ፓራጉዋይ፡ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኮኬይን በከሰል ጭነት ውስጥ ተደብቆ ተገኘ

በከሰል ውስጥ ተደብቆ የተገኘው ኮኬይን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በፓራጉዋይ 23 ኩንታል ኮኬይን በከሰል ጭነት ውስጥ ተደብቆ ተገኘ።

ጭነቱ ወደ እስራኤል እየተጓዘ እንደነበር ፖሊስ የገለፀ ሲሆን 500 ሚሊዮን ዶላርም ያወጣል ተብሏል።

በደቡብ አሜሪካዋ ፓራጉዋይ የተያዘ ትልቁ አደንዛዥ የእፅ ዝውውርም ክምችትም መሆኑ ተገልጿል።

የኮኬይኑ ክምችት የተገኘው በመዲናዋ አስዩኒኮን አቅራቢያ በምትገኘኝ ቪሌታ ከተማ በሚገኝ የግል ወደብ ውስጥ ባለ መጋዘን ነው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ሁለት ሰዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን አንደኛው ግለሰብ የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ የቀድሞ ዳይሬክተር ነው።

ኮኬይኑ ተጠቅልሎ በአንደኛው መጋዘን ውስጥ በከሰሎች መካከል የተገኘ ሲሆን ቀሪ አምስት መጋዘኖችም እንደሚፈተሹ ፖሊስ አስታውቋል።

የአገር ውስጥ ሚኒስትር ኡስሊደስ አክቬዶ እንዳሉት በአጠቃላይ የኮኬይን መጠኑም ወደ 30 ኩንታል ሊሆን እንደሚችልም አመላክተዋል።

በከሰል ውስጥ ተደብቆ የተገኘው ኮኬይን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በላቲን አሜሪካ አገራት መካከል ወደ ውጪ ከሚላኩ ምርቶች መካከል ዋነኛ የሆነው የከሰል ምርት በአለም አቀፍ ድንበሮች ላይ ኮኬይንን ለማዘዋወር ሽፋንም ሆኖ በማገልገል ላይ ነው።

የምርቱ የመጨረሻ መዳረሻ እስራኤል ቢሆንም በመካከል ግን በአርጀንቲናዋ መዲና ቦነስ አይረስና በቤልጂየሟ ከተማ አንትወርፕ ለማቆም እቅድ ይዞ የነበረ መሆኑን ሚኒስትሩ ኡስለደስ አስታውቀዋል።

ጭነቱን በተመለከተ ከቤልጂየም ጥቆማ እንደደረሰውም የፓራጉዋይ ፖሊስ አስታውቋል።

ኮኬይኑ ከቦሊቪያ በአውሮፕላን ተጭኖ ሳይመጣ እንዳልቀረ የፓራጉዋይ ፀረ-አደንዛዥ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ቦሊቪያ በአለም ላይ ሶስተኛ አደንዛዥ እፅ አምራች አገር ናት።

ፓራጉዋይ በአመታትም ውስጥ ቁልፍ የአደንዛዥ እፅ መሻገገሪያ ሆና ቆይታለች።

ለምሳሌም ያህል የብራዚሉ ፈርስት ካፒታል ኮማንድ የተባለው ቡድን በፓራጉዋይም ክንፉን ዘርግቶ ተንሰራፍቶ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም በፓራጉዋይ ትልቁ የተባለው የኮኬይን ክምችት የተገኘው ከአመት በፊት ሲሆን ይህም 22 ኩንታል ነበር።