ሱዳናውያን የሽግግር መንግሥቱ በሲቪሎች እንዲመራ አደባባይ ወጥተው ጠየቁ

ሱዳን ሰንደቅ አላማ

የፎቶው ባለመብት, EPA

በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በሲቪሎች የሚመራ ዴሞክራሲያው ሽግግር እንዲካሄድ በዋና ከተማዋ ካርቱም ድምጻቸውን አሰሙ።

ሰልፉ የተካሄደው ከሳምንት በፊት በአገሪቱ ተካሂዶ የከሸፈውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን ተከትሎ የአገሪቱን የሽግግር መንግሥት በሚመሩት ወታደራዊና ሲቪል ባለሥልጣንት መካከል ያለው ግንኙነት መሻከሩን ተክትሎ ነው።

የሱዳን የሠራተኞች ማኅበራትና የማኅበረሰብ አንቂዎች በጠሩት በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተሳታፊዎች አገሪቱን የሚመራ ከወታደራዊ ባለሥልጣንት ሙሉ ለሙሉ ነጻ የሆነ የሲቪሎች መንግሥት እንዲመሰረት ጠይቀዋል።

በሰልፉ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች የተሳተፉ ሲሆን ከዋና ከተማዋ ውጪ የሚኖሩ በርካታ ተቃዋሚዎችም በተጨናነቁ ባቡሮች ተሳፍረው ወደ ካርቱም በመምጣት በተቃውሞው ሰልፉ ላይ ተሳትፈዋል።

በአገሪቱ መንግሥት ውስጥ ያሉ የሲቪል በላሥልጣንት ከሰልፈኞቹ የቀረበውን ጥያቄ ደግፈውታል።

ከኦማር አልባሽር መውደቅ በኋላ የተቋቋመው የሽግግር መንግሥት በአገሪቱ ጦር ሠራዊት ከፍተኛ አመራሮች፣ በሲቪል ባለሥልጣንትና በተቃውሞ መሪዎች አማካይነት ሲሆን ምርጫ አስኪካሄድ ድረስ የሚቆይ ነው።

አገሪቱን ለረጅም ዓመታት በበላይነት የመሩት ኦማር ሐሰን አል ባሽር ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ከሁለት ዓመት በፊት በአገሪቱ ሠራዊት፣ በሲቪሎች እና ተቃውሞውን በመሩት ቡድኖች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መደረጉ ይታወሳል።

በዚህም ሲቪሉን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን አብደላ ሐምዶክ የያዙ ሲሆን ከሠራዊቱ በኩል ደግሞ የአገሪቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር በመሆን አብዱል ፋታህ አልቡርሐን ከፍተኛውን ቦታ ይዘዋል።

የሱዳን መንግሥት ዜና ወኪል ሱና የአገሪቱን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጠቅሶ እንደዘገበው ከተሞከራው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ በመንግሥት ቁጥጥር ስር መሆኑን አመልክቷል።

አል በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሱዳን ውስጥ በርካታ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች እንደነበሩ ሪፖርት ተደርጓል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ ያለው የደኅንነት ሁኔታ እየተዳከመ የመጣው ወታደራዊ መሪዎቹ ሥልጣን የሚያስረክቡበት ወቅት ለማስተጓጎል ነው ሲሉ ተቺዎች ይናገራሉ።

በሜጀር ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የሚመራው ኃያሉ የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ለሲቪሎች ሥልጣኑን በመጪው ኅዳር እንዲያስተላልፍ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለታል።