ኬንያ፡ ፍርድ ቤት በነፃ ያሰናበተው ኬንያዊ ሽብር ተጠርጣሪ በታጣቂዎች ታገተ

ሊባን አብዱላሂ በፍርድ ቤት ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው ዌስት ጌት የገበያ ማዕከል ላይ ጥቃት ፈፅመዋል በሚል በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከነበሩት መካከል አንደኛው ፍርድ ቤት በነፃ ቢያሰናብተውም ባልታወቁ ታጣቂዎች መታገቱ ተሰምቷል።

የሽብር ጥቃቱ በጎሮጎሳውያኑ 2013 የደረሰ ሲሆን በዚህም ጥቃት 71 ሰዎች ሞተዋል ተብሏል።

ሊባን አብዱላሂ ኦማር የተባለው ግለሰብ ነው በዚህ ሽብር ጥቃት እጁ የለበትም ብሎ ፍርድ ቤቱ በዚህ ሳምንት ረቡዕ በነፃ ያሰናበተው።

ወንድሙ የሽብር ጥቃቱን ካደረሱት መካከል አንዱ ነው የተባለ ሲሆን በወቅቱም በፖሊስ ተገድሏል።

ሃሙስ እለትም ሊባን ተሳፍሮበት የነበረውን ታክሲ መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦች አስቁመውም እንዳገቱትም የአይን እማኞች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የሶማሌ ስደተኛ የሆነው ሊባን የታገተውም የፖሊስ ፀረ-ሽብር ቢሮ ሲወጣ መሆኑንም የእስልምና እምነት ተከታዮች የሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰራ መንግሥታዊ ድርጅት ዳይሬክተር ኬሌፍ ካሊፋ ለቢቢሲ አሳውቀዋል፥

ታስሮበት ከነበረው ካማቲ እስር ቤትም ከተለቀቀ በኋላም ፀረ-ሽብር ቢሮው የሄደው መጨረስ ያለበትን ጉዳዮችም ለማጠናቀቅ ነው ተብሏል።

ባለ ጥቁር ኮፍያ ያለው ሹራብ የለበሱ ታጣቂዎች ታክሲውን ካስቆሙ በኋላም የደህንነት ኃይል መሆናቸውን መናገራቸውንም ጠበቃው ምቡጋ ሙሬቲ ለኬንያው የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

ፖሊስ ምንም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ያገቱት ግለሰቦችን ማንነት በተመለከተ ማንም አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠብም በጠራራ ፀሃይና በቀን እንዲህ ታጥቀው ሊባንን ሊያግቱት የሚችሉት ከፖሊስ ፀረ-ሽብር ቢሮ ጋር ግንኙነት ያላቸው እንደሆኑ በርካቶች እየተናገሩ ነው።

በሽብር ተጠርጥረው ፍርድ ቤት በነፃ ያሰናበታቸው ግለሰቦች አብዛኛውን ጊዜ ደብዛቸው ይጠፋል ወይም ተገድለው ይገኛሉ። በግድያቸውም ሆነ በመጥፋታቸው ተጠያቂ የሚሆን አካልም የለም።

የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ግን በዘፈቀደና በጭካኔ ለሚገደሉትም ሆነ ለሚጠፉት የፀጥታ ኃይሎችንና ፖሊስን ጥፋተኛ ያደርጋሉ።

አምነስቲ በተደጋጋሚ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች ፖሊስ ዳኛም ሆነ የሞት ፍርድ መፍረድ አይችልም ቢልም ፖሊስ በበኩሉ በነዚህ እገታዎችም ሆነ ግድያዎች እጄ የለበትም ይላል።

በጎሮጎሳውያኑ 2013 በዌስት ጌት የመገበያያ ማእከል በደረሰው ጥቃት ታጣቂዎች በሸማቾች ላይ ተኩስ የከፈቱ ሲሆን፤ ለአራት ቀናት ያህልም ቆይቷል። በዚህም ቢያንስ 62 ንፁሃን ዜጎች፣አምስት ፖሊሶችና አራት ታጣቂዎች ተገድለዋል።