አትሌቲክስ፡ ለተሰንበት ግደይ የ5 ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን ሰበረች

ለተ ሰንበት ግደይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያዊቷ ሯጭ ለተሰንበት ግደይ በትናንትናው ዕለት የአምስት ሺህ ሜትር ርቀት ክብረ ወሰን ሰብራለች።

ቫለንሺያ በተደረገው በዚህ ውድድር በጥሩነሽ ዲባባ ለአስራ ሁለት አመታት ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን አሻሽላለች ተብሏል።

የ22 ዓመቷ ሯጭ የገባችበትም ሰዓትም 14 ደቂቃ ከ6.62 ሰኮንዶች ሲሆን የጥሩነሸ ደግሞ 14 ደቂቃ ከ11.15 ሰኮንዶች ነበር።

በትናንትናው ዕለት ከሷ በተጨማሪ ኡጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕተጊ በቀነኒሳ በቀለ ለአስራ አምስት ዓመታት ተይዞ የነበረውን የ10 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን በስድስት ሰኮንዶች በማሻሻልም ሰብሯል።

የ24 ዓመቱ ሯጭ የገባበትም ሰዓት 26 ደቂቃ ከ11 ሰኮንዶች ነው ተብሏል።

በስፔኗ ቫለንሺያ ከተማም ሁለት ክብረ ወሰኖች የተሰበሩበት እለትም ሆኗል።

"በጣም ተደስቻለሁ" በማለትም ለተሰንበት ከሩጫው በኋላ ተናግራለች።

ከዓመት በፊት በዶሃ ተካሂዶ የነበረውን የአለም ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር ብር አግኝታ የነበረ ሲሆን " ለረዥም ጊዜ ሳልመው የነበረ ነው። ለኔ በጣም ትልቅ ነው" በማለትም ተናግራለች

በቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የነበረው 26፡ 17፡53 ሰዓት በወንዶች 10 ሺህ ሜትር ለረዥም ጊዜ በመያዝ ታሪካዊ የተባለ ክብረ ወሰን ነው።

ጆሹዋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጆሹዋ በአስር ወራትም ውስጥ አራት የአለም ክብረ ወሰኖችን መጨበጥ ችሏል።

በታህሳስ ወር የ10 ኪሎ ሜትር የመንገድና በየካቲት ወር እንዲሁም የ5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ክብረ ወሰኖችን ይዟል።

ነሐሴ ወር ላይ በነበረው የሞናኮ ዳይመንድ ሊግም በቀነኒሳ በቀለ ለ16 አመታት ተይዞ የነበረውን የ5 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰንም በሁለት ሰኮንዶች በማሻሻል ሰብሯል።

'የዓለም ሬኮርድ (ክብረ ወሰን) ቀን' በተባለው በዚህ ውድድርም በቫለንሺያ ቱሪያ ስታዲየም 400 ሰዎች በተገኙበት ተካሂዷል።