''በኳታር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በሙቀቱ ተቸግሯል'' የቡድኑ መሪ

የኢትዮጵያ ቡድኑ መሪ ዶክተር በዛብህ ወልዴ
የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ ቡድኑ መሪ ዶክተር በዛብህ ወልዴ

በኳታር የሚገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በሀገር ቤት ከነበረው ቀዝቃዛ የአየር ጸባይና ከፍተኛ ዝናብ አንጻር ወደ ኳታር ሲሄድ በሙቀት ምክንያት መቸገሩን የቡድኑ መሪ የሆኑት ዶክተር በዛብህ ወልዴ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

''ሙቀቱ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ገምተን ነበር፤ ነገር ግን የአየሩ ሁኔታ ከገመትነው በላይ ሆኖ እንኳን ለሩጫ ውድድር ቆሞ መራመድ አስቸጋሪ ሆኖ ነው ያገኘነው። በዚሁም ምክንያት የማራቶኑ ሃሳባችን አልተሳካም፤ የአስር ሺውም ቢሆን መጥፎ ባይባልም እንዳሰብነው አልሆነም።''

በማራቶን ውድድር ወቅት በሙቀቱ ምክንያት አቋርጠው የወጡት ሦስቱም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም የቡድን መሪው አክለዋል።

''ሯጮቹ በሰውነታቸው ውስጥ የውሃ ማነስ ነበር ያጋጠማቸው፤ ይሄን ያህል ለአደጋ የሚሰጣቸው ግን አይደለም።"

በኳታር ካለው ከፍተኛ ሙቀት አንጻር ቡድኑ ከፍተኛ ሙቀት ባለባቸው አካባቢዎች ሄዶ ልምምዱን እንዲሰራ ታስቦ የነበረ ቢሆንም በብዙ ምክንያቶች ሳይሳካ መቅረቱንም የቡድን መሪው ጨምረው አስረድተዋል።

''እንደዚህ አይነት ነገር ለመተግባር ከባድ ነው። ወደታች በወረድን ቁጥር ከሙቀቱ ጋር አብረው የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ" ያሉት ዶ/ር በዛብህ ሙቀት ቦታ ልምምድ መስራት ለእንደዚህ አይነት ውድድሮች ጠቃሚ ቢሆንም ብዙ ጉዳቶችም እንዳሉት ጠቅሰዋል።

አትሌቶች በምን አይነት ሁኔታ ልምምድ መስራት አለባቸው ለሚለው ጥያቄ አሰልጣኞች ወደፊት ብዙ መነጋገርና ሃሳብ ማቅረብ እንዳለባቸውም ዶክተር በዛብህ ወልዴ ጠቁመዋል።

በካታር ዶሃ እየተካሄደ ባለው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና ላይ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ ከትራንስ ኢትዮጵያ ክለብ በተገኘቸው ለተሰንበት ጊደይ አማካይነት አግኝታለች።

ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ ከብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ለተሰንበት ጊደይ በዶሃ
የምስሉ መግለጫ, ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ ከብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ለተሰንበት ጊደይ በዶሃ

ለተሰንበት ጊደይ ውድድሩን 30 ደቂቃ ከ21 ሰከንድ ከ23 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰአት በማጠናቀቅ የሁለተኛ ደረጃን ይዛ መጨረስ ችላለች።

ከፍተኛ ፉክክር በታየበት የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ኔዘርላንድስን ወክላ የተወዳደረችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲፈን ሃሰን የወርቅ ሜዳሊያውን ወስዳለች።

በውድድሩ ኬንያዊቷ አትሌት አግኔስ ትሪፖ ሦስተኛ ደረጃን ስትይዝ፤ በውድድሩ የተሳተፈችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ስድስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ከቢቢሲ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገችው ለተሰንበት ''ውድድሩ በጣም አሪፍ ነበረ፤ አየሩም ቢሆን ከውጪ ነው የሚሞቀው እንጂ ስታዲየም ውስጥ ብዙም አላስቸገረኝም'' ብላለች።

በመጨረሻዎቹ ዙሮች አንደኛ ከወጣችው ሲፈን ሃሰን ጋር የነበረው ፉክክር ምን እንደሚመስልና እንዴት ልታሸንፋት እንደቻለች ስትጠየቅ ለተሰንበት ይህንን ብላለች።

''በዚህ ውድድር ሜዳሊያ አግንቼ ስለማላውቅ አዲስ ሆኖብኝ ነበር፤ በቀጣይ ብዙ የማስተካክለው ነው። እስከመጨረሻው ድረስ ሄጄ ነበር ግን እሷ በአቅም ትንሽ በልጣኛለች'' ስትል በቁጭት ተናግራለች።

ውድድሩ ሲጀመርም ኢትዮጵያዊያን በቡድን ተጋግዘው ለማሸነፍ ተመካክረው እንደነበር የገለጸችው ለተሰንበት ''በመጀመሪያዎቹ ዙሮች ሌሎች አትሌቶች መምራት ሲጀምሩ ደስ ብሎን እየጠበቅናቸው ነበር'' ብላለች።

''ወደ መጨረሻ ላይ ግን እንዳሰብነው ሳይሆን ተበታተንን''።

ኢትዮጵያዊያን ደጋፊዎች

ውድድሩ በተካሄደበት ግዙፉ ካሊፋ ስታዲየም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን ለመደገፍ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የተገኙ ሲሆን ለአትሌቶቹ ሞቅ ያለ ድጋፍ በመስጠት ምሽቱን አድምቀውት እንደነበር የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ጎላ ብሎ የሚሰማ ዝማሬ ሌሎች ታዳሚዎችንም ጭምር ስቦ ነበር። በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ያጌጡት ደጋፊዎች ግዙፋ የስታድየም ስክሪን ላይም ተደጋግመው ሲታዩ አምሽተዋል።