አደንዛዥ እፅ፡ በ'ቢሊዮኖች ዩሮ' የተገመተ ኮኬይን በጀርመንና ቤልጂየም ወደብ ተያዘ

ኮኬይን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በጀርመን የተገኘው ኮኬይን ከ1 ሺህ በላይ ጣሳዎች ውስጥ ተደብቆ ነበር

የጀርመንና የቤልጂየም ጉምሩክ ባለሥልጣናት ከ23 ቶን በላይ የኮኬይን እፅ መያዛቸው ተገለፀ።

በመጠኑ ከዚህ በፊት አጋጥሞ የማያውቅ ነው የተባለው ኮኬይን፤ መዳረሻው ኔዘርላንድስ እንደነበር ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የጀርመን ባለሥልጣናት ከፓራጓይ በአምስት የማጓጓዣ ኮንቴይነር የተጫነ 16 ቶን ኮኬይን በሃምበርግ ወደብ ላይ በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

የኔዘርላንድስ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማም በአንትወርፕ የቤልጂየም ወደብ ተጨማሪ 7.2 ቶን ኮኬይን ተይዟል።

የጀርመን ባለሥልጣናት የኮኬይን እፁ በ'ቢሊየኖች ዩሮ' ዋጋ እንደሚገመት ተናግረዋል።

እፁን በማዘዋወር የተጠረጠረው የ28 ዓመት ወጣት በኔዘርላንድስ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የደች ፖሊስ ረቡዕ እለት አስታውቋል።

ኮኬይን የያዘ ጣሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የጉምሩክ ባለሥልጣናት እንዳሉት የተያዘው ኮኬይን በመንገድ ላይ ዋጋ በቢሊየኖች ዩሮ ይገመታል።

የጉምሩክ በላሥልጣናት እንዳሉት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተካሄዱ ሁለት ፍተሻዎች 'እጅግ ብዙ መጠን' ያለው የኮኬይን እፅ ለመያዝ ምክንያት ሆኗል።

እፁ በቤልጂየም አንትወርፕ ወደብ የተያዘው ከፓናማ እንጨት በተሰራ ሳጥን ተሞልቶ በኮንቴኔር ውስጥ ተደብቆ ነው።

ከዚህ ቀደም ከፓራጓይ ወደ አውሮፓ ገብቶ የነበረውና በሰሜናዊ የጀርመን ከተማ ሃምበርግ የተያዘው ኮኬይን ደግሞ በቆርቆሮ ጣሳ ተሞልቶ ነበር የተገኘው።

የጉምሩክ ባለሥልጣናቱ ከፓራጓይ የገባውን ኮንቴነር በጥብቅ ለመፈተሽ የወሰኑትም በጭነቱ ላይ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮችን ካስተዋሉ በኋላ ነበር።

"በኮኬይኑ የተሞሉት የቆርቆሮ ጣሳዎች ከኮንቴነሩ በር ጀርባ ከተጫኑ ሌሎች እቃዎች መሃል ተሰግስገው ነበር" ብለዋል ባለሥልጣናቱ።

መርማሪዎች ኮንቴኔሮቹ ላይ ባደረጉት ፍተሻም ከ1ሺህ 700 በላይ ጣሳዎች ውስጥ የታሸገ የኮኬይን እፅ ማግኘት ችለው ነበር።

የጀርመን ጉምሩክ እንዳለው ይህ እስካሁን በአውሮፓ ከተያዘው እፅ በጣም ከፍተኛው ሲሆን በዓለም ደረጃም በአንድ ጊዜ የተያዘ ከፍተኛ መጠን ያለው እፅ ነው።

የሀምበርግ ጉምሩክ ባለሥልጣን ሬኔ ማትሽክ ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት 16 ቶን የሚመዝነው እፅ ከ1.5 ቢሊየን እስከ 3.5 ቢሊየን ዩሮ ይገመታል።

ሃምበርግ ወደብ በትልቅነቱ ከአውሮፓ ሦስተኛው ሲሆን በጀርመን ደግሞ በጣም ትልቁ ነው።

ፓራጓይ ለዓመታት ቁልፍ የእፅ ማሸጋገሪያ አገር ሆናለች።

ከጎረቤት አገር ብራዚል አደገኛ እፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች ወደ ፓራጓይ በመሻገር በርካታ የእፅ ዝውውር ተግባራትን ያከናውናሉ።

እፁም በአብዛኛው ከፓራጓይ በኮንቴነር ተጭኖ ወደ አውሮፓ የወደብ ከተሞች ይወሰዳል።

ጥቅምት ወር ላይ ከደቡብ አሜሪካ የመጣ 11 ቶን ኮኬይን በአንትወርፕ ወደብ ተይዟል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ነሐሴ ወር ላይ ደግሞ፤ በሃምበርግ ወደብ ቦሎቄ ነው በሚል ወደ አውሮፓ ሊገባ የነበረ 4.5 ቶን ኮኬይን በጉምሩክ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር ውሏል። በወቅቱ ይህ ኮኬይን ከፍተኛ ጥራት ያለው በመሆኑ 1 ቢሊየን ዩሮ ዋጋ እንደሚያወጣ ተገልጾ ነበር።

ከፍተኛ ጥራት ያለው ኮኬይን ዋጋን ለመጨመር፤ እፁን በመቆራረጥና ከሌላ እፅ ጋር በመደባለቅ በመንገድ ላይ ይሸጣል።

ባለፈው ዓመትም 102 ቶን ኮኬይን ወደ አውሮፓ ሊገባ ሲል መያዙ ይታወሳል።