በዓለም ዙሪያ ሚስቶች ከባሎች ያነሰ ገቢ እንደሚያገኙ ያውቃሉ?

አርማ የያዘች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሴቶች፣ ባለቤቶቻችሁ የሚያገኙትን ያህል ገቢ ታገኛላችሁ?

በባለትዳሮች መካከል ያለው የገቢ ልዩነት ላይ የተደረገ አዲስ ዓለም አቀፍ ጥናት እንዳመለከተው ለአብዛኛዎቹ ሴቶች መልሱ "አናገኝም" ነው።

ጥናቱ አራት አስርት ዓመታትን፣ ከአውሮፓውያኑ 1973 እስከ 2016ን በመሸፈን በ45 አገራትን ያለውን በደሞዝ ውስጥ በፆታዎች መካከል ያለውን አለመመጣጠን ዓለም አቀፋዊውን ገፅታ ዳሷል።

ይህ የዳሰሳ ጥናትም በቤትም ውስጥ ያለውን የገቢ አለመመጣን ዓለም አቀፋዊ በሆነ መልኩ ያሳየ ነው ተብሏል።

ተመራማሪዎቹ ፕሮፌሰር ሄማ ስዋሚናታን እና የሕንድ ፖሊሲ ማዕከልን የወከሉት ፕሮፌሰር ዴፓክ ማልጋን፣ የሕንድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በጥምረት በመሆን ባንጋሎር ውስጥ፣ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 65 ዓመት የተውጣጡ ባለትዳሮች እና ከ2.85 ሚሊዮን ቤተሰቦች የተገኙ መረጃዎችን ተጠቅመዋል።

መረጃው መንግሥታዊ ባልሆነውና ለትርፍ ባልቆመ ድርጅትና ሉክሰምበርግ ኢንካም ስተዲ (ኤልአይኤስ) የተሰበሰበ ነው።

"በተለመደው የድህነት እሳቤ ውስጥ ቤተሰብ ሲታይ እንደማይነጣጠል አንድ ነገር ነው" ይላሉ ፕሮፌሰር ስዋሚናታን።

"በተለይም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ገቢዎች ተሰብስበው በእኩል ይከፋፈላሉ የሚል ግምት አለ። ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ቤተሰብ በከፍተኛ ሁኔታ የገቢ አለመመጣጠን የሚታይበት ቦታ ነው። እንደሚታሰበው እኩልነት የለም እሱንም በተቻለ መጠን አፍታትተን ማሳየት ፈልገን ነበር" ይላሉ።

ሪፖርቱ ቤተሰብን ልክ እንደ አውሮፕላን ውስጥ የመረጃ ቋት "ጥቁር ሳጥን" ነው በማለት ይገልጸዋል የሚሉት ፕሮፌሰር ስዋሚናታን "ልክ እንደ ጥቁር ሳጥን ምስጢራዊ ነው። ውስጡ ካልታየና በደንብ ካልተፈተሸ ያለውንስ ነገር እንዴት መቀየር ይቻላል?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

ባለው የቅጥር ሁኔታ በሕንድ ውስጥ የጾታ አለመመጣጠን እንደሚኖር የታወቀ ነው። በአጠቃላይ በሠራተኛው ኃይል ውስጥ ጥቂት ሴቶች ሲኖሩ ቋሚ ሥራ የመሥራት ዕድላቸው አነስተኛ ነው።

ፕሮፌሰር ስዋሚናታን እና ማልጋን ከሕንድ ባለፈ ዓለም አቀፋዊ ገፅታውንም ለመገምገም ፍላጎት እንዳደረባቸው ያስረዳሉ።

"ለምሳሌ፣ የኖርዲክ አገሮችን በምንመለከትበት ወቅት ለሥርዓተ ፆታ እኩልነት የተስፋ ጮራን የፈነጠቁ ናቸው። ነገር ግን በነዚህ አገሮች ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? የሥራ ክፍፍሉና በቤት ውስጥ ያለው የሀብት መጠን እኩል ነው?" በማለት ፕሮፌሰር ስዋሚናታን ይጠይቃሉ።

ተመራማሪዎቹ አገሮቹን በአጠቃላይ በፆታዎች በኩል ባለው አለመመጣጠን እንዲሁም በቤተሰብ ውስጥ ያለውን አለመመጣጠን ደረጃ ሰጥተዋቸዋል።

የምርምር ውጤታቸውም እንደሚያሳየው በፆታዎች መካከል ያለው የገቢ አለመመጣጠን ሰለጠኑ ወይም ደሃ በሚባሉ አገራት፣ በሀብታም እና በደሃ ቤተሰቦች መካከል መኖሩን አይተዋል።

"የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያመለክተው ሁለቱም ባልና ሚስት ተቀጥረው በሚሠሩ ጊዜ ሚስቶች የባሎቻቸውን ያህል እኩል ገቢ የሚያገኙበት አንድም አገር የለም። ይህም በጣም ሀብታም ወይም ባደጉ በአንድም አገር እንኳን የለም" ይላሉ ፕሮፌሰር ማልጋን።

"በዓለም ላይ ጥሩ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ባላቸው ኖርዲክ አገሮች ውስጥ እንኳን የሴቶች ድርሻ ከ50 በመቶ በታች ሆኖ አግኝተነዋል" በማለትም ያክላሉ።

በፋብሪካ የምትሰራ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሴቶች ዝቅተኛ ገቢ ከሚያገኙባቸው ምክንያቶች መካከል አንዳንዶቹ ዓለም አቀፋዊ ናቸው።

ወንዶች በባህላዊ መንገድ የቀን ገቢ ማግኘት ያለባቸውና እንደ አስተዳዳሪ የሚቆጠሩ ሲሆን ሴቶች ደግሞ የቤቱን ሥራ ማጀት ውስጥ ማከናወን ድርሻቸው ተደርጎ ይታሰባል።

ብዙ ሴቶች ከወሊድ በኋላ እረፍት ይወስዳሉ፣ ሥራቸውንም ይተዋሉ። ከዚህም በተጨማሪ በበርካታ አገራት በፆታዎች መካከል ያለው ያልተመጣጠነ የደመወዝ ክፍያም ሌላኛው ምክንያት ነው።

ምንም እንኳን ሴቶችና ወንዶች ተመሳሳይ ሥራ ቢሰሩም በበርካታ አገራት እኩል ክፍያ ሳይሆን የሚከፈለው በተቃራኒው ሴቶች ያነሰ ይከፈላቸዋል። በሌላ መልኩ ደግሞ ክፍያ የማይከፈልበት የቤት ውስጥ ሥራ እና የልጆችና የቤተሰብ እንክብካቤ በዋናነት የሴቶች ኃላፊነት ተደርጎ ይታያል።

የዓለም አቀፉ የሠራተኛ ድርጅት በአውሮፓውያኑ 2018 ያለውን ያልተከፈለ ሥራ ገምግሞ ባጠናቀረው ሪፖርት መሰረት ከጠቅላላው ያልተከፈለ የቤት ውስጥና የእንክብካቤ ሥራ ከወንዶች በሦስት እጥፍ በልጦ 76.2 በመቶ ሴቶች የተከናወነ ሲሆን በእስያና በፓስፊክ አገራት ይህ አሃዝ ወደ 80 በመቶ ከፍ ይላል።

በሪፖርቱ መሰረት የማይከፈል የቤትና የቤተሰብ እንክብካቤ ሥራ ሴቶች ወደ ሥራው ዓለም እንዳይቀላቀሉና እንዳያድጉ ዋነኛው እንቅፋት እንደሆነ አፅንኦት ሰጥቷል።

የሴቶች ገቢ ዝቅተኛ መሆኑ ኢኮኖሚው ላይ ሊያደርሰው ከሚችለው ተፅዕኖ ባሻገር በእነሱም ላይ የኃይል ሚዛኑ እንዲለዋወጥና ውሳኔ የማይወስኑና በርካታ ነገሮች ከነሱ ቁጥጥር ውጭ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

"በቤት ውስጥ የሚያደርጉት የሴቶች አስተዋፅኦ የሚታይ አይደለም፤ ጥሬ ገንዘብ ግን የሚታይ ነው። ስለዚህ አንዲት ሴት ተቀጥራ በምትሰራበትና ደመወዝ አግኝታ ወደ ቤተሰቡ ገንዘብ በምታመጣበት ወቅት ከፍ ያለ ደረጃ ታገኛለች። በቤት ውስጥ የውሳኔ ሰጭነትዋም ሆነ ድምፅዋ የመሰማቱ ሁኔታ ከፍ ይላል" በማለት ፕሮፌሰር ስዋሚናታን ያስረዳሉ።

"የሴቶች ገቢ መጨመር የድርድር ኃይላቸውንም ያሳድጋል። በተለይም የቤት ውስጥ ጥቃት ባለበት ሁኔታም ቶሎ ለመውጣት እንዲችሉና በራሳቸው እንዲቆሙ ይረዳቸዋል" ይላሉ።

ዳቦ የምትጋግር ግለሰብ

የጡረታ ፖሊሲዎች ከገቢዎች ጋር በከፍተኛ ሁኔታ የተሳሰሩ በመሆናቸው ሴቶች እድሜያቸው በሚገፋበት ወቅት ዝቅተኛ ቁጠባ እና ሀብት የማያፈሩበት ዋነኛ ምክንያት በወጣትነታቸው ከሚያገኙት የገቢ ልዩነት ተፅእኖ ጋር የተያያዘ ነው።

ሆኖም በሪፖርቱ ውስጥ አንድ የታየው ለየት ያለ ጉዳይ ከ1973 እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ የቤት ውስጥ የደመወዝ አለመመጣጠን 20 በመቶ መቀነሱን ተመራማሪዎቹ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ያደረጉትን ጥናት ዋቢ አድርገው አካትተዋል።

"በአብዛኞቹ የዓለም ክፍሎች የኢኮኖሚ ልማት እና እድገት ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የሴቶች በሥራው ዓለም የመቀጠር ተሳትፎ ጨምሯል" የሚሉት ፕሮፌሰር ስዋሚናታን "በብዙ የዓለም ክፍሎች ለሴቶች ተስማሚ የሆኑ ፖሊሲዎች መምጣታቸው ያለውን ክፍተት አጥብቦታል። ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ ለማግኘት የተደረጉ ዘመቻዎችም የደመወዙን ክፍተት እንዲቀንስ አድርጎታል" ይላሉ።

ነገር ግን ያለው የደመወዝ አለመመጣጠን በተወሰነ ቢቀንስም ያሉት ክፍተቶች አሁንም ጉልህ እንደሆኑና ልዩነቱን ለማጥበብ መሰራት አለበት ብለዋል።

"መንግሥታት ልዩነቱን ለማጥበብ እየሰሩ አይደለም። ኩባንያዎች የእንክብካቤ ሥራን እና ያልተከፈለ የቤት ሥራን የሚሰሩ ሴቶች ቅጣት በሚመስል ሁኔታ እየመለመሉ አይደለም። ስለዚህ እኛ መጠየቅ ያለብን የሴቶች ሥራ እውቅና ተሰጥቶታል? ለቤተሰብ ተስማሚ እና ለልጆች ተስማሚ ፖሊሲዎች አሉን? እንዲሁም ያልተከፈለባቸው የቤት ውስጥ ሥራዎችን ሸክም የሚካፈሉ ወንዶች በተሻለ ሁኔታ ማሳደግ አለብን።"

"መንግሥታት እና ማኅበረሰቦች ሊያደርጉ የሚችሏቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እንደዚህ መሆን የለበትም" ይላሉ።