በሕዝብ እንደራሴው ሰር ዴቪድ አሜስ ግድያ የተጠረጠረው ግለሰብ ጉዳዩ በሽብር ድርጊት መያዙ ተነገረ

ሰር ዴቪድ አሜስ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, በስብሰባ ላይ ሳሉ በስለት ተወግተው ተገደሉት ሰር ዴቪድ

በዩናይትድ ኪንግደም በሕዝብ እንደራሴው ሰር ዴቪድ አሜስ ግድያን ተከትሎ በፖሊስ የተያዘው ግለሰብ አሊ ሃርቢ አሊ ጉዳይ በሽብር ድርጊት እየታየ መሆኑ ተገለጸ።

የ25 ዓመቱ ተጠርጣሪ በሽብርተኝነት ሕግ መሠረት በእስር ላይ ይገኛል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በግድያው የተጠረጠረውን ግለሰብ በተመለከተ ለአገሪቱ ፀረ-ሽብር አካል መረጃ የተሰጠ መሆኑን ኤምአይ5 የተባለው የአገሪቱ የደኅንንት መሥሪያ ቤት ግን በአሊ ላይ ክትትል እንዳላደረገበት ቢቢሲ ተረድቷል።

አንድ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ እንደገለጹት በቁጥጥር ስር የዋለው ሰው አሊ ሃርቢ አሊ እንደሚባል እና ሶማሊያዊ የዘር ሐረግ ያለው እንግሊዛዊ ዜጋ ነው።

አርብ ዕለት በኤሴክስ ውስጥ በሕዝብ እንደራሴው ግድያ ተጠርጥሮ የተያዘው ግለሰብ በሽብር ሕጉ መሠረት እንደገና ከታሰረ በኋላ ለንደን ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ስር ይገኛል።

ባለሥልጣናት በጥቃቱ ሌላ ተጨማሪ ሰው ተሳትፏል ብለው አያምኑም።

የግድያው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ እንዳመለከተው ለወንጀሉ እስላማዊ አክራሪነት ከጀርባው እንደሚኖር ማመልከቱን ፖሊስ አርብ ዕለት ገልጿል።

ወግ አጥባቂው ሰር ዴቪድ ከ1983 ጀምሮ ለሳውዝኤንድ የሕዝብ እንደራሴ ሲሆኑ በቤልፌየርስ ሜቶዲስት ቤተክርስቲያን ውስጥ መደበኛ የአርብ ስብሰባ ሲያካሂዱ ነበር በተደጋጋሚ በስለት የተወጉት።

በግድያው የተጠረጠረው አሊ ሰዎችን አክራሪ ከመሆን ለመከላከል በሚሰጠው 'ፕሪቨንት' በተባለው ፕሮግራም ውስጥ ብዙ ጊዜ እንዳልተሳተፈ ተነግሯል።

ይህ ፕሮግራም በማኅበራዊና በጤና ባለሙያዎች የሚታዘዝና በፈቃደኝነት የሚሳተፉበት ሲሆን ከተፈጸመ ወንጀል ጋር በተያያዘ ሚጣል ቅጣት አይደለም።

አሊ ግድያውን ከፈጸመ በኋላ መጀመሪያ በተጠርጣሪነት በኤሴክስ ተይዞ ነበር። ከዚያ በኋላ በሽብር ሕግ አንቀጽ 41 መሠረት ወደ ለንደን ተዛውሮ በእስር ላይ ይገኛል።

ቅዳሜ መርማሪዎች አሊ እስከ አርብ ጥቅምት 22 ድረስ በእስር ላይ እንዲያቆዩት በዳኞች ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

የሜትሮፖሊታን ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ለጥቃቱ የተጠቀመበት ስለት በቦታው መገኘቱን ገልጿል።

ፖሊሶች በለንደን አካባቢ ሦስት ቦታዎችን በፈተሽ ቅዳሜን አሳልፈዋል። የአስከሬን ምርመራም ቅዳሜ ዕለትም መደረጉን ፖሊስ አክሎ ገልጿል።

የሌበር ፓርቲው ሰር ኬይር እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ግድያው በተጸፈመበት ቦታ ተገኝተው ሐዘናቸውን ገልጸዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሌበር ፓርቲው ሰር ኬይር እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ግድያው በተጸፈመበት ቦታ ተገኝተው ሐዘናቸውን ገልጸዋል

ሰር ዴቪድ ባለትዳር፣ የአራት ሴት ልጆች እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ። የ69 ዓመቱን የሕዝብ እንደራሴን ለማሰብ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ቅዳሜ ምሽት ተካሂዷል።

በምሽቱ ዝግጅት ንግግር ያደረጉት የሳውዝኢንድ ምክር ቤት አባል አለን ውድ ሰር ዴቪድ "ጨዋ እና ታላቅ ሰው" ነበሩ ብለዋል።

ሰር ዴቪድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተገደሉ ሁለተኛው የሕዝብ እንደራሴ ናቸው። የሌበር ፓርቲው የሕዝብ እንደራሴ ጆ ኮክስ ከአራት ዓመት በፊት መግደላቸው ይታወሳል።

ጥቃቱ ማንም ሰው ሊሳተፍባቸው የሚችሉ ውይይቶችን ለሚያደርጉት የሕዝብ እንደራሴዎች ደኅንነትን አሳሳቢ አደርጎታል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፓቴል የሕዝብ እንደራሴዎችን ለመጠበቅ የደኅንነት እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል። የዕለት ከዕለት ተግባርና የዲሞክራሲ ባህል ሳይደናቀፉ እንደሚቀጥሉ አጥብቀው ተናግረዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ ከሌበር ፓርቲ መሪ ሰር ኬር ስታመር እና ከአፈ ጉባኤ ሰር ሊንሳይ ሆይል ጋር በመሆን ጥቃቱ በተፈጸመበት ጉብኝት አድርገው "እንቀጥላለን። እኛ ግልጽ በሆነ ማኅበረሰብ እና ዴሞክራሲ ውስጥ እንኖራለን" ብለዋል።

"በማንኛውም ግለሰብ ወይም ተነሳሽነት ልንገፋ አንችልም ... የመረጥነውን ዴሞክራሲ ላለማገልገል ምንም አያቆመንም" ብለዋል ፓቴል፤ ከመራጮች ጋር የፊት ለፊት ስብሰባዎች እንዲቀጥሉ ለማስቻል አስፈላጊው እንደሚደረግ ገልጸዋል።

እአአ በ2017 በዌስትሚኒስተር የሽብር ጥቃት ወቅት በስለት የተወጋ የፖሊስ መኮንን የረዱት ወግ አጥባቂ የሕዝብ እንደራሴ ቶቢያስ ኤልውድ የሕዝብ እንደራሴዎች ለጊዜው በስልክ ወይም በቪዲዮ ስብሰባ ሕዝቡን እንዲያነጋግሩ ሀሳብ አቅርበዋል።

የአሌበር ፓርቲ አባል የሆኑት ዳያን አቦት በስለት የመውጋት ጥቃትን ለማስወገድ ከወከላቸው ሕዝብ ጋር ከበቪዲዮ የስብሰባ ዘዴ ለመገናኘት እንደሚመርጡ ተናግረዋል።

የምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሰር ሊንድሳይ ሆይል የሕዝብ አንደራሴዎች ደኅንነትን የሚሻሻልበትን መንገዶች ለማግኘት ከአገር ውስጥ ጉዳይ መሥሪያ ቤትና ከፖሊስ ጋር "በፍጥነት" እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በሰው እጅ ህይወታቸው ለጠፋው ለሰር ዴቪድ ያላቸውን አክብሮት ፖለቲከኞች እና ከተለያዩ ወገኖች እየገለጹ ነው። የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ፓቴል ሰር ዴቪድን "የሚወደውን ሥራ በመስራት" የተገደለ "የሕዝብ ሰው" ብለው ገልጸዋቸዋል።

ፓቴል ጨምረውም "ዴቪድ ለሁሉም ሰው ይደርስ ነበር። በጣም የተወደደ የሕዝብ እንደራሴ ነበር። ለእኔ ውድ እና ታማኝ ጓደኛ ነበር። ለቤተሰቡም ታማኝ ባል እና አባትም ነበር" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦሪስ ጆንሰን ደግሞ "በፖለቲካ ውስጥ በጣም ደግ፣ ጥሩ እና ከጨዋ ሰዎች አንዱ ነበር" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።