በዩናይትድ ኪንግደም ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂ ታዳጊዎች ራሳቸውን ማጥፋት የፈጠረው ጥያቄ

የፎቶው ባለመብት, Family photo
ሄኖክ ዛይድ ገብረሥላሴ በልጅነቱ ከትውልድ አገሩ ኤርትራ ሸሽቶ ለዓመታት በስደት ከኖረ በኋላ በእንግሊዝ ውስጥ የተሻለ ህይወት እኖራለሁ የሚል ተስፋን ሰንቆ ነበር።
ነገር ግን ያለመው ሳይሳካ በወጣትነቱ ተቀጨ። የ23 ዓመቱ ሄኖክ ዌስት ሚድላንድስ በሚገኝ ኮቨንትሪ በተባለ የአዕምሮ ጤና ተቋም ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል።
የራሱን ህይወት ሳያጠፋ እንዳልቀረ ተነግሯል። የሄኖክ ሞት ግን ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፤ ከበርካታ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ሞት አንዱ እንደሆነና ራሳቸውን የሚያጠፉ ጥገኝነት ጠያቂዎችም ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሆነ አንድ የበጎ አድራጎት ድርጅት አስታውቋል።
ሄኖክን ወንድሙ ተወልደ ሲገልፀው ደግ፣ ሩህሩህ፣ እግር ኳስ የሚወድ፣ የሰው ልጆችን ሳይለይ አፍቃሪ ነበር ይለዋል።
"አንድ ሰው በጭንቀት ውስጥ ከሆነ ወይም እርዳታ ከፈለገ ሳይጠየቅ ቀድሞ ማንንም የሚረዳ ነው" ይላል ተወልደ ዛይድ።
ሁልጊዜ መቀለድ የሚወደው ሄኖክ በጓደኞቹና በሌሎች በሚያውቁት ግለሰቦች ዘንድ በጣም ታማኝ እና መርህ ያለው ወጣት ነበር።
በኤርትራ ያለውን የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎትንና ጭቆናን ሸሽቶ ሄኖክ ከአገሩ የወጣው በ14 ዓመቱ ነበር። ከዚያም ወደ ሱዳን አቅንቶ በስደተኝነት ለጥቂት ዓመታት ኖሯል።
ነገር ግን ህልሙ ዩናይትድ ኪንግደም መድረስ ነበር። ቆራጥ የነበረው ሄኖክ በሰሃራ በረሃ እና በሊቢያ በኩል ብቻውን በመጓዝ የሜዲትራኒያን ባሕርን አቋርጦ ከሁለት ዓመት በፊት ኮቨንትሪ ሲደርስ እድሜው 21 ነበር።
"በዚያ ጉዞ ላይ ብዙ ስቃይ ቢያይም ተስፋ አልቆረጠም። አንድ ቀን ደኅንነቱ የተጠበቀ ማረፊያና አገር እንደሚያገኝ ሁልጊዜ ተስፋ ነበረው" ይላል ተወልደ።
ሄኖክ እንግሊዝ በደረሰበት ወቅትም በከፍተኛ ደስታ ተውጦ እንደደወለለትም ተወልደ ያስታውሳል።
"በርካታ መሰናክል ከተሞላበት ጉዞው በኋላ ለየት ያለ ተስፋ ነበረው" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Family photo
ልክ እንደ በርካታዎቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች በስቃይ የተሞላው የሄኖክ የስደተኝነት ጉዞ በአእምሮ ጤንነቱ ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስበት እንደሚችል የበጎ አድራጎት ሠራተኛ ቢኒ ሃንተር ይናገራሉ። ይባስ ብሎ የጥገኝነት ጥያቄውን ለማቅረብ የዩናይትድ ኪንግደም ሥርዓት ተደራራቢ መሆን በጣም ፈታኝ እንደሆነበትም ያምናሉ።
የአራት ወጣት ኤርትራውያን ሞትን ተከትሎ በኤርትራውያን የተቋቋመው 'ዳዕሮ' ለተባለ የወጣቶች ፕሮጀክት ነው ቢኒ ሃንተር የሚሰሩት።
"በርካታዎቹ አብረን የምንሰራቸው ወጣቶች ሁከት፣ መደፈር ወይም ከሞት አፋፍ ደርሰው የተመለሱ ናቸው" የሚሉት ቢኒ "ስደተኛ መሆን የራሱን ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ነው" ይላሉ።
"በሆቴል ተወስኖ፣ መስራት አለመቻል፣ በየሳምንቱ በሚሰጥ ትንሽ ገንዘብ መገደብ፤ ለብዙዎች በተለይም ብቻውን ለሆነና ለወጣቶች ከባድ ነው" ይላሉ።
በርካታ ጥገኝነት ጠያቂዎች አብዛኛውን ጊዜ ማኅበራዊ መገለል፣ መድልዎ አልፎ አልፎም ጥላቻ እንደሚገጥማቸውም ቢኒ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Da'aro Youth Project
"በዋነኝነት ትኩረት እንዲያገኝ የሞከርናቸው ጉዳዮች በጥገኝነት ጥየቃ ሥርዓት ሂደቱ ውስጥ በሚያልፉ ሰዎች ላይ በተለይም ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ላይ ነው" ይላሉ።
ከኤርትራ የመጡት እጅግ በጣም ብዙ ስደተኞች በዩናይትድ ኪንግደም የስደተኝነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ቢያገኝም አሁንም "በርካታዎቹ በጥገኝነት ጥያቄያቸው ላይ ውሳኔ ለማግኘት ረጅም ዓመታት ሲጠብቁ እናያለን" ብለዋል።
ሄኖክ የተሻለ ኑሮ ለመኖር በእንግሊዝ ውስጥ ጥገኝነት ጠይቆም እየተጠባበቀ እንደነበር ወንድሙ ተወልደ ይናገራል።
"የተቻለውን ሁሉ እየሞከረ ነበር። 'እኔ እራሴን የተሻለ ሰው አደርጋለሁ፣ ትምህርቴን ተከታትዬ በማንም ላይ ጥገኛ ሳልሆን ሥራ አገኛለሁ' እያለ ይነግረኝ ነበር" በማለት ተወልደ በሃዘን ያስረዳል።
ለመጨረሻ ጊዜ ከወንድሙ ጋር የተነጋገረው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ማብቂያ ላይ ነበር።
"ለረጅም ሰዓት በስልክ አወራን። በሱዳን የነበረኝን ሠርግ ፎቶዎችንም ለማየት ፈልጎ ነበር" ይላል ተወልደ የመጨረሻ የስልክ ንግግራቸውን ሲያስታውስ።
ነገር ግን ከስምንት ቀናት በኋላ ሄኖክ ኮቨንትሪ በሚገኘው ካሉዶን ማዕከል ውስጥ በአዋቂዎች የአእምሮ ጤና ተቋም ሞቶ ተገኘ። ራሱንም እንዳጠፋ ጥርጣሬ አለ።
"በችግሩ ወቅት የአእምሮ ጤና አገልግሎቶችን አግኝቶ ሊሆን ይችላል" የሚሉት ሃንተር ድርጅታቸው የጥገኝነት ሥርዓቱ በወጣቶች አእምሮ ውስጥ የሚያሳርፈውን ጫና ለማጉላት እየሠራ ነበር ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Handout
ተወልደ የሄኖክን ሞት አምኖ መቀበል ከባድ እንደነበር ይናገራል፤ አስከሬኑን ወደ ኤርትራ ለመውሰድም ጥረት እየተደረገ ሲሆን መዘግየቱም ቤተሰቡን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከትቶታል።
"ቀብሩ እስኪፈጸም ድረስ፣ የቅርብ ቤተሰቦቹ በሙሉ እርማችንን ልናወጣ አንችልም" ይላል።
"ወላጆቼ፣ ልጃቸውን በማጣታቸው ከፍተኛ ሐዘንና ስቃይ ላይ ናቸው። ነገር ግን ካልቀበሩና እርማቸውን ማውጣት ካልቻሉ ሐዘናቸው የከፋና የማይሽር ይሆናል" ይላል።
"ባለሥልጣናቱ የጠየቁትን ሁሉ አቅርበናል። ለምን እንዳወሳሰቡት አላውቅም፤ በተለይ ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ ለምን ይህንን ያህል ጊዜ እንደፈጀበት ስጋት አሳድሮብኛል። ባለሥልጣናቱ እኛን ያዩበት መንገድ አናዶኛል እንዲሁም አሳዝኖኛል" ብሏል።
የመባረር ፍርሃት
በበርሚንግሃም የሚኖር የ19 ዓመት አፍጋኒስታናዊ ከአገር እንዳይባረር በመፍራት በዚህ ዓመት ራሱን ያጠፋ ሲሆን፤ ከእርሱ በተጨማሪም በመባረር ፍራቻ በርካቶች ራሳቸውን ማጥፋታቸውን በመጥቀስ መንግሥት ፖሊሲውን እንዲቀይር ተማጽነው 46 ድርጅቶች ደብዳቤ ጽፈዋል።
ባለፈው ወር የአፍጋኒስታናዊውን ታዳጊ ሞት ምርመራ በተመለከተ በወጣው መረጃ መሰረት በዩናይትድ ኪንግደም የደረሰው የ13 ዓመት ታዳጊ እያለ ሲሆን ዕድሜው 18 ዓመት እስኪሞላ ድረስም በአከባቢው ባለሥልጣን እንክብባቤ እንዲቆይ ተወስኖ ነበር።
ታዳጊው በአገሪቱ ውስጥ ለመቆየት የተሰጠው ጊዜያዊ ፈቃድ ብቻ ሲሆን ወደ አፍጋኒስታን ይመልሱኛል የሚል ፍራቻ ነበረው።
በምርመራው ላይ የተገኙት ሃንተር እንደሚናገሩት እንደ ብዙዎቹ ጥገኝነት ጠያቂዎች ሞት ታዳጊው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የደረሰው ብቻውን ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Handout
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር የተደገረ ሌላ ምርመራ የ19 ዓመቱ ኤርትራዊ ሙሉብርሃን መድኃኔዓለም ፍሉዮስ በአውሮፓውያኑ 2019 ራሱን ማጥፋቱን ይፋ አድርጓል።
በበርካቶች ዘንድ ሙሉ በመባል የሚታወቀው ታዳጊ እንግሊዝ በደረሱ በ16 ወራቶች ጊዜ ውስጥ ከሞቱት አራት ኤርትራውያን ጓደኞች መካከል አንዱ መሆኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።
የአእምሮ ህመሙ አሳሳቢነት ሁኔታም አልታወቀም ነበር ሲል ምርመራው አጠቃሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የ18 ዓመቱ ፊልሞን የማነ በአውሮፓውያኑ 2017 እና ጓደኛው የ18 ዓመቱ አሌክሳንደር ተክሌ ደግሞ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሞተዋል።
የ19 ዓመቱ ኦስማን አህመድ ኑር በአውሮፓውያኑ 2018 በለንደን ከተማ ካምደን በሚባል ሰፈር ውስጥ ሞቶ ተገኘ።
ኦስማን ሁለቱ ጓደኞቹ ራሳቸውን በማጥፋታቸው ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶት ራሱን እንዳጠፋም ምርመራው አሳይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Da'aro Youth Project
ከአራቱ ሟቾች መካከል ሦስቱን ቤተሰቦች የወከሉት የሕግ ባለሙያዋ ኦሊቪያ አኔስ የወጣቶቹ ሞት አስደንጋጭ መሆኑን ገልጸዋል።
"ይህ ታዳጊዎቹ በዩኬ ውስጥ ስለሚሰጣቸው እንክብካቤ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ ጥያቄ የሚያጭር ነው። ከዚህም በተጨማሪም ምን ያህል ተጋላጭ እንደሆኑም በደንብ የሚያሳይ ነው" ይላሉ።
"እነዚህ ልጆች ጦርነትና ጭቆናን ሸሽተው ለተሻለ ህይወት እንግሊዝ የገቡና ጥገኝነት የሚፈልጉ ናቸው በእንግሊዝ መንግሥት ስር ሆነው ብዙዎቹ ለምን እየሞቱ እንደሆነ ማወቅ አለብን" ይላሉ።
አክለውም "በእነዚህ ታዳጊዎች ሞት ላይ ይፋዊ የሆነ የፍርድ ቤት ምርመራ መደረግ እንዳለበት ግልጽ ነው። በየቀኑ እርምጃ ካልተወሰደና በዘገየ ቁጥር የበለጠ አሳዛኝ ሞቶችንም ያስከትላል" በማለት ያስረዳሉ።
"ምን ያህል ታዳጊዎች እንደሞቱ አናውቅም። መንግሥትም መረጃው የለውም። ምን ያህል ወጣቶች እንደሞቱ እርግጠኛ ካልሆኑ ያለውን የስጋት ደረጃ እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ? ተጨማሪ ሞትንስ እንዴት መከላከል ይችላሉ?" በማለት ሃንተር ይጠይቃሉ።
በበጎ አድራጎት ድርጅቱ በተደረገው ምርመራ ባለፉት ዓመታት ከአስር በላይ የሚሆኑ ሞቶች ተመዝግበዋል ይህም "እንደ ብሔራዊ ሐዘን የሚቆጠር ነው።"
ምናልባትም ድርጅቱ ይፋ ያደረገው ጥቂቱን ሞት ነው ይላሉ ሃንተር።

የፎቶው ባለመብት, Handout
በጥገኝነት ሥርዓቱ ውስጥ ስለሞቱ ታዳጊዎች አስቸኳይ የሆነ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለቀረበው ጥያቄ መንግሥት እስካሁን ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም።
ነገር ግን ቃለ አቀባዩ በበኩላቸው "ተጋላጭ የሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን የመለየት እና በጤና እና በማኅበራዊ እንክብካቤ ፍላጎቶቻቸው የመደገፍ ኃላፊነት ያለው" ራሱን የቻለ ቡድን እንዳለው ተናግረዋል።
አክለውም ቃለ አቀባዩ "በዚህ ፈታኝ ወቅት ሃሳባችን እና ሐዘናችን ከአቶ ገብረስላሴ ቤተሰብ እና ጓደኞች ጋር ነው" ብለዋል።
የካልዶን ማዕከልን የሚያስተዳድረው ኮቨንትሪ እና ዋርዊርስሻየር ሽርክና ኤን ኤች ኤስ ትረስት በበኩሉ "በዚህ ዓመት መጀመሪያ በአንደኛው ታካሚያችን ላይ ለተከሰተው ክስተት ጥልቅ ሐዘናችንን ለመግለጽ እንወዳለን" ብለዋል።
ድርጅቱ አክሎም ሙሉ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል።
የሄኖክን አሟሟት በተመለከተ የሚደረገው ምርመራ እንደሚሰማ የኮቨንትሪ ኮሮነር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።








