ሱዳን የመፈንቅለ መንግሥት 'ሞካሪዎቹ በሙሉ' በቁጥጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሱዳን የተሞከረውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ማክሸፏንና "ተሳታፊዎቹ በሙሉ" በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀች።
የሱዳን መንግሥት ቃል አቀባይ ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት የመንግሥት ግልበጣ ሴራውን የወጠኑት ከሁለት ዓመት በፊት ከሥልጣን ከተወገዱት ከኦማር አል ባሽር ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።
የመንግሥት ግልበጣ ሙከራውን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ካርቱም እና በቅርበት በምትገኘው ኦምዱርማን ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳለና በናይል ወንዝ ላይ ያለው ግዙፉ ድልድይ ተዘግቶ እንደነበር ተዘግቧል።
ወደ ካርቱምና ወደ ወደቦች የሚወስዱት ጎዳናዎች ተዘግተዋል።
የመፈንቅለ መንግሥቱ ሞካሪዎች የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የሚገኙበትን ህንጻ ለመቆጣጠር ሙከራ ማድረጋቸውን የፈንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
የሱዳን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው ማክሰኞ ማለዳ በአገሪቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፉን ይፋ ያደረገው።
የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት መሐመድ አል ፋኪ ሱሌይማን በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የተጠረጠሩ አካላት ላይ ምርምራ እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል።
የመንግሥት ግልበጣውን የሞከሩት ሰዎች በኡምዱርማን የሚገኘውን የአገሪቱን ብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያን ለመቆጣጠር ሙከራ ተደርጎ ነበር።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከካርቱም የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አውራ መንገዶች ላይ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች የመኪናውን ፍሰት ሲቆጣጠሩ ታይተዋል።
በካርቱም ለዛሬ ሊካሄድ የታቀደ የተቃውሞ ሰልፍ የነበረ ሲሆን የመከላከያ ኃይሉ የከተማዋን የፀጥታ ሁኔታ አጠናክሮታል።
ሱዳን ፕሬዝዳንት አል ባሽር እኤአ በ2019 ሚያዚያ ወር ላይ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ የሚመራ የሽግግር መንግሥት እየተዳደረች ትገኛለች።
የቀድሞውን መሪ ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል ከቆዩበት ሥልጣን እንዲወገዱ ምክንያት የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ የጀመረው የዳቦ እና የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ነበር።
አል ባሽር ከስልጣን የተነሱት ለወራት የዘለቀ የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ሲሆን ራሳቸውን ወደ ስልጣን ያመጣቸውን የ1989 መፈንቅለ መንግሥት በሚመለከት የፍርድ ሂደታቸውን እየተከታተሉ ነው።
የመፈንቅለ መንግሥቱ መከራውን ተከትሎ ሁኔታውን ለመቆጣጠር መንግሥት እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑ ተነግሯል።
የመንግሥት ግልበጣው በማን እንደተሞከረ እስካሁን የተባለ ነገር የለም። በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ጉልህ ሚና ባላቸው ወታደራዊና ሲቪል አመራሮች መካከል በየወቅቱ አለመግባባትና ውጥረት በተደጋጋሚ ሲከሰት መቆቱ ይነገራል።
ከሲቪል አመራሮች መካከል ዋነኛ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ከአንድ ዓመት በፊት ካርቱም ውስጥ በመኪናቸው እተጓዙ ሳለ መንገድ ላይ በተጠመደ ፈንጂ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው እንደነበር ይታወሳል።
አገሪቱን ለረጅም ዓመታት በበላይነት የመሩት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ ሠራዊት፣ በሲቪሎች እና ተቃውሞውን በመሩት ቡድኖች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መደረጉ ይታወሳል።
በዚህም ሲቪሉን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን አብደላ ሐምዶክ ያዙ ሲሆን ከሠራዊቱ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር በመሆን አብዱል ፋታህ አልቡርሐን ከፍተኛውን ቦታ ይዘዋል።
የሱዳን መንግሥት ዜና ወኪል ሱና የአገሪቱን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጠቅሶ እንደዘገበው ከተሞከራው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆኑን አመልክቷል።
አል በባሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ሱዳን ውስጥ በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች እንደነበሩ ሪፖርት ተደርጓል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የደኅንነት ሁኔታ እየተዳከመ የመጣው ወታደራዊ መሪዎቹ ሥልጣን የሚያስረክቡበት ወቅት ለማስተጓጎል ነው ሲሉ ተቺዎች ይናገራሉ።
በሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው ኃያሉ የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ለሲቪሎች ሥልጣኑን በመጪው ኅዳር እንዲያስተላልፍ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለታል።












