ሳምራዊት ፍቅሩ፡ የራይድ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸለመች

ሳምራዊት ፍቅሩ፣ የራይድ መስራችና ስራ አስኪያጅ

የፎቶው ባለመብት, Samrawit

የሃይብሪድ ዲዛይንስ ኤንድ ራይድ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ሳምራዊት ፍቅሩ የአፍሪካዊ ቢዝነስ ባለ ራዕይ ሽልማት አሸናፊ ሆናለች።

በየዓመቱ የሚዘጋጀው የአፍሪካ ኦፕን ቢዝነስ አዋርድ ሳምራዊት ፍቅሩን ለበርካቶች የሥራ እድል በመፍጠር ምርጥ አፍሪካዊ የቢዝነስ ባለ ራዕይ (Best African Business Visionary) ብሎ የ2021 ተሸላሚ አድርጓታል።

ይህ ሽልማት የተዘጋጀው መንግሥታዊ ባልሆነው፣ የአፍሪካ ሬናይሰንስ ኤንድ ዲያስፖራ አሶሲዬሽን (African Renaissance And Diaspora Network) መሆኑን ሳምራዊት ለቢቢሲ ተናግራለች።

ድርጅቱ ከየአህጉሩ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ግለሰቦችን በመምረጥ አወዳድሮ ተሸላሚ ያደርጋል።

አፍሪካ ኦፕን ቢዝነስ አዋርድ በየዓመቱ በኒው ዮርክ የሚዘጋጅ ሲሆን ውድድሩ የሚካሄደው በግለሰቡ ማንነት፣ የፈጠራ ሥራው በማኅበረሰቡ ውስጥ ባበረከተው አስተዋጽኦና በፈጠረው ተጽዕኖ፣ የፈጠረው የሥራ እድል በመስፈርት ታይቶ ነው።

ድርጅቱ በየዓመቱ ዲያስፖራ ሆኑም አልሆኑ በቢዝነስ እና በፖለቲካ ለአገራቸው ብሎም ለማኅበረሰቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የፈጠሩ ሰዎችን በመምረጥ እንደሚሸልሙ ትናገራለች።

በዚህ ዓመት ከአፍሪካ ለሽልማት የተመረጠው ቢዝነስ ራይድ ብቻ መሆኑን የምትናገረው ሳምራዊት፤ ነገር ግን በጤናው እና በፖለቲካው ዘርፍ ተመርጠው የተሸለሙ ግለሰቦች መኖራቸውን ታስታውሳለች።

በቴክኖሎጂ እና በአገልግሎት ዘርፍ የራይድ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ተሸላሚ ሆናለች።

ሳምራዊት ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ የተለያዩ ሽልማቶችን ብታገኝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስትሸለም ይህ የመጀመሪያዋ ነው።

"ራይድ" የጥሪና የአፕልኬሽን የትራንስፖርት አገልግሎት ምስረታ

"ራይድ የተነሳው ከችግር ነው" ትላለች ሳምራዊት ስለ ድርጅቷ ስታስረዳ።

ከዚህ ሁሉ በፊት ግን ሳምራዊት ለሌሎች ተቀጥራ የምትሰራ የወር ደሞዝተኛ ነበረች። ሕልም እንጂ ገንዘብ አልነበራትም። ለኢትዮጵያ ቢዝነስም ሆነ ለሥራው ዓለም እድሜዋ ገና ለጋ ነበር።

በራሷ አንደበት "በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር የምገኘው" ትላለች።

ዛሬ 'ራይድ' በማንኛውም የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊ አንደበት ላይ የሚመላለስ ስም ሆኗል።

ሳምራዊት ይህንን ድርጅት ለመመስረት ደሞዟን አጠራቅማ መጀመሯን ለቢቢሲ ተናግራለች።

በሙያዋ የኮምፒዩተር ፕሮግራመር ናት። ተቀጥራ ትሰራ በነበረችበት ጊዜ የራሷን ቢዝነስ ለመጀመር በማሰብ ከምታገኘው ደመወዝ ላይ መቆጠብ ጀመረች።

የቆጠበችው ገንዘብ 40 ሺህ ብር ደረሰላት።

በወቅቱ ከደሞዟ 40 ሺህ ብር ማጠራቀም የቻለችው ሳምራዊት፣ "የሕብረተሰቡን ችግር የሚፈታ" ነገር ለመስራት ወሰነች።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቴክኖሎጂ መፍታት የዘወትር ሕልሟ ነው።

በወቅቱ 22 ዓመቷ የነበረው ሳምራዊት ሁለት የፕሮጀክት ሃሳብ ሰርታ ብታቀርብም ለፍሬ አለመብቃታቸውን ትናገራለች።

የባለሃብቶችን ቀልብ ያልሳቡት የሳምራዊት ፕሮጀክቶች የአጭር መልዕከት የሎተሪ ሲስተም እና የጥገና ታሪክን መዝግቦ የሚይዝ እና የሚያስታውስ ሲስተም እንደነበሩ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ተናግራለች።

እነዚህ ሥራዎች ለምን ወደ ተጠቃሚ ጋር አልደረሱም ለሚለው ጥያቄ ሳምራዊት ስትመልስ "በፖሊሲ እንዲሁም በፋይናንስ ችግር ሳይለቀቁ ቀርተዋል" አጭር መልሷ ነው።

ከዚህ በመቀጠል አንድን የማኅበረሰብ ችግር ለመፍታት ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚለውን አቋሟን ለሦስተኛ ጊዜ ፈተነችው።

በወቅቱ ለብቻዋ ትሰራ እንደነበር የምታስታውሰው ሳምራዊት መተግበሪያዎችን በመሥራት፣ የሽያጭ ሠራተኛ በመሆን እንዲሁም የሒሳብ ሥራውን ብቻዋን ታከናውን ነበር።

አንድ ሆና እንደ ብዙ ስትሰራ ማለዳ 12 ሰዓት ከቤቷ ወጥታ እስከ ምሽቱ 6 እና 7 ሰዓት ድረስ ቢሮዋ ትቆይ ነበር።

ከውድቅት ሌሊት በኋላ ወደ ቤቷ ለመግባት የምትጠቀማቸውን የኮንትራት ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ሁኔታ የደኅንነት ስጋት ውስጥ ይከትቷት እንደነበር ታስታውሳለች።

አንድ አደጋ ቢደርስባት ቤተሰቦቿ የነበረችበትን እና ያለችበትን ስፍራ የሚያውቁበት ቴክኖሎጂ አለመኖሩን ያስተዋለችው ሳምራዊት ይህንን አገልግሎት የመጀመር ሃሳብ በአእምሮዋ ተፀነሰ።

ሳምራዊት ያስተዋለችውን ችግር ለበርካታ ሰዎች ስታካፍል፣ 'ማታ አምሽተን አንሰራም ስንት ችግር ያጋጥመናል' የሚል መልስ አገኘች።

እነዚህ ግለሰቦች ካለባቸው የደኅንነት ስጋት የተነሳ ቢሯቸው መጨረስ ያልቻሉትን ሥራ ወደ ቤታቸው ይዘው በመሄድ እንደሚሰሩ እንደነገሯት ታስታውሳለች።

ከዚህ በኋላ አገልግሎት ሰጪው እንዲሁም አቅራቢው በሚገባ በሲስተም ውስጥ ተመዝግበው ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ቢያንቀሳቅሳችሁ ፈቃደኛ ትሆናላችሁ? የሚል ጥያቄ አቅርባለች።

በወቅቱ የሳምራዊት ጥያቄ የቀረበላቸው ሰዎች ፈቃደኝነታቸውን በደስታ ገለፁ።

ከዚህ በኋላ "ራይድ" የተሰኘውን ታክሲና ተሳፋሪን በቴክኖሎጂ የማገናኘት ፕሮጀክት ቀረፀች።

ስትጀምረው ብቻዋን በ40 ሺህ ብር ካፒታል የነበረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ግን ስድስት የአክሲዮን አባላትን በባለድርሻነት ይዞ ካፒታሉን ወደ ሚሊዮኖች አሳድጓል።

ሲስተሙን ለመሥራት አራት ወር እንደወሰደባት የምትናገረው ሳምራዊት በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ስማርት ስልኮችን የሚጠቀሙ ግለሰቦች ቁጥር አነስተኛ እንደነበር፣ ኢንተርኔቱም ጠንካራ ስላልነበር አጭር መልዕክት በመላክ አገልግሎት መስጠት መጀመሯን ታስታውሳለች።

ይህ የአጭር መልዕከት ሲስተም ወደ ሥራ ከገባ በኋላ በሬዲዮ ማስታወቂያው ሲነገር ሰዎች "ልክ እንደ ኡበር ሲሉ ሰማሁ" ትላለች።

ያኔ ኡበር ምንድን ነው በሚል ወደ ጉግል ጎራ በማለት ተመለከተች።

ዓለም ላይ ኡበር የሚባል የታክሲ አገልግሎት መኖሩን አታውቂም ነበር? የቢቢሲ ጥያቄ ነው።

"ምንም እውቀቱ አልነበረኝም፤ ራይድ ከተወለደ በኋላ እንደ ኡበር ማለት ነው ሲሉ ስለ ኡበር በብዛት እያነበብኩ መጣሁ።"

ከዚህ በኋላ የኢንተርኔት አገልግሎት እየተስፋፋ እንዲሁም የስማርት ስልኮች ተጠቃሚ ሲጨምር በኢንተርኔት አፕሊኬሽን መቀየር አለበት በሚል የራይድ መተግበሪያን ሰራች።

ሳምራዊት ፍቅሩ፣ የራይድ መስራችና ስራ አስኪያጅ

የፎቶው ባለመብት, Samrawit

ራይድ የታክሲ አገልግሎት

ሳምራዊት የራይድ የትራንስፖርት አገልግሎትን ስትጀምር አርዓያ አድርጋ ልትከተለው የምትችለው ሰው በአድማሷ ላይ አልነበረም። ስለዚህ ራሷን አርዓያ አድርጋ ለመቅረጽ መጣሯን በተደጋጋሚ ስትናገር ይደመጣል።

ይህ ህልሟ የተሳካላት ይመስላል፤ ራይድ ወደ ሥራ ከገባ ስምንት ዓመት ሊሞላው የወራት እድሜ ቀርተውታል።

በ2013 ዓ. ም የበጀት ዓመት በአጠቃላይ አሽከርካሪዎቹን ጨምሮ ከ347 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር አስገብታለች።

ራይድ በስሩ 37 ሺህ አሽከርካሪዎችን የሥራ አጋር አድርጎ እየሰራ ነው።

ራይድ ከመምጣቱ በፊት በትራንስፖርቱ ዘርፍ ብዙ ሴቶች እንዳልነበሩ የምትናገረው ሳምራዊት፣ ራይድ ውስጥ ብቻ በአሁኑ ሰዓት በአሽከርካሪነት 400 ሴቶች ይሰራሉ ትላለች።

ወደ 7000 የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ መኪናቸውን አሽከርካሪ በመቅጠር ያሰራሉ። በድርጅቱ ውስጥ በቋሚነት ተቀጥረው የሚሰሩ 500 ሠራተኞችም አሉ።

ይህ በአዲስ አበባ ብቻ ሲሆን ድርጅቱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለመሰማራት ካለው ፍላጎት አንጻር ይህ ቁጥር ሊያድግ እንደሚችል ሳምራዊት ትናገራለች።

ራይድ በመጪዎቹ ዓመታት ውስጥ ቢያንስ በአምስት የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ [ሐዋሳ፣ ጎንደር፣ አዳማ እና ባሕርዳር] አገልግሎቱን ለማዳረስ እቅድ ይዟል።

ድርጅቱ አገልግሎት ሲሰጥ የሚኖሩ ቅሬታዎችን ለመፍታት ሁለት የአገልግሎት ቢሮዎችን በመክፈት ያስተናግዳል።

ይህንን ለመፍታት ሲባል የተቋቋመው ክፍልም ጉዳዩን በማየት ለችግሮቹ መፍትሄ ለመስጠት እንደሚሰራ ታስረዳለች።

ደንበኞች ቅሬታቸውን በኢሜል ለቢሯቸውም ቢያሳውቁ ጉዳያቸውን ቢሯቸው እንደሚከታተለው ጨምራ ገልጻለች።

ሳምራዊት ፍቅሩ፣ የራይድ መስራችና ስራ አስኪያጅ

የፎቶው ባለመብት, Samrawit

ተግዳሮቶች

"ራይድን ስንጀምረው የት እንደሚደርስ ብናውቅም እንኳ ኢንቨስትመንት ማግኘት በጣም ከባድ ነበር" ትላለች ሳምራዊት።

ለሳምራዊት በዚህ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ሰዎችን አሳምኖ ሃብታቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ማድረግ ከባድ ነበር።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአጭር ጊዜ ትርፍ የሚገኝባቸው የንግድ ሃሳቦች በርካታ መሆናቸውን የምትጠቅሰው ሳምራዊት፤ በርካታ ሰዎች በቴክኖሎጂ ዘርፍ ላይ ገንዘባቸውን ከማዋል ይልቅ በቀላሉ ሪል ስቴት እና ግብርና የመሳሰሉ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ትርፋማ መሆን እንደሚችሉ ይነግሯት ነበር።

የራይድን አገልግሎት ከጀመረች በኋላ በሬዲዮ ማስታወቂያ ለማስነገር እንኳ ውድ ሆኖ ወጪው እጅጉን ፈታኝ እንደነበር ታስታውሳለች።

ይህንን ተግዳሮት "እንደምንም አለፍነው" የምትለው ሳምራዊት፣ አሽከርካሪዎቹን የቴክኖሎጂውን ጥቅም ለማስረዳት እና ወደ ሥራ ለማስገባት፣ የነበረውን የሥራ ባህል በአዲስ ለመቀየር አንድ ዓመት ያህል ጊዜ እንደፈጀባቸው ተናግራለች።

"አንድ ዓመት ሙሉ በነጻ በጣም ለፍተናል።"

ከዚህ በኋላ ራይድ ተቀባይነት እያገኘ እና በርካታ ደንበኞችን እያፈራ ሲመጣ መንግሥት የምቆጣጠርበት ሥርዓት የለም በሚል ክልከላዎች ማድረጉን ታስታውሳለች።

ከመንግሥት ጋራ ሦስት ዓመት የፈጀ የፍርድ ቤት ክርክር በማድረግ ጉዳዩ በራይድ አሸናፊነት እልባት አግኝቷል።

ለሳምራዊት ያቀረብነው የመጨረሻ ጥያቄ አሁን ቢሊየነር ወይንም ሚሊየነር አልሆንሽም?

(ፈገግታ) በግል ሳይሆን በድርጅት ጥሩ እየሰራን ነው።

በግልስ ሃብት አላፈራሽም?

እርሱ ፐርሰናል ነው ይፋ ማድረግ አልችልም። (ፈገግታ)

ሳምራዊት የወጣችውን አቀበት የወረደችበትን ቁልቁለት መለስ ብላ በማየት ሽልማቱን በተቀበለችበት ወቅት በዙም በተላለፈ መልዕክቷ ለወጣት ሥራ ፈጣሪዎች "ምን ጊዜም የሚገጥማችሁ ተግዳሮት ላይ ሳይሆን ራዕያችሁ ላይ አተኩሩ" ስትል ምክሯን አስተላልፋለች።