ሹራ ቂጣታ፡ “የለንደን ማራቶንን ያሸነፍኩት በቀነኒሳ ምክር ነው”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከትናንት በስቲያ እሁድ ዕለት በተካሄደው የለንደን ማራቶንን በማሸነፍ ዓለምን ያስደነቀው አትሌት ሹራ ቂጣታ የድሉ ምክንያት የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ምክር መሆኑን ለቢቢሲ ተናገረ።
ሹራ ከውድድሩ በፊት ከአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ጋር ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሶ፤ ቀነኒሳ እግሩ ላይ ባጋጠመው ጉዳት በውድድሩ ሳይሳተፍ መቅረቱን ያስታውሳል።
"ከውድድሩ በፊት ቀነኒሳ ብዙ ምክር ለግሶኛል። ቀድመህ ወጥተህ እንዳትመራ፣ እራስህን እየጠበክ እሩጥ፣ ከፊት ሆነህ ከንፋስ ጋር አትጋፈጥ፣ ውሃም በደንብ ውሰድ፣ ውሃ ልታነሳ ስትል ደግሞ ከሌሎች ሯጮች ጋር እንዳትጋጭ ተጠንቀቅ ብሎ መክሮኛል" በማለት ከአትሌት ቀነኒሳ ያገኘውን ምክር ያስረዳል።
"እኔም እሱ እንዳለኝ ነበር ያደረኩት። ወደፊትም የወጣሁት እሱ በነገረኝ ኪሎ ሜትር ላይ ነው። በዚህ ምክንያት ነው ውድድሩን ማሸነፍ የቻልኩት" በማለት አትሌት ሹራ ውድድሩን በድል ለማጠናቀቅ የአትሌት ቀነኒሳን ምክር ወሳኝ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።
የዚህ ዓመቱ የለንደን ማራቶን ላይ በኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለና በበኬንያዊው ኢሉድ ኪፕቾጌ መካከል የሚደረገውን ፉክክር ዓለም በጉጉት እየተጠባበቀ በነበረበት በመጨረሻው ሰዓት ላይ ቀነኒሳ ባቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት በውድድሩ ዋዜማ ከውድድሩ መውጣቱ ይታወሳል።
ከውድድሩ በፊት የለንደን ማራቶንን ያሸንፋል ተብሎ በስፋት ተጠብቆ የነበረው የርቀቱ የክብረ ወሰን ባለቤት ኬኒያዊው ኤሊዩድ ኪፕቼጌ ነበር።
ይሁን እንጂ የተጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ ኪፕቼጎ 8ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
"ሚዲያው ሲያወራና ሲያስተላልፍ የነበረው ስለ እነኪፕቾጌ ነበር" ያለው ሹራ፤ ይህን ውድድር ለማሸነፍ እልህ አስጨራሽ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበረ ለቢቢሲ ገልጿል።
"ወድድሩ ከባድ ነበር። የአየር ሁኔታውም ዝናባማ ነበር። ጠንካራ አትሌቶችም ነበሩበት፤ ይሁን እንጂ 80 በመቶ ውድድሩን እንዳሸንፍ የሚያስችለኝን ጠንካራ ዝግጅት አድርጌ ስለነበረ ለድል በቅቻለሁ" ሲል አትሌት ሹራ ቂጣታ ያደረገውን ዝግጅት ተናግሯል።
ኬኒያዊው አትሌት ኪፕቾጌ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ በውድድሩ ለመሸነፉ ዋነኛ ምክንያት በውድድሩ ላይ እያለ በጆሮው ላይ ባጋጠመው እክል ምክንያት መሆኑን አስፍሮ ነበር።
"ከ25ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ጆሮዬ ተደፍኖ አልከፈት አለኝ። ስፖርት እንዲህ ነው። ሽንፈትን ተቀብለን በቀጣይ ለማሸነፍ ማተኮር አለብን" ያለው አትሌት ኪፕቾጌ ለተደረገለት ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቧል።
አትሌት ኪፕቾጌ በውድድሩ ለመሸነፉ ዋነኛው ምክንያት ጆሮው መደፈኑ መሆኑን በገለፀበት ጽሁፉ አስተያየት መስጫ ሥር በአትሌት ሹራ ስም በተከፈተ ገጽ ምክንያቱን የሚያጣጥል ምላሽ ተሰጥቶ በርካቶች ሲጋሩት ነበር።
ይህንን በተመለከተ በቢቢሲ የተጠየቀው አትሌት ሹራ፤ ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላም ከኪፕቾጌ ጋር እንዳልተገናኙ እንዲሁም ከኪፕቾጌ የፌስቡክ ጽሑፍ ሥር በስሙ የተሰጠው አስተያየት የእርሱ አለመሆኑን ተናግሯል።
የ2018 ለንደን ማራቶን በ2ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው አትሌት ሹራ ቂጣታ የዚህ ዓመቱ የማራቶን ድል "ትልቅ ደስታ እና መነሳሳትን ፈጥሮልኛል" ብሏል።
"በሽልማት በኩል ለውድድሩ አሸናፊው የተሰጠው ከነበረው የሽልማት መጠን የዘንድሮ በ50 በመቶ ቀንሷል። 30 ሺህ ዶላር አካባቢ ነው የተሸለምኩት። ሌሎች ሽልማቶችም ይኖራሉ" ሲል አትሌት ሹራ ቂጣታ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በሹራ ቂጣታ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የለንደኑ የወንዶች ማራቶን ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያን ሯጮች በበላይነት አጠናቀዋል።
በዚህም መሰረት በውድድሩ ሁለተኛ ከወጣው ኬንያዊው ቪንሰንት ኪፕቹምባ ውጪ ከአንድ አስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቁት ኢትዮጵያውያን ናቸው።
አሸናፊው ሹራ ቂጣታ፣ ሦስተኛ ሲሳይ ለማ፣ አራተኛ ሞሰነት ገረመው፣ አምስተኛ ሙሌ ዋሲሁን እና ስድስተኛ ታምራት ቶላ ተከታትለው በመግባት አሸናፊ መሆናቸው ይታወቃል።















