የዩናይትድ ኪንግደም ምክር ቤት አባል በስለት ተወግተው ተገደሉ

ሰር ዴቪድ አሜስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወግ አጥባቂው የዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ አባል ሰር ዴቪድ አሜስ አርብ ዕለት በስለት ተወግተው ተገደሉ።

የምክር ቤት አባሉ ለንደን በሚገኘው ኢሴክስ የምርጫ ክልላቸው ውስጥ ነው ህይወታቸው ያለፈው።

ሊይ ኦን ሲ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከመራጮች ጋር በነበሩበት ወቅት በስለት ወግቷቸዋል በሚልም ፖሊስ አንድ የ25 አመት ወጣት ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር አውሏል።

የወጋበትን ስለት እንዳገኙና ከምክር ቤቱ አባል ግድያ ጋር በተያያዘ ሌላ ተጠርጣሪ እንደማይፈልጉ ፖሊሶች አስታውቀዋል።

የ69 ዓመቱ ሰር ዴቪድ ከአውሮፓውያኑ 1983 ጀምሮ በምክር ቤት አባልነት ያገለገሉ ባለትዳር እና የአምስት ልጆች አባት ነበሩ።

"ታላቅ ሰው፣ ታላቅ ጓደኛ እና ታላቅ የፓርላማ አባል፣ ዴሞክራሲያዊ ሚናውን ሲወጣ ተገድሏል" በማለት የጤና ሚኒስትሩ ሳጂድ ጃቪድ ሐዘናቸውን ገልፀዋል።

"ከሁሉ የከፋው የአመፅ ገጽታ ኢሰብአዊነት ነው። ከዓለም ደስታን ይሰርቃል እናም እኛ በጣም የምንወደውንም ሰው ከእኛ ወስዷል" በማለት ቻንስለር ሪሺ ሱናክ ተናግረዋል።

"ዛሬ አባት፣ ባል እና የተከበረ ባልደረባችንን ተነጠቅን። ለሚወዱት በሙሉ በጸሎት አስባቸዋለሁ። መፅናናትንም እመኛለሁ" በማለት አክለዋል።

የሳውዝ ኢንድ ዌስት ተወካይ የሆኑት ሰር ዴቪድ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በምርጫ ወረዳቸው የመረጧቸው አባላቶቻቸው አሳሳቢ የሚሏቸውን ጉዳዮች እንዲሁም ቃል የገቡትን ሁኔታ የሚያነሱበት ውይይት እያካሄዱ ነበር።

ውይይቱም እየተካሄደ የነበረው በሜቶዲስት ቤተክርስቲያን ነበር።

የኢሴክስ ፖሊስ እንደገለጸው አንድ ሰው በስለት ተወግቶ መጎዳቱ ሪፖርት የደረሰው በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር አርብ 6፡05 ነበር።

በስፍራው በአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ህክምና ቢደረግላቸውም ህይወታቸው ያለፈው ወዲያው ነው።

ሰር ዴቪድ በአውሮፓውያኑ 2016 የፓርላማ አባል ጆ ኮክስን ግድያ ተከትሎ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የተገደሉ ሁለተኛው የምክር ቤት አባል ናቸው።

ጆ ኮክሰን የምርጫ ውይይት ለማድረግ በምዕራብ ዮርክሻዮር ባቀኑበት ወቅት ነበር ከቤተ መጽሃፍት ውጪ የተገደሉት።