የአውስትራሊያ ፖሊስ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ዕፅ ያዘ

በአውስትራሊያ ፖሊስ ከተያዘው ሄሮይን ዕፅ በከፊል

የፎቶው ባለመብት, AUSTRALIAN FEDERAL POLICE

የምስሉ መግለጫ, በአውስትራሊያ ፖሊስ ከተያዘው ሄሮይን ዕፅ በከፊል

የአውስትራሊያ ፖሊስ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ መጠን ያለውን ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ ሄሮይን የተባለ አደንዛዥ ዕፅ መያዙን አስታወቀ።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት እንዳሉት 104 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣውና 450 ኪሎ ግራም የሚመዝነው በ1,290 ለየት ባሉ ቀይ አሽጎች የተዘጋጀ የዕፅ ጭነት ነው።

ይህ የሄሮይን ዕፅ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ወደቦች ሁሉ ትልቁ በሆነው በሜልበርን ወደብ በኩል ሊገባ ሲል ነው ተብሏል።

ፖሊስ በአንድ ሴራሚክ በተጫነበት ኮንቴይነር ውስጥ የሄሮይን ዕፁን ማግኘቱን ተከትሎ አንድ የማሌዢያ ዜግነት ያለውን ግለሰብ ይዟል።

ተከትሎም ግለሰቡ ከፍተኛ መጠን ያለው ለንግድ የሚውል ዕፅ ወደ አውስትራሊያ ግዛት ለማስገባት ይዞ በመገኘቱ ክስ ተመስርቶበታል። ተጠርጣሪው ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ አስከ እድሜ ልክ አስራት የሚደረስ ቅጣት ሊጣልበት ይችላል።

በተያዙት እሽጎች ላይ ፖሊስ ባካሄደው ምርመራ በውስጣቸው ሄሮይን የተባለው ዕፅ መያዛቸውን አረጋግጧል።

የዕፅ ጭነቱ ከማሌዢያ የተነሳ መሆኑንና ሜልበርን ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ለሽያጭ ሊቀርብ ታስቦ እንደነበርም ተገልጿል። ይህንንም ተከትሎ በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ ፖሊስ ፍተሻ አድርጓል።

የአውስትራሊያ ፌደራል ፖሊስ ባለሥልጣን የሆኑት ክሪሲ ባሬት እንደተናገሩት ይህን ከፍተኛ መጠን ያለውን ዕፅ በቁጥጥር ስር ለማዋል ከማሌዢያ የፖሊስ ኃይል ጋር በትብብር መሥራታቸውን ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ ጨምረውም በቁጥጥር ስር ውሎ ከአውስትራሊያ የዕፅ ዝውውር ውስጥ እንዲወጣ ከተደረገው በእያንዳንዱ ሁለት ኪሎ ግራም የአንድ ሰው ህይወት ለማዳን እንደሚቻልና በአጠቃላይ በዕፁ ምክንያት ሊጠፋ ይችል ከነበረው የ225 ሰዎች ህይወት ይተርፋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በተመሳሳይ የአውስትራሊያ ባለሥልጣናት ከፍተኛ መጠን ያለው የተከለከለ ዕፅ በቁጥጥር ስር አውለው ነበር።