ኬንያዊው አትሌት ኪፕቾጌ የዓመቱ የዓለም የስፖርት ኮከብ ሆኖ ተመረጠ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
የማራቶኑ ጀግና ኤሉድ ኪፕቾጌ ቢቢሲ በሚያደርገው ምርጫ የአመቱ የዓለም የስፖርት ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
ኪፕቾጌ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች በማጠናቀቅ ታሪክ የሰራ የመጀመሪያው ሯጭ መሆን ችሏል።
የ35 አመቱ ኬንያዊ በኦስትሪያዋ መዲና ቪየና በተደረገው የማራቶን ወይም የ42.2 ኪሎሜትር ርቀትን በ1 ሰዓት ከ 59 ደቂቃ ከ 40 ሰኮንዶች በመግባት አለምን አስደምሟል።
ይህንንም ውድድር ከማሸነፉ ከስድስት ወራት በፊት የለንደንን ማራቶን ለአራተኛ ጊዜ አሸንፏል።
ከሶስት ዓመት በፊት ሪዮ በተደረገው የኦሎምፒክ ውድድር አሸንፎ የነበረው ኪፕቾጌ፤ ለንደን ላይ ባደረገው ውድድርም በሃያ ስምንት ሰኮንዶች የሪዮ ሰአቱን አሻሽሎታል።
ለህዝብ ክፍት በነበረው በዚህ የኮከብነት ምርጫም አሜሪካዊቷን የጂምናዝየም ስፖርተኛ ሲሞን ቢሌስ፣ የደቡብ አፍሪካ የራግቢ ተጫዋቹን ሲያ ኮሊሲ፣ የክሪኬት ተጫዋቹን ስቲቭ ስሚዝ፣ አሜሪካዊው ጎልፍ ተጫዋች ታይገር ውድስና አሜሪካዊቷ እግር ኳሰኛ ሜጋን ራፒኖን በመርታት ኪፕቾጌ አሸንፏል።
በባለፈው አመት ጣልያናዊው የጎልፍ ተጫዋች ፍራንቸስኮ ሞሊናሪ ማሸነፉ ይታወሳል።












