው ሉአላዊ ምክር ቤት አባላት መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።
የሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት በሱዳን የሽግግር አስተዳደር ላይና በአገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ላይ ወሳኝ ሁኔታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ይገመታል።
የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ደጋፊዎች አሁን ያለው የሱዳን መንግሥት በሌላ እንዲተካ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ ዛሬ ቅዳሜ ለማድረግ ጥሪ አቅርበዋል።
በሚቀጥለው ሐሙስ ደግሞ ሱዳን ወደ ሲቪል አስተዳደር እንድትሸጋገር የሚጠይቅ ሌላ የተቃውሞ ሰልፍ ተጠርቷል።
በአሁኑ ጊዜ ሱዳን ከፖለቲካዊ ቀውሱ ባሻገር ከባድ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ገጥሟታል።
የአገሪቱ ዋነኛ ወደብ በተቃውሞ ሳቢያ በመዘጋቱ ከውጪ የሚገቡ ቁሳቁሶች ዋና ከተማዋን ካርቱምን ጨምሮ ወደ የትኛውም የአገሪቱ ክፍል መንቀሳቀስ ካቆመ ቀናት ተቆጥረዋል።
በዚህም ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት ችግር ተከስቷል።
አገሪቱን ለረጅም ዓመታት በበላይነት የመሩት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ ሠራዊት፣ በሲቪሎች እና ተቃውሞውን በመሩት ቡድኖች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መደረጉ ይታወሳል።
በዚህም ሲቪሉን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን አብደላ ሐምዶክ የያዙ ሲሆን ከሠራዊቱ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር በመሆን አብዱል ፋታህ አልቡርሐን ከፍተኛውን ቦታ ይዘዋል።
ነገር ግን የሱዳንን የሽግግር አስተዳደር በሚመሩት ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናት መካከል ያለው ግንኙነት የሰከነ ሳይሆን ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የደኅንነት ሁኔታ እየተዳከመ የመጣ ሲሆን፣ ምክንያቱም ወታደራዊ መሪዎቹ ሥልጣን የሚያስረክቡበት ወቅትን ለማስተጓጎል ነው ሲሉ ተቺዎች ይናገራሉ።
በሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው ኃያሉ የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ለሲቪሎች ሥልጣኑን በመጪው ኅዳር እንዲያስተላልፍ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለታል።












