ለንደን ማራቶን፡ ያልተጠበቀው ኢትዮጵያዊ ሹራ ቂጣታ በለንደን ማራቶን ማሸነፍ ዓለምን አስደመመ

ያልተጠበቀው ኢትዮጵያዊ ሹራ ኪታታ በለንደን ማራቶን ማሸነፍ አለምን አስደመመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሹራ ኪታታ መጨረሻው ዙር ላይ

የአለም የማራቶን ሬኮርድ ባለቤት ኢሉይድ ኪፕቾጌን በማሸነፍ ኢትዮጵያዊው ሹራ ቂጣታ በዛሬው የለንደን ማራቶን ያልተጠበቀ ድልን ተጎናፅፏል።

የለንደን ማራቶን አራት ጊዜ አሸናፊው ኪፕቾጌ እንደሚያሸንፍ ብዙዎች ባይጠራጠሩም ባልተጠበቀ ሁኔታ ሁለት ዙር ሲቀረው ወደኋላ ቀርቶም በዚህ ውድድር ስምንተኛ ሆኗል።

ኢትዮጵያዊው ሹራና ኬንያዊው ቪንስንት ኪፕቹምባ ተከታትለው አንደኛና ሁለተኛ የሆኑ ሲሆን፣ ሹራ ያሸነፈበትም ሰዓት 2፡05፡41 ነው።

በሴቶችም የማራቶን ውድድር የክብረ ወሰኑ ባለቤት ብሪጅድ ኮሴጊ አሸንፋለች።

"በጣም ነው ያዘንኩት፣ ምን እንደተፈጠረ አላውቅም" በማለትም ኪፕቾጌ ከውድድሩ በኋላ ተናግሯል።

"በመጨረሻዎቹ 15 ኪሎሜትሮች የቀኝ ጆሮዬ ተደፍኖ ነበር። በጭኔና ጉልበቴም የቁርጥማት ህምም እየተሰማኝ ነበር" ያለው ኪፕቾጌ አክሎም

"ድንገት በውድድሩ ላይ ያጋጠመኝ ነው። ውድድሩን በመልካም ሁኔታ ነበር የጀመርኩት። አየሩ በጣም ቀዝቃዛ ነበር ግን እሱን ምክንያት አላደርግም" ብሏል።

ባቱ ላይ ባጋጠመው አደጋ ምክንያት ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን ማቋረጡን ተከትሎም ኪፕቾጌ በቀላሉ ያሸንፋልም የሚል ግምት ተቀምጦ ነበር።

በ2፡01፡39 የኦለምን ሬኮርድ የተቆናጠጠው የ35 አመቱ ኪፕቾጌ ስምንተኛም ቢሆን ውድድሩን ሳያቋርጥ ጨርሷል።

በተለይም ውድድሩ አስራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው ሹራ ሩጫውን ያፋጠነው ሲሆን ኪፕቾጌም ምቾት ተነስቶ ታይቷል።

በርካቶች ውድድሩን ያቋረጡ ሲሆን ሹራ በአንደኛነት፣ በሁለተኛነት ኬንያዊው ኪፕቹምባና በሦስተኛነት ሲሳይ ለማ ተከታትለው ገብተዋል።

የ24 ዓመቱ ሹራ ኪፕቹምባን በአንድ ሰኮንድ የቀደመው ሲሆን ሲሳይን ደግሞ በሶስት ሰኮንዶች ብቻ ነው።

"ለዚህ ውድድር በደንብ ተዘጋጅቼ ነበር። ቀነኒሳ በቀለም በጣም ነው የረዳኝ፤ በማሸነፌ ደስተኛ ነኝ" ብሏል።

ኢትዮጵያውያኖቹ ሞስነት ገረመው፣ ሙሌ ዋሲሁንና ታምራት ቶላም ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ቦታ ይዘዋል።