አፍሪካ፡ በናይጄሪያ የፖሊስ ጭካኔን ለመቃወም በተጠራው ሰልፍ ላይ ሁለት ሰዎች ተገደሉ

የፖሊስ ጭካኔን ለመቃወም የወጡ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፖሊስን የጭካኔ በትር መቋቋም አልቻልንም ያሉ ናይጄሪያውያን ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ስድስተኛ ቀናቸውን ይዘዋል።

በናይጄሪያ ትልቋ ከተማ ሌጎስ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ላይም አንድ ፖሊስና ሰላማዊ ዜጋ ተገድለዋል።

ፖሊስ ቀጥታ በሰልፈኞቹም ላይ ጥይት ተኩሷል የሚሉ ሪፖርቶችም እየወጡ ነው።

እነዚህ ተቃውሞዎች በተለይም ዘረፋን ለማስቆም የተቋቋመውን ልዩ የፌደራል ፖሊስ ክፍል ወይም ሳርስ ተብሎ የሚታወቀው ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።

ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን ማሰር፣ ማሰቃየትና ግድያም ይፈፅማል በሚልም ከፍተኛ ውግዘትም የቀረበበት ሳርስ እንዲበተን ተደርጓል።

ሆኖም የሳርስ አባላት በሌሎች የፖሊስ ክፍሎች እየተሰማሩና እየተመደቡ ነው የሚሉ ጉዳዮች መሰማታቸውን ተከትሎም እንደገና ተቃውሞቹ የቀጠሉት።

ሰልፈኞቹ እነዚህ የሳርስ አባላት ለፈፀሙት ወንጀል ህግ ፊት መቅረብ አለባቸውም እያሉ ነው።

ይህንንም ተከትሎ በተጋጋለው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በርካታ ተቃዋሚዎችና ፖሊስ እንደተጋጩም የቢቢሲ ዘጋቢ አይዛክ ካሊድ ከመዲናዋ አቡጃ ዘግቧል።

በትልቋ ከተማም ሌጎስ ሱሩሌ በሚባለው አካባቢ ፖሊስ በትናንትናው እለት ጥይት እንደተኮሰም ገልጿል።

አንዳንድ ሰልፈኞች በፖሊስ ላይ ድንጋይ መወርወራቸውንም ተከትሎ ፖሊስ " የታጠቁ ሰልፈኞች" ናቸው በማለት ፈርጇቸዋል።

አንድ ፖሊስ መሞቱንና ሌላኛው ደግሞ ክፉኛ መጎዳቱንም ፖሊስ አስታውቋል።

ከዚህም በተጨማሪ በተቃውሞ ሰልፉ ላይ የሞተው የ55 አመቱ ሰላማዊ ግለሰብ ሞት ላይ ኃላፊነቱ የማን ነው በሚል የሌጎስ ፖሊስና ሰልፈኞች እየተወዛገቡ ይገኛሉ።

የፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ረዳት በበኩላቸው በሰልፈኞቹ ላይ ጥይት መተኮሱን አውግዘዋል።

የሌጎስ አየር መንገድን መንገድ የዘጉ ሰልፈኞችንም ለመበተን የታጠቁ ወታደሮችና መኪኖች እንደሚሰማሩም ሪፖርቶች እየወጡ ነው።

ከሰሞኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት "ስር ነቀል" የፖሊስ ማሻሻያ እንደሚደረግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉትም የሳርስ አባላት ወደ ፍርድ ይቀርባሉ ብለው ነበር።

ሆኖም በትናንንትናው ዕለት ፖሊስ በሰልፈኞች ላይ ጥይት መተኮሱ የነበረውን ተቃውሞ የበለጠ ሊያቀጣጥለው እንደሚችልም የቢቢሲ ዘጋቢ ይናገራል።

ፕሬዚዳንቱ ሰኞ እለት ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ሳርስን መበተን የመጀመሪያ ሂደት ሲሆን ሌሎች ማሻሻያዎች ይኖራሉ ብለዋል።

ሆኖም የፖሊስ አባላቱ ጠንካራ ሰራተኛ እንደሆኑ ገልፀው በጥቂት መጥፎ ፖሊሶች ምክንያት አጠቃላይ የፀጥታ ኃይሉ ስም ሊጠለሽ አይገባም ብለዋል።

የናይጄሪያ ፖሊስ ኃላፊ መሃመድ አዳሙ በበኩላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያደረሱ ፖሊሶች የሲቪል ማህበረሰቡን ጨምሮ ከሌሎች አካላት በተዋቀረ ኮሚቴ ማጣራት ይደረጋል ብለዋል።

የፖሊስ ጭካኔን ለመቃወም የወጡ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters